ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናቱ እና የተጠቀሱት ተቋማት ላይ ክስ የሚመሰረተው ሰሞኑን ‘‘ጃሃዳዊ ሃራካት’’ በሚል በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ደርጅት የቀረበው ዘጋቢ ፊልም በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ስር ያሉትን ተጠርጣሪዎች መብት ሲጣስ መከላከል ባለመቻላቸው፣ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀማቸው፣ በሕዝብ ሐብት ያለአግባብ በመገልገላቸው፣ የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ ባለመወጣታቸውና በሃይማኖት ጣልቃ በመግባታቸው የወንጀልና የፍትሐብሔር ክስ ይመሰረትባቸዋል። ክሱን የሚመሰርቱት በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ ባሉት ተጠርጣሪዎች ጠበቆች አማካኝነት ሲሆን ክሱም በሁለት ደረጃ ተከፍሎ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል።
ክሱን እያዘጋጁ ከሚገኙት ጠበቆች አንዱ የሆኑት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ክሱን በማስመልከት በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሚመሰረተው ክስ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይቀርባል ብለዋል። በኢቲቪ ላይ የሚመሰረተው የፕሬስ ክስ ቀጥታ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚቀርብ ሲሆን ክሱም ከሞራል ጉዳት ጋር እንደሚያያዝ ጠበቃው አስታውቀዋል።
‘‘መጀመሪያ ክርክራችን ዘጋቢ ፊልሙ እንዳይተላለፍ ነበር። ከተላለፈ በኋላ ግን ይግባኝ ማለት ሳይጠበቅብን ይሄንን ጉዳት ባደረሱ አካላት ማለትም ፊልሙን በሰሩት፣ ፖሊስና የደህንነት ኃይሎች ጨማምረን ክሱ እንመሰርታለን’’ ያሉት ጠበቃ ተማም በፕሬስ ህጉ መሰረትም ዘጋቢ ፊልሙ በተላለፈ በሦስት ወራት ውስጥ ክስ መመስረት እንደሚያስችልም አያይዘው ገልፀዋል።
በኢቲቪ በተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ላይ በሚመሰረተው ክስ እስከ 100ሺህ ብር የሞራል ካሳ እንደሚጠየቅ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ክስ ደግሞ በሌላ መዝገብ በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በሚመሰረተው ክስ ለደንበኞቻችን የሞራል ካሳ እንዲካሱ፣ ደንበኞቻችን ይቅርታ እንዲጠየቁ፣ በተመሳሳይ የአየር ጊዜ ተሰጥቷቸው ደንበኞቻችን የራሳቸውን ኀሳብ እንዲሰጡ፣ በሃይማኖት ውስጥ በተደረገ ጣልቃ ገብነት ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚያደርግ ክስ ነው ብለዋል።
‘‘ክሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማያካትትበት ምክንያት የለም። የሀገሪቱ መሪ እሳቸው ናቸው። ፖሊስም እያደረገ ላለው ነገር ለምሳሌ ተጠርጣሪዎችን ቶርች በማድረግ ጭምር እንከሳለን። የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዘጋቢ ፊልሙ ያግዱ፣ አያግዱ የሚለውን አጣርተን የሚመለከታቸውን አካላት ለይተን ክሱን ለመመስረት ተዘጋጅተናል። ክሱን ለማዘጋጀት አስፈላጊ መረጃዎችን እየሰበሰብን ነው። በቅርቡም ክሱን እንመሰርታለን’’ ሲሉ ጠበቃ ተማም ጨምረው ገልፀዋል።
ደንበኞቻችን እራሳቸውን በማይከላከሉበት ሁኔታ ታስረው፣ መልስ እንዲሰጡ ባልተደረገበት ሁኔታ ስማቸው እንዲጠፋ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን የጠቀሱት ጠበቃው ዘጋቢ ፊልሙ የደንበኞቻችንን መልካም ባህሪ የገደለ (Character assination) ነው ብለዋል።
መንግስት በሽብርተኝነትና ከህገ-መንግስቱ በተቃራኒ ሃይማኖታዊ መንግስት ለማቋቋም ሲያሴሩ አግኝቻቸዋለሁ፤ በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰውና ከአለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን አልቃይዳ ጋር ከሚንቀሳቀሰው አል-ሻባብ ጋር ተመሳጥረው ሲሰሩ አግኝቻቸዋለሁ ባላቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ዘጋቢ ፊልም ማቅረቡ ይታወሳል።
ፊልሙ ከመተላለፉ በፊት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የእግድ ትእዛዝ ቢያስተላልፍም ፊልሙ ለሕዝብ አይታ መቅረቡ አይዘነጋም፤ ፊልሙ ለተመልካቾች ከቀረበ በኋላም አነጋጋሪ ሁኔታ መፈጠሩም ይታወቃል።
ፊልሙ ከመተላለፉ በፊት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የእግድ ትእዛዝ ቢያስተላልፍም ፊልሙ ለሕዝብ አይታ መቅረቡ አይዘነጋም፤ ፊልሙ ለተመልካቾች ከቀረበ በኋላም አነጋጋሪ ሁኔታ መፈጠሩም ይታወቃል።
ምንጭ፡ ሠንደቅ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment