ክንፉ አሰፋ
ከሰሜን እና ከበስተ-ምስራቅ አቅጣጫ እየነፈሰ ያለው አውሎንፋስ መርከብዋን እያናጋት ይገኛል። ጫፍ ላይ ጉብ ያሉትን አስተናጋጆች እያንጠባጠበ የሚገፋው ሃይል እየበረታ መጥቶ፣ አሁን ከካፒቴኑ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ይመስላል። ይህ ሁላችንንም የሚያስማማን መራራ ሃቅ ነው። ችግሩ እዚህ ላይ አይደለም። ግን… እየሰመጠ ካለው ከዚህ መርከብ ለማምለጥ የተገኘችውን ቀዳዳ እየተጠቀሙ የሚሾልኩትን ሁሉ “ጀግና” ብለን ለመጥራት እንደምን ይዳዳን?
ራስን ማዳን እና ሃገርን ማዳን፤ በሰማይና በምድር መሃከል ያለ ርቀትን ያህል የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
ዘንግተነው ከሆነ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ስራዓት “በስብሷል” ብሎ ከተናገረ 10 አመታት አልፈውታል። ከ 26 ዓመታት በኋላ ደግሞ እነሆ ህወሃት ከርፍቶ መርገፍ ጀመረ። ችግሮቹ ግን እጅግ እየተባባሱ እንጂ እየተሻሻሉ አልመጡም። ይህ ስርዓት ዛሬ እንደ ውሃ እና መብራት ያሉ መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጅ ፍላጎቶችን እንኳን ማሟላት ተስኖታል። “በመለስ ግዜ በፈረቃ፣ ደብረጽዮን ግዜ በደቂቃ” እያለ ከተሜው የስርዓቱን ቁልቁል እድገት የሚነግረን ያለ ምክንያት አይደለም።
ታዲያ በዚህ ሁሉ ረጅም ጉዞ አብረው ዘልቀው፣ አብረው በልተው፣ አብረው ጠጥተው፣ አብረው ዶልተው፣ አብረው ፈስተው፣ አብረው ሰርቀው፣ አብረው ዋኝተው፣ አብረው ቀልተው፣ አብረው አርደው፣ አብረው ቀብረው … አሁን ከድተናል ሲሉ በእርግጥ “ሃገርና ሕዝብን አስበው ነው? ወይንስ ራስን ለማዳን?” ብለን መጠየቅ ግድ ይለናል። ሃገርና ሕዝብ ለ26 ዓመታት እንደ አህያ ሲረገጡ እነዚህ ሰዎች መርከብዋ ውስጥ አብረው ነበሩ። እጃቸውን ሳይጠመዘዙ ከተዳሩበት የህወሃት የጋብቻ ትስስር በኋላ “ሰዎቹ አሜሪካ አገር ሲገቡ ውሉን ለምን አፈረሱት?” ብሎ የሚጠይቅ ብዙ አይታይም።
እናም የብርጋዴር ጀነራል መላኩ እና የአቶ ሃይለማርያም ፕሮቶኮል መኮብለል፣ “ሰበር ዜና” ብለን የምንጠራው ነገር ሊሆን አይችልም። የሰዓቱ መፍረድ እንጂ፣ የነዚህ ሰዎች ሽሽት ፈጽሞ አይጠቅምም ማለትም አይቻልም። ቢያንስ የፖለቲካ ትኩሳቱን የግለት መጠን ይነግረናል። ሰበር የምንለው ግን ጀነራል ሳሞራ የኑስ ወይንም አይቴ ደብረጽዮን ቢኮበልሉ ነበር።
