*ዶ/ር ነጋሶ ለአትሌት ኃይሌ ሃሳብ አቀረቡ -“ አንድነት ፓርቲ ይሻልሃል!”
ፖለቲካዊ ወጋችንን የምንጀምረው ሰሞኑን የተፈጠረች አንድ “ህዝባዊ ቀልድ” በመጋራት ነው፡፡ ምን ሆነ መሰላችሁ? ባለፈው ሳምንት የኦሮምያ ክልል ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ሃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው መያዛቸውን ተከትሎ በአካባቢው ውሃ ጠፍቶ ነበር አሉ፡፡ ህዝቡ ምንም ምርጫ ሲያጣ ነገሩን ለበላይ ሃላፊዎች ለማመልከት ተገደደ (ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል አሉ!) የተሰጠው ምላሽ ግን ከእስከዛሬው ለየት ያለ ነው፡፡ “ውሃ የጠፋው በኤግዚቢትነት ተይዞ ነው” ተባለ፡፡ ይሄን እንደሰማው ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቃላችሁ? በሙስና ተጠርጥረው የተያዙት ዘጠኙ የኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ሃላፊዎችና ሲጠፋብን የነበረው መብራት! ከዚያማ የሞኝ ነገር በዚያው ቀጠልኩ፡፡ የዚያን ሰሞን የተከሰተውን የወርቅ መወደድና የዶላር መጥፋት ከታሰሩ የባንክ ሃላፊዎች ጋር አገናኝቼው ቁጭ አልኩ፡፡ (እቺን እቺንማ ማን ብሎኝ!) ከ97 ምርጫ ቀውስ ጋር ተያይዞ የቅንጅት አመራሮች ከታሰሩ በኋላ የፖለቲካ ድርቀት ተከስቶ እንደነበረ ትዝ አይላችሁም ? እኛ ግን በጣም ትዝ ይለናል (በእንጀራችም መጥቶብን ነበራ!) እንዴ ጋዜጣ የሚገዛ እኮ አልነበረም (ፖለቲካ ጠፍቶ ነበራ!) እና ያኔ ፖለቲካው የት ገብቶ ነበር ብዬ አሰብኩ፡፡ ወዲያው መልሱ ብልጭ አለልኝ “ፖሊስ በኤግዚቢትነት ይዞት ነበር!” (ከፖሊስ ማረጋገጫ ባይገኝም) በኋላ ሲፈቱ እኮ በኤግዚቢትነት የተያዘውም ተፈታ፡፡ እኛም እንጀራ መብላት ጀመርን – የአንባቢን የፖለቲካ ጥማት ለማርካት እየሞከርን፡፡ (በኤግዚቢትነት የተያዘው ውሃ አልተለቀቀ ይሆን?)