(የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ በ2004 ዓ.ም የመምህራን ደመወዝ ጭማሪን አስመልከቶ በተነሳው ተቃውሞ መምህራኑን አነሳስተሀል ተብሎ ከመምህርነት ሙያው የተባረረ ነው)
ከሁኔ አቢሲኒያዊ
- ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 3481 መምህራን ከስራቸው ለቀዋል
- አዲስ አበባ ውሰጥ በበርካት ት/ቤቶች በአንድ ክፍል ውስጥ ከ90 በላይ ተማሪ ይማራል
- ልጁን በመንግስት ት/ቤት የሚያስተምር አንድም ባለስልጣን የለም
- በስኳር ቴክኖሎጂ የተማረ የሰው ኃይል የለም ብለዋል አቦይ ስብሀት
- ለየወረዳው ካድሬዎች እስከ 2500 የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ ተደርጓል
- በስብሰባ ምክንያት ቅዳሜ ማስተማር ያስቀጣል
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ትምህርት አስተሳሰብን ብሎም ኑሮን ይቀይራል ብለው በማመን ልጆቻቸውን ወደ አሰኳላ በመላክ የማስተማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው ለዚህም እንደምክንያት የሚያቀርቡት ልጆችን ማስተማር የነገ ህወታቸውን ማስተካከል ነው ብለው ስለሚያምኑ እና ትክክልም ስለነበሩ ነው ነገር ግን ባለፉት 23 ዓመታት የህወሀት ኢህአዴግ ዘመን ከጊዜው እና ካለው የህዝብ ቁጥር አንፃር የተማረ የሰው ኃይል ቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም ብዙሀኑ ህዝብ ግን ትምህርትን የሚማረው ነገ ተምሮ ምንም ተስፋ እንደሌለው ተረድቶ ነው፡፡
የዚህ ፅሁፍ ፀሀፊ ሀሳብ ኢትዮጵያ እውን ቁጥሩን አሳክታለች አላሳካችም ሳይሆን ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ የትምህርት አሰጣጥን ማሳየት ነው፡፡ከሰሞኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ ትምህርት ለሁሉም በማዳረስ አቻ እንዳልተገኘላት የህወሀት ታማኝ አገልጋይ የሆነው ደመቀ መኮንን በቴሌቪዥን መስኮታችን ብቅ ብሎ ነግሮናል ወይም ዋሽቶናል፡፡
በአንድ ወቅት ሁሉንም አውቃለው የሚለው ስብሀት ነጋ በስኳር ቴክኖሎጂ ሀገሪቷ ውስጥ ምንም የተማረ የሰው ኃይል እንደሌለ ሰንደቅ ለተበላው ጋዜጣ ተናግሮ ነበር ነገር ግን ይህ የህዝቡ በስኳር ቴክኖሎጂ ተምሮ ያለመመረቅ ፍላጎት ሳይሆን የመንግስት የተሳሳተ የትምህርት ፖሊሲ በዘልማድ እና ገበያውን እንዲሁም ሀገራችን የሚያስፈልጋትን የተማረ የሰው ኃይል አይነት ካለማወቅ የሚመጣ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዐት በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ኬሚስትሪ እና ፊዚክስ ተምረው እቤት ተቀምጠዋል ድህነታቸው ለህወሀት አሽከር ያደረጋቸው ወንድሞቻችን ደግሞ ኮብልስቶን እየሰሩ ይገኛሉ እነዚህ ወጣቶች ቀድሞውኑ የተሻለ የትምህርት ስርዓት እና ፖሊሲ ቢኖር ኖሮ አቦይ ስብሀት እንደሚሉን ምንም የተማረ የሰው ኃይል በሌለበት የስኳር ቴክኖሎጂ ተምረው እራሳቸውንም ሀገራቸውንም በቀየሩ ኖሮ፡፡
ደመቀ መኮንን እንደዛ ያለማፈር አፉን ሞልቶ የተናገረለት የሀገራችን የትምህርት ስርዐትን ለመታዘብ አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ የመንግስት ትምህርት ቤት ጎራ ማለት አልያም መምህራኑን ማነጋገር በቂ ነው፡፡
በትምህርት የተሻለ ደረጃ ደርሳለች በምትባለው አዲስ አበባ በርካታ ት/ቤቶች ውስጥ በአንድ ክፍል እስከ 90 የሚደርስ ተማሪ ይማራል ይኸውም ተማሪው በትክክሉ ትምህርት አንዳያገኝ ብሎም መምህሩ እውቀቱን በአግባቡ እንዳያደርስ የሚያደርግ ነው ይህንንም ችግር ስለሚያውቁ ነው ሁሉም ባለስልጣኖች ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገራት ብሎም ከፍተኛ ክፍያ በሚያስከፍሉ ት/ቤቶች የሚያስተምሩት ነገር ግን ልጆቻቸው እንኳን እንዲማሩ የማይፈቅዱበትን የመንግስት ት/ቤቶች ሀገሪቷ እንደተቀየረች ማሳያ አድርገው ያቀርቡልናል፡፡
መንግስት ማለትም ህወሀት ከትምህርት ይልቅ የፖለቲካው ነገር ያንገበግበዋል ፡፡ በቅርቡ ለሁሉም የህወሀት ኢህአዲግ ተቀጣሪ የየወረዳው የፖቲካ ሹመኞች በሀገሪቱ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ እስከ 2500 ብር የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ አድርጓል ከዚህ ቀደም በኑሮ ውድነቱ ተሰቃየን ሲሉ ከፍተኛ ዛቻ እና ከስራ ማባረር ለፈፀመባው መምህራን እና የመንግስት ሰራተኞች ትኩረት አለመስጠቱ ብሎም ደመወዛቸውን ለመጨመር አለማሰቡ ህወሀት ኢህአዴግ ከዜጎች በላይ ካድሬዎች የሚል ፅንሰ ሀሳብ ውስጥ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ት/ቤቶች በአሁኑ ሰዐት እንደበፊቱ ቅዳሜ እና እሁድ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጫ ከመሆን ይልቅ የካድሬ መሰብሰቢያ ማዕከል ወደመሆን ተሸጋግረዋል ቅዳሜ ቀን ተማሪዎቹን የማጠናከሪያ ትምህርት የሚጠራ ማንኛውም መምህር ስብሰባ እንዳወከ ተቆጥሮ በት/ቤቱ ኃላፊዎች ከፍተኛ ሆነ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርሰዋል ይህንንም ተከትሎ በርካታ መምህራን መምህርነት ሙያን እንደስራ መፈለጊያ ይጠቀሙበታል፡፡ በቅርቡ ከአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ለከተማው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ የቀረበው ማስረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 3481 መምህራን ስራቸውን ለቀዋል፡፡
እንግዲህ ይህንን ነው ባለልምዱ ውሸታም ደመቀ መኮንን ለውጥ ብሎ የሚነግረን፡፡
No comments:
Post a Comment