Translate

Sunday, October 8, 2017

HR 128/SR 168 ጸሐይ እየጠለቀችበት ነው!

ለኢትዮጵውያን ታላቅ ተስፋ ይዞ የተነሳው HR 128/SR 168 በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኘ ተነገረ። የህወሃት/ኢህአዴግን ህልውና በማያፈናፍን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከት ብዙ የተባለለት ይህ ረቂቅ ሕግ ወደ ሕግ መወሰኛ ምክርቤት ቀርቦ ድምጽ ከማግኘቱ በፊት ጊዜውን ጠብቆ እንዲሞት የማቀዛቀዝ ተግባር እየተፈጸመበት ነው። ኢትዮጵያውያን ተባብረው በመታገል ይህ ዕድል እንዳያመልጣቸው ማድረግ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተሰጠ።

ሐምሌ 20፤ 2009ዓም (7/27/2017) የህወሃት/ኢህአዴግን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታና አጠቃላይ አስተዳደርን የሚወቅስ የህግ ረቂቅ በዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መምሪያ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ፊት ቀርቦ በሙሉ ስምምነት ማለፉ ይታወሳል። ከውሳኔው በላይ የአሜሪካ ወዳጅ በመሆን ሕዝብን ለመከራና ስቃይ ሲዳርግ የኖረው የኢህአዴግ አገዛዝ በአሻባሪነቱ ከሚወገዘው ሒዝቦላ እና ከሰሜን ኮሪያ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ጋር በእኩል ቀርቦ መታየቱ “የአሜሪካና ኢህአዴግ ወዳጅነት ወዴት?” ያስባለ መሆኑን ጎልጉል ዘግቦ ነበር።
በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት H. Res. (house Resolution) 128 በመባል የሚታወቀው ረቂቅ በሕግ መወሰኛ ምክርቤት (ሴኔት) S. Res. (Senate Resolution)168 የሚል ስያሜ ያለው ነው። ረቂቅ ሕጉ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት ከሁለቱም ፓርቲዎች (ሪፓብሊካንና ዴሞክራት) በ68 እንደራሴዎች ድጋፍ ያለው ሲሆን በሕግ መወሰኛ ም/ቤት ደግሞ አሁንም ከሁለቱም ፓርቲዎች የ20 ሴናተሮችን ድጋፍ ያገኘ ነው።
ከዚህ በፊት እኤአ በ2003 ዓም የረቀቀውና HR 2003 ተብሎ ከሚጠራው ረቂቅ ሕግ በሚልቅ መልኩ የተዘጋጀውና እጅግ በርካታ ድርጅቶችና የኮንግረስ አባላት ድጋፍ የሰጡት ይህ ረቂቅ ሕግ እንቅፋት እንዳይገጥመው ተደረጎ የተዘጋጀና ያለአንዳች ችግር ለውሳኔ ያልፋል የሚል ግምት ተሰጥቶት ነበር። ሆኖም ገና ከጅምሩ የረቂቅ ሕጉ አካሄድ የሚያመጣበትን አስከፊ ውጤት የተገነዘበው ህወሓት ሕጉን ለማክሸፍ ሲታትር ቆይቷል።
ዘመነ ኦባማ
በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአስተዳደር ዘመን የበርካታ “ነጭ ወያኔዎች” ድጋፍ የነበረው ህወሓት “አሸባሪዎችን እዋጋለሁ” በሚል የአሜሪካንን ሙሉ ድጋፍ ሲያገኝ መቆየቱ ይታወሳል። አልሻባብን ጥሩ ሰበብ በማድረግ በኢትዮጵውያን ላይ የአሸባሪነትን ተግባር በሕግ ሲፈጽም አሜሪካም ሆነ ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአዞ እንባ ሲያነቡ ነበር የቆዩት።
የዛሬ አስር ዓመት እስላማዊ ፍርድቤቶች ሶማሊያን በተቆጣጠረ ጊዜና የሻዕሪያን ህግ በመተግበር ሰላምና መረጋጋት በሶማሊያ ማስፈን ሲጀምር፤ አክራሪና አሸባሪ ናቸው ብሎ በመወንጀልና በማስወንጀል ብልጣብልጡ መለስ የአሜሪካንን ድጋፍ አግኝቶ ነበር። “በኮንዶም አንዋጋም” እያለ ለንግግሩ ለከት ሳያደርግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በአፉ ሲቀዝን የነበረው መለስ፤ ሶማሊያን በወረረ ጊዜ “እዚያ የምንቆየው የሽግግር መንግሥቱ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እንዲችል ለጥቂት ቀናት ለማገዝ ነው፤ … ይህ ምናልባት አንድ ሳምንት ቢበዛ ደግሞ ሁለት ሳምንት” ሊፈጅ ይችላል ማለቱ የሚረሳ አይደለም። ሆኖም ህወሓት እስላማዊ ፍርድቤቶችን አስወግዶ አልሻባብን በምትኩ አስቀምጦ የመውጣት ያህል አሻጥር መፈጸሙ እየታወቀ “አሸባሪነትን በመወጋት” ስም የአሜሪካ ወዳጅ ሆኖ ቆይቷል። ይህንን ለመተግበር እስላማዊ ፍርድቤቶችን ከተዋጋና በሶማሊያ ክፍተት በመፍጠር ለአልሻባብ መፈልፈል ሁኔታውን ካመቻቸ በኋላ በጥር 2008ዓም ጦሩን ከሶማሊያ አስወጣ።
ፎቶ: የወያኔ ቀንደኛ ደጋፊ የUSAID በኢትዮጵያ ሃላፊ ጌይል ስሚዝ (በመኪናው ላይ የሚታየው ምህጻረ ቃል “ማረት” – ማኅበረ ረድኤት ትግራይ) – Photo: David Kahrmann USAID Ethiopia)
በአልሻባብ መጠናከር ምክንያት አሸባሪነት ያሳሰባት አሜሪካ አሚሶምን (በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሚሽን) በማጠናከርና ድጋፍ በመስጠት ጥቃቷን ስትቀጥል ህወሓትም ጦር እንደገና ልኳል፤ የ“ትርፉ”ም ተጠቃሚ ሆኗል።ለዚህ ውለታው ከባራክ ኦባማ “ዴሞክራሲያዊ አገር” እስከመባል የደረሰ ትልቅ ሙገሳ አግኝቷል። በሎንዶን የሚገኘው ቻተም ሃውስ እንደገመተው አልሻባብን ለመዋጋት ለአሚሶም የተመደበው በጀት እኤአ በ2009ዓም 300 ሚሊዮን ዶላር የነበረው በ2016ዓም ወደ 900ሚሊዮን ዶላር አድጓል።
ሆኖም ላለፉት በርካታ ዓመታት ከአሜሪካ በኩል የፖለቲካ ተጽዕኖ ሲነሳበት የአልሻባብን ካርድ በመምዘዝ ሲጫወት የነበረው ህወሓት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስሉሱ እየዞረበት ሲመጣ ጦሩን ከሶማሊያ በማስወጣት ለመናፈቅ ፈልጎ ነበር። የኦባማ ከሥልጣን መልቀቅና የነጭ ወያኔዎች አብሮ ከአስተዳደሩ ጋር መወገድ ህወሓትን በአደባባይ ደጋፊ አልባ አድርጎታል።
ዘመነ ትራምፕ
ባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በመንበሩ ላይ የተሰየሙት ዶናልድ ጄ ትራምፕ አስተዳደራቸው በአፍሪካ ላይ የተለየ አቋም የሚይዝ መሆኑ የተነገረው ገና ከጅምሩ ነበር። የትራምፕ የሽግግር ቡድን አፍሪካን በተመለከተ ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ መ/ቤቶች ያቀረበው ባለ አራት ገጽ ጥያቄዎችን ያዘለ መረጃ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቦበት ነበር። ከበርካታዎቹ ጥያቄዎች ጥቂቶቹ፤ “በአፍሪካ ይህንን ያህል ሙስና ተንሰራፍቶ እያለ ለአፍሪካ ከምንሰጠው ዕርዳታ ምን ያህሉ ይሰረቃል? እዚህ አሜሪካ ውስጥ በስንቱ እየተሰቃየን ይህንን ይህል ገንዘብ አፍሪካ ላይ የምናፈሰው ለምንድነው? …” የሚሉ ነበሩበት።
ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል “አልሻባብን ለአስር ዓመት ያህል ስንዋጋ ቆይተን ለምንድነው እስካሁን ያላሸነፍነው?” የሚለው ጥያቄ በራሱ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሳና ለብዙዎቹም መልስ የሚሆን ተደርጎ የተወሰደ ነበር።
