የሰበር ዜና ልክፍት የተጠናወተው የዘመኑ “ሚዲያ” የአባዱላን ከአፈጉባኤነት መልቀቅ በሰበር ዜናነት ማናፈሱ ቆም ብሎ ላየው ራስን ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። የአባዱላ መልቀቂያ ማስገባት “ምስጢር” በቅርቡ የሚለይለት ቢሆንም በህወሓት ተለክቶና ተጠፍጥፎ የተሠራ ድርጅትና ስብዕና ያለው ለዚህ ዓይነት የሞራል ልዕልና ይደርሳል ብሎ መገመት ህወሓትን ካለማወቅ ወይም ራስን ከመሳት የሚመነጭ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
በበርካታ የሙስና ተግባራትና ህይወት ማጥፋት አለበት እየተባለ የሚነገርለት አባዱላ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ተማርኮ በሻዕቢያ ፈቃድና በህወሓት ፈጣሪነት አዲስ ስብዕና ተሰጥቶት ኦህዴድ የሚባል የጀመረ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ይህ ስብዕናው ህወሓት በህንፍሽፍሽ ልትበታተን ስትል የኦሮሞውን ክንፍ ይዞ መለስን የታደገ በመሆኑ ባለውለታነቱ ለማን እንደሆነ በድጋሚ ያስመሰከረ ሆኗል።
በሌላው አንጻር አባዱላ የኦሮሚያ ዋና ኃላፊ በነበረበት ጊዜ ጁነዲን ሳዶ በኦሮሚያ የፈጠረውን ካቢኔ እና አደረጃጀት በማፍረስ አዲስ ለመለመላቸው የኦህዴድ አባላት “አትደግፉን ነገር ግን የክልሉን ልማት አታደናቅፉ” በማለት እስከ ቀበሌ የደረሰ አዲስ የካድሬ አደረጃጀት አዋቅሮ ነበር። አባዱላ ይህንን ተፈጻሚ ሲያደርግ የሄደበት የአደረጃጀት መንገድ የኦነግም ሆነ የተቀናቃኝ ፓርቲ አባላትን የኦህዴድ ጭምብል በማልበስ ነበር። ለዚህ ድፍረት ያበቃውም በህንፍሽፍሹ የነ ስዬና ተወልደን ውህዳን ቡድን በመቃወም ከመለስ ጋር በመወገን ኦህዴድን ለህወሓት በማዳኑ ከመለስ በተሰጠው “በኦሮሚያ ያሻህን አድርግ” ፈቃድ ነበር። ለካድሬው “ነጻነት” በመስጠት የተወዳጀው አባዱላ ባንድ ወገን ይህ ድርጊቱ የካድሬውን ፍቅር ሲቸረውና “ጃርሳው” ሲያስብለው በሌላው ግን ከአላሙዲ ጋር በግብር ጉዳይ፤ ከመለስ ጋር ደግሞ በተወዳጅነት ቅንዓት ጥርስ ውስጥ አስገባው። እንደ ሰይጣን ወዳጅ የሌለው ህወሓትም አባዱላን አፈጉባኤ በማለት አከሸፈው።
አንድ የማይካድ ሐቅ ቢኖር አባዱላ ኦሮሚያን ከለቀቀ ወዲህ ኦሮሚያ እንደቀድሞው መሆን አቅቷታል። የጁነዲን አርሲ ተኮር ኦህዴድ በጃርሳው ከተናደበኋላ ኦህአዴድም እንደ ድርጅት የህወሓት ሎሌነቱን በበላይ አመራሩ ብቻ ወስኖ የመካከለኛውና የበታቹ ከከዳ ሰንብቷል። በሙክታር ከዲር የሥልጣን ዘመን ከመለስ ሞት ጋር ተዳምሮ ህልውና ያጣውን ኦህዴድን ወደነበረበት የመመለስ ሥራ የለማ መገርሳ ትከሻ የማይሸከመው ሆኗል።
የመናገር፣ የመጻፍ፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ ወዘተ መብቶች በማይታሰቡባት ኢትዮጵያ እንደ ብአዴን በህወሓት ተጠፍጥፎ የተሠራው ኦህዴድና ከስም እስከ ስብዕና ተለክቶ የተሰጠው አባዱላ በቴሌቪዥን ቀርቦ “ሥልጣኔን እለቃለሁ” ብሎ በነጻነት መናገሩ አእምሮ ላለው “እንዴት” ብሎ እንዲጠይቅ የሚያስገድድ ተግባር ነው። በአደባባይ “ስኳር እወዳለሁ፤ ይጣፍጠኛል” አስብሎና አዋርዶ አብሮ የታገለውን ታምራት ላይኔን ያዋረደው ህወሓት፤ በርካታ “በቁምሳጥን ውስጥ የተደበቁ አጽሞች” ያሉበትን አባዱላ ለዚህ “ዕድል” ማብቃቱ ከአባዱላ የመልቀቂ ጥያቄ በላይ በሰበር ዜናነት ሊበሰር የሚገባው ነበር።
ለማንኛውም ሁኔታው በቅርቡ ግልጽ ይሆናል። የኦሮሚያ ጉዳይ እጅግ መከራ ውስጥ ያስገባው ህወሓት አባዱላን በጃርሳውነት ወደ ኦሮሚያ (ጨፌ) ይመልሰው ይሆናል (ከአፈጉባኤነት እንጂ ከድርጅቴ አለቀኩም ማለቱን ያጤኗል) ወይም በቅርቡ በሙስና ጉዳይ ተጠርጣሪ ከአገር እንዲስኮበልል አድርጓል፣ አንጃ ሆኗል፣ በሙስና ተጨማልቋል፣ … ብሎ ወደ ሸቤ ይወረውረዋል። አለበለዚያም ፋይሉ እንደ ተዘጋ ጉዳይ በመዝገብ ቤት በኩል ወደ “ዴድ ፋይል” ክፍል ይልከዋል። ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለመቆየት የሚያሰጋት በርካታ ጉዳይ መኖሩን ሳንዘነጋ ጥይታችንን በእንደዚህ ዓይነት አናሳ ዜና ላይ ከማባከን ይልቅ በህወሓት ላይ ማድረጉ ነጻነታችንን ቅርብ ያደርግልናል።
ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ታዛቢው ነኝ ከታላቋ እስርቤት ኢትዮጵያ (አዲሳባ) (ፎቶ፡ በተለምዶ አባዱላ የሚባለው ቶዮታ ሚኒባስ)
No comments:
Post a Comment