ወትሮም ቤት የእግዚአብሄር፤ ቪላ ሁሉ የገብረ-እግዚአብሄር እየተባለ የሚተረትበት ሃገር፣ ባህር ማዶ ዘልቆ መጠለያ መፈለግ እንግዳ ነገር አይሆንም። ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆኑ አገልጋዮች ሁሉ እንደ ብጻይ ደሳለኝ ከባዱን የሸክም ስራ ሰርተው ሲያበቁ፤ ደከሙ እንጂ ከዱ አይባልምም። የእነዚህን ቦታ በሌሎች ተሸካሚዎች ለመሸፈን፤ የ”ጥልቅ ተሃድሶ መተካካት” እንኳ የሚያሻ አይመስለኝም። እንደሰው ሳይሆን እንደ እንሰሳ ስለሚያዩዋቸው በመሄዳቸው ቅንጣት ያህል አይበርዳቸውም፣ ቅንጣት ያህልም አይሞቃቸውም።
እኛ ግን ሳምንቱን በሁለት ሰበሮች እያሟሟቅን አሳልፈን፤ በሳምንቱ መዝጊያ ላይ ደግሞ የአባዱላ “ሰበር” ዜና ማህበራዊውን ድረ-ገጽ አጨናነቅነው። በጉዳዩ ላይ ጽዮን ግርማ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ያቀረበችውን ዜና ልብ ብሎ ላዳመጠ፤ እዚያ ሰፈር አንድ የሚሸት ነገር እንዳለ ይገነዘባል። ከሽፈራው ሽጉጤ መርበትበት እስከ ስልክ ዘግቶ መሸሽ፣ በአንዱ አቅጣጫ የሚሰማው ነገር፣ ከሌላው ጋር መጣረዝ፣ ከስብሰባው ጋጋታ እስከሽምግልና መሯሯጥ፣… ሁሉ የሙቀቱ መጠን መለክያዎች ናቸው። ህወሃት ለክፉ ግዜ ብሎ ያስቀመጣት የሶማልያ ጥይትም የከሸፈችበት ይመስላል። አሁን ለርዓቱ እድሜ ማራዘምያ የቀረ ነገር የለም። ሁሉም ካርዶች ተመዝዘዋል። ይህ የመጨረሻው ካርድ ግን በክሽፈት ብቻ አላበቃም፤ ይልቁንም በራሱ በስርዓቱ ላይ መዘዝ ይዞ የመጣ ነው የሚመስለው። አባዱላን ሳይቀር አዳልጦ ያስተነፈሰ መዘዝ።
አባዱላ ገመዳ ለአሜሪካ ድምጽ ራድዮ የዘጋውን በር ለዛሚዋ ሚሚ ስብሃቱ መክፈቱ በራሱ የሚጠቁመን ነገር አለ። ትላንት ክቡር፣ ዶክተር፣ ጀነራል አባ ዱላ ተብሎ ሲጠራ በነበረበት ራዲዮ ዛሬ እንደ ገላባ መቅለልን ይመርጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። አያሌ ከጠረጴዛ ስር የሚደረጉ ስምምነቶችን ላስተዋለ ሰው ግን “እባብን ያየ ልጥ ይፈራል” ማለቱ አይቀርም።
እዚህ ላይ ይሰመርበት። አባዱላ ከስፍራው ለቀቀም፤ አልለቀቀም በህወሃት የፖለቲካ አሰላለፍ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። የተባለውን ደብዳቤ እርግጥም አባዱላ ከሆነ የጻፈው፣ የህወሃት መልስ የሚሆነው፣ “ድሮም አልነበርክም፤ አሁንም የለህም!” ነው። አባዱላ የስርዓቱ ጭምብል እንጂ ምሰሶ እንዳይደለ ቄሮም ቢሆን ያውቃል። ይልቁንም ይህ የስንብት ማስታወሻ፣ ኦነግ “ከሽግግሩ መንግስት ራሴን አግልያለው” ሲል ያወጣውን መግለጫ ያስታውሰናል። 