አዳዲሶቹ የትራምፕ ሹማምንት በአልሻባብም ጉዳይ ወደ አፍሪካ ጉብኝት ሲያደርጉም ሆነ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ስብሰባ ለመቀመጥ ሲያስቡ እንደተለመደው ህወሓት/ኢህአዴግ ታሳቢ በማድረግ ሳይሆን መቅረቱ በህወሓት ዘንድ ጭንቀት ሲፈጥር ቆይቷል። በተለይ የመከላከያ ሚኒስትሩ ማቲስ ጅቡቲን ጎብኝተውና በአልሻባብ ጉዳይ ላይ መክረው ሲመለሱ ህወሓት በስብሰባው ላይ እንዳይገኝ ተደርጓል። ሚስተር ማቲስም ከጅቡቲ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ጉብኝት ሳያደርጉ ተመልሰዋል፤ የብሩ ቋትም መጉደል ከጀመረ ሰነባብቷል። በኦባማ አስተዳደር ዘመን ኢትዮጵያ የአሜሪካ “ስትራቴጂካዊ አጋር”የሚለው አነጋገር በትራምፕ ዘመን ሲነገር እስካሁን አለመሰማቱ ብቻ ሳይሆን ህወሓት የሚቆምርበት የአልሻባብን ጉዳይ አሜሪካ በራሷ የምትወጣው ጉዳይ አድርጋ መውሰዷ አቅጣጫዎች በገሃድ መቀየራቸውን ያመላከተ ሆኖ ታይቷል።
የትራምፕ አስተዳደር በአፍሪካ ላይ የተለየ አቋም የመያዙን ሁኔታ ተከትሎ በተለይ ከሕዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች አስመልክቶ የተቀናበረው HR 128 የህወሓት ሹሞችንና ቤተሰቦቻቸውን ያስጨነቀ መሆኑን ጎልጉል ዘግቦ ነበር። በዚህ ሁሉ መካከል የህወሓት ታዳጊ ሆነው ብቅ ያሉት የኦክላሆማው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ናቸው።
አክሻፊው ኢንሆፍ!
ሴናተር ኢንሆፍ (ፎቶ ምንጭ)
የትራምፕ አስተዳደር በህወሓት ላይ ፊቱን ማዞሩ ግልጽ ሆኖ በቆየበት ጊዜ የህወሓት ደጋፊ በመሆን “ኢትዮጵያ የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና በቀጣናው ሰላምንና መረጋጋትን በማስፈን ረገድ በአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር (ከአሜሪካ ጋር ያላት) ግንኙነት ይቀጥላል” ያሉት ሴናተር ኢንሆፍ ብቻ ናቸው።
አሁን በረቂቅ ሕግ መልክ የበርካታ የሕዝብ ተመራጮችን ድጋፍ አግኝቶ ወደ ሙሉ ድምጽ ምርጫ እየሄደ ያለው HR 128ከመተዋወቁ በፊት HR 2003 የሚባል ተመሳሳይ ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ ምክር ቤት ወጥቶ ነበር። ይህ ረቂቅ ሕግ በርካታ መሰናክሎችን አልፎ ድምጽ ወደመስጠቱ መስመር እየሄደ ባለበት ወቅት ያከሸፉት ሴናተር ጂም ኢንሆፍ መሆናቸው ይታወሳል።
በወቅቱ በጽ/ቤታቸው ድረገጽ ላይ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት፤“ይህ ረቂቅ ሕግ ዓላማው በኢትዮጵያ ‹ሰላምና መረጋጋትን ለማበረታታትና ለማመቻቸት ነው ቢልም› እንደ እውነታው ግን ጉድለት ላይ ትኩረት በመስጠት አገሪቱ ያደረገችውን ያልተጠበቀ ዕድገት በጉልህ የሚክድ ነው” ብለው ነበር። ሲቀጥሉም፤ “… በእርግጥ የ1997 ምርጫ ተከትሎ መንግሥት ከመጠን በላይ ኃይል ተጠቅሟል፤ ሆኖም ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት አግባብ ያለው ዴሞክራሲያዊ ሒደቶችን በመከተልና የሰብዓዊ መብቶችን በማክበር ወሳኝ እርምጃዎችን ወስዷል፤ … ምንም እንኳን ለአፍሪካ በተለይም ለኢትዮጵያ እየተሰጠ ያለውን ትኩረት የማደንቅ ብሆንም ነገር ግን ይህ ረቂቅ ሕግ (HR 2003) በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ግልጽ የሆነ መሻሻል እያደረገ ያለ አንድ ወዳጅ (አገር) ላይ (አስገዳጅ) ጥያቄዎችን በመጫን የተሳሳተ ዘዴ እየተከተለ ነው ብዬ አምናለሁ” በማለት ረቂቅ ሕጉ ህይወት አጥቶ እንዲሞት ቁልፍ ሚና በመጫወት ለህወሓት ታላቅ ውለታ የሠሩ ሰው ናቸው።
ሴናተሩ ከኢትዮጵያዊት ልጅ ልጃቸው ጋር (ፎቶ ምንጭ)
