ከስዩም ተሾመ
ሰኞ መስከረም 28/2010 ዓ.ም 5ኛው ዙር የ3ኛ አመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ይጀመራል። ይህን አስመልክቶ የሪፖርተር ጋዜጣ ሁለት ጥያቄዎች አቅርቦልኝ ነበር። የመጀመሪያው ባለፉት ሁለት አመታት በሀገራችን ከነበረው አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚወክሉትን ሕዝብ በሚገባ እያገለገሉት ነው ወይ?” የሚል ነበር። ይህ ጥያቄ ምክር ቤቱ በሕገ መንግስቱ ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት አንፃር መታየት አለበት። በዚህ መሰረት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቼ ነበር፡-
“ባለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ተቃውሞና አድማ ተካሂዷል። ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡት እና የሥራ አድማ የሚጠሩት፤ አንደኛ፡- በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 30ና 42 ላይ በግልፅ የተደነገገ ዴሞክራሲያዊ መብት ስለሆነ ነው፣ ሁለተኛ፡- ዜጎች የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ስላላቸው ነው። ነገር ግን፣ ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ ሲወጡ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ የብዙዎች ሕይወትና ንብረት ጠፍቷል። ይህ ሁሉ የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 55 መሰረት የተሰጣቸውን ስልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው ነው።”
ሁለተኛው የሪፖርተር ጥያቄ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉበትን ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ “በቀጣይ ምን መደረግ አለበት?” የሚል ነው። ለዚህ ጥያቄ የሰጠሁት ምላሽ በጣም አጭርና ግልፅ ሲሆን፣ እሱም “የምክር ቤቱ አባላት ለኢህአዴግ መንግስት ሳይሆን ለሕገ-መንግስቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናቸው ተገዢ በመሆን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጡ!” የሚል ነበር።
አዎ… እያንዳንዱ የሕዝብ ተወካይ ያለው ምርጫ የመሆንና ያለመሆን ምርጫ ነው። ለፌደራሉ መንግስት ተገዢና አገልጋይ መሆን ወይም ለሕገ-መንግስቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናው ተገዢ መሆን። የፌደራሉ መንግስት በአንድ ወገን፣ ሕገ-መንግስቱና ሕዝቡ በሌላ ወገን ሆነው ተለያይተዋል። ስለዚህ አንድ የምክር ቤት አባል ለፌደራሉ መንግስት እና ለሕገ መንግስቱና ለሕዝቡ እኩል ተገዢና አገልጋይ ሊሆን አይችልም።
ትላንት እኩለ ሌሊት ላይ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ራሳቸውን ከኃላፊነት አንሱ” የሚል ጭምጭምታ ስሰማ ብዙም አልገረመኝም። ምክንያቱም በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አፈ-ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ሆኑ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ያላቸው ምርጫ አንድና አንድ ነው። እሱም ኃላፊነታቸውን በፍቃዳቸው በመልቀቅ ራሳቸውን ከፌደራል መንግስቱ ማግለል ነው።
አፈ-ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በራሳቸው ፍቃድ ስልጣናቸውን የለቀቁበት ምክንያት በዋናነት በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል መካከል በተፈጠረው ግጭት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ-ገብነትን በመቃወም እንደሆነ ተሰምቷል። በእርግጥ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ነዋሪዎች ላይ እየፈፀመ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ መቆም ያለበትና ይህ እንዲሆን የፈቀዱ የክልሉ መንግስት ኃላፊዎች በሕግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁኔታውን ለመቆጣጠርና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ አይደለም። በመሆኑም የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በማንአለብኝነት ከ200ሺህ በላይ ዘጎችን ሲያፈናቅል ከ200 በላይ ደግሞ ገድሏል። በዚህም እንደ ምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ 8 መሰረት “የፌደራሉ መንግስት፤ የሀገርና የሕዝብ መከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ ኃይሎች የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ሲጥሱና የሀገር ደህንነትን የሚነካ ተግባር ሲፈፅሙ ተከታትሎ ማጣራትና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ” አልቻልም። በመሆኑም፣ አፈ-ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ለሕገ መንግስቱ፥ ለሕዝቡና ለሕሊናቸው ተገዢ በመሆን ራሳቸውን ከኃላፊነት ከማውረድ በስተቀር ሌላ ምርጫና አማራጭ የላቸውም።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ላለፉት አስር አመታት ሕገ መንግስቱ የተደነገጉ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን ሙሉ በሙሉ በሚጥሰው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አማካኝነት 1405 የሚሆኑ የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሃይማኖት መሪዎች፣….ወዘተ ተከሰው በእስር የማቀቁና እየማቀቁ ባለበት ሀገር ለሕገ መንግስቱ ተገዢ መሆን አይቻልም። ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ በተለይ በኦሮሚያ፥ አማራና ደቡብ ክልሎች ዜጎች መብትና ነፃነታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ ብዙ ሺህዎች ለሞት፥ እስራትና የአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 55(16) በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ይህን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም የተሳነው ምክር ቤት ተገዢነቱ ለአስፈፃሚው አካል እንጂ ለሕገ መንግስቱ፥ ለሕዝቡ ወይም ለሕሊናው አይደለም። ስለዚህ ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ልክ እንደ አፈ-ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ለሕገ መንግስቱ፥ ለሕዝቡ ወይም ለሕሊናቸው ተገዢ በመሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የደህንነትና የፖሊስ ኃይሎች በዜጎች ላይ ከሚፈፅሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሀገር ደህንነትን ከሚያናጋ ተግባር እንዲቆጠቡ ለማድረግ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው።
No comments:
Post a Comment