20 ሺህ የኦነግ ሰራዊት፣ በጦር ካምፕ ውስጥ እንዲታጎር ካደረጉ በኋላ ነበር እነ ሌንጮ ለታ መግለጫውን የሰጡት። ህወሃቶች በክስተቱ ፈጽሞ አልተደናገጡም ነበር። ራስን በራስ የመግደል ያህል ለፈጸሙት ለዚያ ጅላጅል ውሳኔያቸው፣ አገዛዙን ጮቤ አስረገጠው እንጂ አላበሳጨውም። በቦሌ በኩል እንዲሸኙ ተደረገ እንጂ ፤ በፈቃዳቸው አቅመቢስ በሆኑት በእነ ሌንጮ ላይ እጃቸውን አላነሱም ነበር።
ቄሮ ግን የቅርቡ እልቂት እንኳን ረስቶት፣ የአባዱላን ጀብድ ማውራት ጀመረ። የአባዱላ ከህወሃት መፋታት እኮ ብርቅ ነገር አይደለም። ከዚህ ቀደም ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ታፋትተዋል፣ ጀነራል ባጫ ደበሌም ገለል ተደርገዋል፣ ሃሰን አሊ ተሰድዷል፣ አልማዝ መኮ እና ጁነዲን ሳዶም ወደ አውሮፓና አሜሪካ አምልጠዋል። አንዱ ሲሄድ ሌላው ሲተካ እነሆ ኦህዴድዳቸው ሳይሸረፍና ሳይቀነስ ቀጥሏል። ምክንያቱም ኦህዴድን ጠፍጥፎ የፈጠረው ህወሃት መሆኑን ሁሉም በሚገባ ያውቀዋል። ኦህዴድን የሚያኖረውም፣ የሚያቆየውም ሆነ የሚያጠፋው፣ አባዱላ ሳይሆን ህወሃት ነው።
የመልቀቅያ ደብዳቤ የማስገባቱ ትርክት በህወሃት ቀጭን ትእዛዝ ነው የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቡት ምልከታም ሆነ መላ ምት ውሃ የሚቋጥረውም ከዚህ የተነሳ ነው። በአውሬ ጥርስ ውስጥ ሆኖ አውሬውን መተናኮስ የሚሻ ካለ፤ ይህ ጅል ብቻ ነው። አባዱላ ደግሞ እጆቹም ሆኑ እግሮቹ መስና ውስጥ የተዘፈቁበት ሰው ነው። ወያኔ ይህንን ሰው ሸቤ ለማስገባት አንድ ሚሊዮን ፋይሎችን መምዘዝ እንደሚችል ይታወቃል። “አፍ ስላበዛህ በገዛ ፍቃድህ ልቀቅ!” መባሉ አዲስ ነገር አይሆንም። ቀይ መስመር ሊያልፍ ይችላል ተብለው ለሚጠረጠሩ “ሹሞች” አስቀድሞ የተዘጋጁ የወንጀል ፋይሎች አሉ።
የአባዱላ መልቀቅያ ደብዳቤ ግማሽ እውነት ነው። ግማሽ እውነት ማለት ደግሞ ሙሉ ውሸት ነው። የሚደንቀው ይህ ሳይሆን የዲያስፖራው ጭብጨባ ነው። ልክ እንደ ቤተሰብ ጨዋታ፤ ጥያቄያቸውን በትክክል ሲመልሱ ይጨበጨባል፣ ሲሳሳቱም ይጨበጨባል። አባዱላ የቀድሞ ሰራዊት ምርኮኛ መሆኑን ለአፍታ እንኳን ብናስታውስ፣ ከዚህ የተሳሳተ ግምታችን እንታረም ይሆናል።
ዝቅ ብለው እንዲበሩ ተነግሯቸው የነበሩ “ባለስልጣናት” ጉዳይ እንግዳ ነገር አይደለም። እነዚህን ሰዎች አስቀድመው ስኳር የሚያልሱዋቸው ፣ ከህወሃት ራዳር እንዳይወጡ ለማድረግ ብቻ ነው። ከፍ ብለው ለመብረር ከሞከሩ ውርድ ከራስ ይሆንና ቀሪው አማራጭ እጅ መስጠት ይሆናል።
No comments:
Post a Comment