ልጃቸው ከኢትዮጵያ አንዲት እትብቷ ሳይቆረጥ ተጥላ የነበረች ህጻን ልጅ በጉዲፈቻነት በማሳደግ የጥቁር የልጅ ልጅ እንደሆኑ በኩራት የሚናገሩት ሴናተር ኢንሆፍ ከህወሓት ሌላ ከዑጋንዳው አምባገነን ሙሴቪኒ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው። በአማካይ በዓመት ሁለት ጊዜ ወደ አፍሪካ እንደሚጓዙ የሚነገርላቸው ኢንሆፍ ጉዟቸው ከሃይማኖት ጋር የተያያዘና ለአፍሪካ ልዩ ትኩረት ስላላቸው እንደሆነ ይናገራሉ። እኤአ ከ1998 እስከ 2008 ባሉት አስር ዓመታት ቢያንስ 20 ጊዜ ወደ አፍሪካ በመጓዝ ከማንኛውም የአሜሪካ ሴናተር ቀዳሚ ናቸው የሚባልላቸው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ለጉዟቸው ወታደራዊ አውሮጵላን መጠቀማቸውና እጅግ በርካታ የመንግሥት ገንዘብ ለጉዞ ማውጣታቸው አነጋጋሪ እንደሆነ ይነገራል
የቀደመውን ረቂቅ ህግ በማክሸፍ ቁልፍ ሚና የተጫወቱት እኚህ ሴናተር አሁንም HR 128/SR 168 ወደ መቃብሩ እንዲወርድ ተግተው እየሠሩ ነው። ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ መረጃ ያቀበሉ እንደሚሉት ሴናተሩ ያሁኑ ረቂቅ ሕግ እንዲከሽፍ የሚያቀርቡት ምክንያት፤
  • በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ሰላምና መረጋጋት እየተሻሻለ ነው፤
  • የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቷል፤
  • በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሊያሸንፉ የሚችሉበት የማሟያ ምርጫ በቅርቡ ይካሄዳል፤
የሚሉ ሲሆኑ እነዚህ ጉዳዮች በተለይ የምርጫው ውጤት ሳይታወቅ ይህንን ዓይነት ረቂቅ ህግ በማውጣት ተጽዕኖ ማድረግ ጉዳት ያስከትላል በማለት ለህወሓት እየተከራከሩ ይገኛሉ።
እንደ መረጃ ምንጮቻችን ሴናተሩ ከሕዝብ እንደራሴዎችም ይሁኑ ከአቻ ሴናተሮች ረቂቅ ህጉን የሚቃወሙ እያሰባሰቡና እያነሳሱ እንደሆነ ተነግሯል። ይህ ከፍተኛ ድጋፍ ያለው ረቂቅ ሕግ ለድምጽ እንዲቀርብ ቢደረግ በከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያልፍ የሚናገሩ ወገኖች በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት አሠራር መሠረት አንድ ሴናተር አንድ ረቂቅ ሕግ ወደ መድረክ ለድምጽ እንዳይቀርብ የማድረግ ሥልጣኑን መጠቀምና ረቂቅ ሕግጋትን የማክሸፍ፣ የማቀዛቀዝ፣ ወዘተ ልዩ መብት አለው።
ይህንን ረቂቅ ህግ ገና ከጅምሩ የፈራው ህወሃት ለወትዋቾች (ሎቢይስቶች) በጀት መድቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ አስር ወራት ሆኖታል። በዋሽንግቶን ዲሲ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ተጠሪ የሆነው ግርማ ብሩ SGR Government Relations ከተባለ የወትዋቾች ድርጅት ጋር በተፈራረመው ሰነድ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ለዚህ የውትወታ ሥራ ድርጅቱ በወር 150ሺህ ዶላር፤ በጥቅሉ 1.8 ሚሊዮን ዶላር ይከፈለዋል። በርካታ የተቃዋሚ ድርጅቶችና ቡድኖች (በተለይ በዳያስፖራ ያሉቱ) ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጡት ቀሩ እንጂ ሁኔታዎች እንዳላማሩለት የተረዳው ህወሓት የቤት ሥራውን መሥራት የጀመረው አስቀድሞ ነበር።
