ክንፉ አሰፋ
ከሰሜን እና ከበስተ-ምስራቅ አቅጣጫ እየነፈሰ ያለው አውሎንፋስ መርከብዋን እያናጋት ይገኛል። ጫፍ ላይ ጉብ ያሉትን አስተናጋጆች እያንጠባጠበ የሚገፋው ሃይል እየበረታ መጥቶ፣ አሁን ከካፒቴኑ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ይመስላል። ይህ ሁላችንንም የሚያስማማን መራራ ሃቅ ነው። ችግሩ እዚህ ላይ አይደለም። ግን… እየሰመጠ ካለው ከዚህ መርከብ ለማምለጥ የተገኘችውን ቀዳዳ እየተጠቀሙ የሚሾልኩትን ሁሉ “ጀግና” ብለን ለመጥራት እንደምን ይዳዳን?
ራስን ማዳን እና ሃገርን ማዳን፤ በሰማይና በምድር መሃከል ያለ ርቀትን ያህል የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
ዘንግተነው ከሆነ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ስራዓት “በስብሷል” ብሎ ከተናገረ 10 አመታት አልፈውታል። ከ 26 ዓመታት በኋላ ደግሞ እነሆ ህወሃት ከርፍቶ መርገፍ ጀመረ። ችግሮቹ ግን እጅግ እየተባባሱ እንጂ እየተሻሻሉ አልመጡም። ይህ ስርዓት ዛሬ እንደ ውሃ እና መብራት ያሉ መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጅ ፍላጎቶችን እንኳን ማሟላት ተስኖታል። “በመለስ ግዜ በፈረቃ፣ ደብረጽዮን ግዜ በደቂቃ” እያለ ከተሜው የስርዓቱን ቁልቁል እድገት የሚነግረን ያለ ምክንያት አይደለም።
ታዲያ በዚህ ሁሉ ረጅም ጉዞ አብረው ዘልቀው፣ አብረው በልተው፣ አብረው ጠጥተው፣ አብረው ዶልተው፣ አብረው ፈስተው፣ አብረው ሰርቀው፣ አብረው ዋኝተው፣ አብረው ቀልተው፣ አብረው አርደው፣ አብረው ቀብረው … አሁን ከድተናል ሲሉ በእርግጥ “ሃገርና ሕዝብን አስበው ነው? ወይንስ ራስን ለማዳን?” ብለን መጠየቅ ግድ ይለናል። ሃገርና ሕዝብ ለ26 ዓመታት እንደ አህያ ሲረገጡ እነዚህ ሰዎች መርከብዋ ውስጥ አብረው ነበሩ። እጃቸውን ሳይጠመዘዙ ከተዳሩበት የህወሃት የጋብቻ ትስስር በኋላ “ሰዎቹ አሜሪካ አገር ሲገቡ ውሉን ለምን አፈረሱት?” ብሎ የሚጠይቅ ብዙ አይታይም።