Translate

Monday, October 16, 2017

በረከት ስሞዖን መልቀቂያ ማስገባታቸው ተነገረ

ትናንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነታቸው መባረራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገበ ማግስት የብአዴን/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ከድርጅታቸውና ከሥራቸው የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው እየተነገረ ነው::
የጠቅላይ ሚኒስተሩ አማካሪ ሆነው እየሰሩ የሰነበቱት አቶ በረከት ስምዖን መልቀቂያ ያስገቡበት ምክንያት እስካሁን አልተገለጸም:: ሆኖም ግን በዚህ መረጃ ዙሪያ የተለያዩ አክቲቭስቶች አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ይገኛሉ::


በተለያዩ ሚድያዎች ላይ በመቅረብ በወቅታዊ የሃገራችን ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት ዶ/ር ሰማኸኝ ጋሹ “በረከት ሰምኦን ከፖሊሲ ጥናት አስተባባሪነቱና የጠቅላይ ሚንስትር አማካሪነቱ የመልቀቁ ነገር እውነት ከሆነ ከአባ ዱላ ስልጣን መልቀቅ በላይ ትልቅ ትርጉም አለው። የ1997 ምርጫ በደም እንዲበከል ያደረገው፥ መለስ ከሞተ በሁዋላ የድርጅቱ የርእዮት አለም ጉዳይ ዋና መሀንዲስ ፥ ግትሩና ስልጣኑን ለመተው የመጨረሻው ሰው ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው በረከት መልቀቅ በርግጥም የለውጥ መባቻ ላይ ለመሆናችን ትልቅ ምልክት ነው። በረከት ያክል ችኮ ሰው ተስፋ የቆረጠበት ስርአት አይበረክትም።” ብለዋል::
በሌላ በኩልም ቬሮኒካ መላኩ የተሰኙ ጸሐፊ “ምን እየተካሄደ ነው? ኢህአድግ ህመሙን መደበቅ አልቻለም ። በሁለት ቀን ውስጥ ብቻ በረከት ስምኦን ከጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪነቱ ፣ ከፖሊሲ ጥናት እና ምርምር አስተባባሪ ሀላፊነቱ እና ከንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነቱ ስልጣኑን ለቋል ። ቀጣዩ ርምጃ ምን ሊሆን ይችላል ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ የህውሃት ጀነራሎች መፈንቅለ መንግስት ሊያደርጉ ይችላሉ። አገሪቱ ከሲቪል አስተዳደር ወደ ወታደራዊ አገዛዝ እያኮበኮበች ይመስላል።” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:: የሕወሓት ጀነራሎች መፈንቅለ መንግስት ሊያደርጉ ይችላሉ የሚለውን ሲያብራሩም “ቅድም የህውሃት ጀኔራሎች መፈንቅለ መንግስት ሊያደርጉ ይችላሉ ” ብዬ ስፅፍ ብዙ ሰው ” አሁንስ የሚገዙት ራሳቸው አይደሉም ወይ? እንደት ራሳቸውን በራሳቸው ይፈነቅላሉ? ” የሚል ጥያቄ ቀርቧል። ይሄን ጉዳይ በ2 ወይም 3 መስመር አጠር አድርጌ ላብራራው። ህውሃት ከዚህ በኋላ አሁን ባለው የኢህአድግ መዋቅር እንደ ባለፉት 24 አመታት በፍፁም የበላይነት የማስተዳደር ፓወሩ ተንጠፍጥፎ አልቋል ። መከላከያውና ደህንነቱ መቶ በመቶ በህውሃት ቁጥጥር ስር ሆኖ እንኳን ክልሎች እየተገዳደሯቸው ነው። መከላከያን የክልል ልዩ ሀይሎች ከጨዋታ ውጭ እያደረጉት ነው። ደህንነቱንም የክልል የፀጥታ ሀይሎች እየቀደሙት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በህውሃት በራሱ ውስጥም ክፍፍል አለ ። ከዚህ በኋላ ውጤቱ ለህውሃት ጎጅም ሆነ ጠቃሚ ያላቸው አማራጭ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ የነበረውን መዋቅር ካፈራረሱ በኋላ እንደገና የበላይነታቸውን በሚያስጠብቅ ሁኔታ ሀ ብሎ መጀመር ነው። ” ይሄ ሊሳካ ይችላል ወይ ? ” እሱ ደሞ ሌላ ትንታኔ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው።” ብለዋል::
ዶ/ር ገሰሰ የኔዓየሁ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ምንም አዲስ ነገር የለም:: በመተካካት መርሆ ትላንት እነ አዲሱ ለገሰ እና ስዮም መስፉን ለአዲሱ አመራር አስረከብን ብለው በጀርባ እንደተቀመጡ ሁሉ አሁን የህወዓት ታድሶ ውጤት የሆነውን ድራማ ነው እያየን የቀጠልነው። አባ ዱላ፣በረከት ስምዖን እና ሌሎችንም እንሰማለን። የሚጠረዘው ተጠርዞ የህወዓት አገዛዝ ይቀጥላል። ህወዓትን በአፈ ሙዝ አልያም ከዳር እስከዳር የተነሳ የህዝብ ማእበል ብቻ ነው ሊነቀንቀው የሚችለው። ከዚያ ውጭ ያው የለመድነውን ልስ እየቀመስን አገታችንን መድፋታችን ይቀጥላል። እከሌ በዚህ በኩል ሾለከ፣አባ ዱላ እንዲህ አለ እያልን የምናጣብበትን የአየር ሰዓት በርካታ ቁምነገሮችን መስራት ይጠበቅብን ነበር። እነሱ የቤት ስራ ይሰጡናል እኛ በእነሱ ኢሹ እንተራመሳለን። በቃ መውጫ ቀዳዳው ሮኬት ሳይንስ አይደለም ግልፅ ነው። ኦሮሞ ኬኛ ምናምን ቅብጥሬስ አሽቀንጥሮ ጥሎ ጥያቄን የፉትህ እና የእኩልነት ጥያቄ አድርጎ ከመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ በአንድ ድምፅ ለአንድ ለአላማ መቆም ሲቻል ብቻ ነው። አለበለዚያ እንደለመድነው ሺወች ወጣቶችን እያስበላን፣ዘግናኝ ግድያወችን እየተመለከትን እንቀጥላለን።” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::

No comments:

Post a Comment