ከዚህ የውትወታ ሥራ በተጨማሪ ሴናተር ኢንሆፍ በHR128/SR168 ላይ ሰይፋቸውን መዝዘዋል። ከህወሓት ከፍተኛ ሹማምንት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው የሚባልላቸው ኢንሆፍ በቅርቡ ይህንንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ነበር። በዚህ የየካቲት ወር 2009ዓም ጉብኝት ሴናተሩ ከኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተነጋገሩ ተብሎ ቢዘገብም ለህወሓት መሪዎች ግን የHR128 ጉዳይ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘ እንደነበር የጎልጉል መረጃ አቀባዮች ያስረዳሉ።
በHR128 ላይ ፀሐይ እየጠለቀችበት ባለበት በአሁኑ ጊዜ ምን መደረግ አለበት የሚለው አንገብጋቢና ወቅታዊ ጥያቄ ነው የሚሉት የመረጃ ምንጮች ኢትዮጵያውያን የሚተባበሩበት ጊዜ ካለ አሁን ወሳኝና ብቸኛው ጊዜ ነው ይላሉ። “ረቂቅ ሕጉ ለኦሮሞ፣ ለአማራ፣ ለጋምቤላ፣ ለሶማሊ፣ … በህወሓት ጭቆና ሥር ለሚገኙ ሁሉ የሚጠቅምና በህወሓት ላይ ብርቱ በትር የሚያሳርፍ መሆኑን በመረዳት ሁሉም በአንድነት መነሳት አለበት” በማለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ። በሴናተር ኢንሆፍ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ከተቻለ ረቂቅ ሕጉ በሕዝብ እንደራሴዎችም ሆነ በሕግ መወሰኛ ም/ቤት አብላጫ ድምጽ እንደሚያልፍ በእርግጠኝነት የሚናገሩ ወገኖች እንደሚሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሕጉን ወዲያውኑ ለመፈረም እንደሚችሉ አክለው ያስረዳሉ። እንዲያውም አንድ ጊዜ ይህ ሕግ በድምጽ ብልጫ ቢያልፍ ትራምፕ የህወሓትን አገዛዝ እንደ ሰሜን ኮሪያ “ለማስተናገድ” ወደኋላ አይሉም በማለት በድፍረት ይናገራሉ።
ስለዚህ በኦክላሆማ ጠቅላይ ግዛት የሚገኙም ሆነ በተለያዩ የአሜሪካ ክፍሎች የሚኖሩ የህወሓትን ግፈኛ አገዛዝ የሚቃወሙ ሁሉ በሴናተር ኢንሆፍ ላይ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በኢሜይል፣ በስልክ፣ በፋክስ፣ በደብዳቤ፣ ወዘተ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማሳሰቢያው ቀርቧል። ኦክላሆማ በሚገኘው የሴናተሩ ቢሮም ሆነ በቱልሳ ኦክላሆማ የሚገኘው የሴናተሩ ቤተክርስቲያን ስልክ በመደወልም ሆነ ህወሓት በኢትዮጵያ እየፈጸመ ያለውን ግፍ የሚያስረዱ መልዕክቶችን (ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች) በመላክ ሴናተሩ ይህንን ከመሰለው አምባገነን አገዛዝ ጋር ያላቸው ግንኙነትና የሚሰጡት ድጋፍ ፍጹም ከእምነቱም ሆነ ከሰብዓዊ መብቶች አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው ማሳወቅ የእያንዳንዱ ድርሻ ነው በማለት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ በአጽዕኖት ያስረዳሉ።
በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የማሟያ ምርጫ እንሳተፋለን የሚሉ ኢህአዴግ በተቃዋሚ ስም የፈጠራቸው ቤተሰብ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች በዚህ ምርጫ ላይ መወዳደር ለህወሓት/ኢህአዴግ አራጅነት ቢላ የማቀበል ያህል እኩል የሚያስጠይቃቸው መሆኑ በአስተያየት ሰጪዎች ይነገራል።
በመጨረሻም ሁላችንም አንድ የጋራ ጠላት እንዳለን በማመን የተባበረ ክንዳችንን በህወሓት ላይ በማሳረፍ ይህ በህወሓት አንገት ላይ ማነቆ ለማድረግ የተመቻቸ አጋጣሚ ልንጠቀምበት ይገባናል፤ ካልሆነ ግን ይህ ከአስራ አራት ዓመት በኋላ የተፈጠረ ዕድል ይከሽፋል፤ ብዙ ተስፋ የተጣለበት HR128 ፀሐይ ይጠልቅበታል፤ ህወሃትም አፈር ልሶ ይነሳል በማለት ሥጋታቸውን በግልጽ አሰምተዋል።

No comments:

Post a Comment