ሰሞኑን የህወሃት 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በመላው ኢትዮጲያ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ በቅድሚያ እንኳን ለአርባኛው አመት የምስረታ በዓል አደረሳችሁ እላለሁ ፡፡ በትጥቅ ትግሉም ወቅት ሆነ ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ይህን ቀን ለማየት ሳይታደሉ ያለፉ ብዙዎች ናቸውና ምንም ይሁን ምን ለዚህ ቀን መብቃት ትልቅ ነገር እንደሆነ ይሰማኛል ፡፡ ይህን ፅሁፍ የምፅፈው በተወለድኩባት ባደኩባትና አሁንም እየኖርኩባት ባለችው ኢትዮጲያ ከተመሰረተ ድፍን 40 ዓመት ያስቆጠረ ጎልማሳ የፖለቲካ ድርጅት ላይ እንደአንድ ዜጋ ያለኝን ቅሬታ ለማሳወቅ ነው ፡፡
ሰሞኑን የድርጅቱን 40ኛ ዓመት በዓል በቴሌቪዥን በሬዲዮ እንዲሁም ከመሃበራዊ ድረ ገፆች ላይ ስመለከት እንዲሁም አገሪቱ ላይ ያለውን ተጨባጭ ችግር ስታዘብ ሳልፈልገው አእምሮየ ታሪክ እየመዘዘ ይሞግተኛል ፡፡ ባጭሩ ይህ በዓል በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ምን ያህል ነው ብየ ሳስብ ከግራና ቀኝ ከህዝቡ የሚሰነዘረውን ትችት አስተያየትና ምሬት ስመለከት በዓሉን ለብቻችሁ እያከበራችሁት ነው የሚል ስጋት ፈጥሮብኛል ፡፡
ምንም እንኳን የህወሃት የትጥቅ ትግል የዛሬው የህወሃት ቀንደኛ ጠላት ሻእቢያን ጨምሮ በከፈሉት መስዋእትነት ባደረጉት ተጋድሎ አገራችንን ከደርግ አሰቃቂ አገዛዝ የታደጋት መሆኑን ሁሉም ኢትዮጲያዊ ቢያውቅም ከነፃነቱ በኋላ ግን ስርዓቱ በሚከተለው ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስመር ከፍ ያለ ቅሬታ አለው ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ህዝቡ የትም ሂዱ የት ይማረራል … መቸም ይሄ ሁሉ ህዝብ የሚማረረው የኢትዮጲያ ህዝብ ምስጋና የማያውቅ ስለሆነ አይመስለኝም ፡፡ እንደውም ከእግዜር ጀምሮ እስከአምባገነን መሪወቹ ድረስ ራቱን በልቶ ባደረ ቁጥር ከእልፍ ችግሩ ጋር ተጠቅልሎ በሚተኛባት መደብ ‹‹ተመስገን›› ብሎ የሚያድር ህዝብ እንደኢትዮጲያ ህዝብ ያለ አይመስለኝም ፡፡ ግን …… ብሶት ህወሃትን እንደወለደ ሁሉ አሁንም ተማራሪ ህዝብ እየፈለፈለ ምድሩን እየሞላው ነው ፡፡ እናንተም ለህዝብ ብሶትና ጥያቄ ጅራትና ቀንድ እየቀጠላችሁ ተናጋሪውን ሁሉ ባልሆነ መንገድ በመፈረጅ ከማሳቀቃችሁም በላይ የዝሆን ጆሮ ይስጠን እንዳላችሁ ይሄው ድፍን 40 ዓመት ፡፡
በእርግጥ በቴሌቪዥንም ሆነ በአካል ለህዝብ ንግግር ማድረግ ቀላል ነው … ከባዱ ከህዝብ ጋር መነጋገር ነው ፡፡ ይሁንና ንግግር ማድረግም ቢሆን ቀላልነቱ ለሚናገሩባት ቅፅበት እንጅ ሲቆይ ወደሰማይ እንደወረወሩት ድንጋይ ተመልሶ አናት ላይ መስፈሩ አይቀርም ፡፡አሁንም እየሆነ ያለው ይሄው ነው ፡፡ የተገባው ቃል ሁሉ ስንዝር አልተራመደም ፡፡ በርካታ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል መንገድ የጤና እና የትምህርት ተቋማት ግንባታ ግድቦች ዩኒቨርስቲዎች እነዚህ ሁሉ እናተም በተደጋጋሚ እንዲነገርላችሁ የምትፈልጓቸው ስኬቶች ናቸው ፡፡ ይሁንና ህዝብ ያልተሟላለትን ነገር ሲናገር የተሰራለትን እንደካደ አድርጎ ማሰብ ትልቁ የአረዳድ ችግራችሁ ነው ፡፡ ሰው ኑሮ ተወደደብኝ ብሎ ሲያማርር ኑሮ የሚቃለልበት መንገድ ላይ መስራት ብቻ ነው መልሱ ሊሆን የሚችለው ! …‹‹ አይ ኑሮ ቢወደድብህም ዩኒቨርስቲ ግን ሰርተንልሃል›› የሚል ምላሽ መቸም ህዝብን ሊያረካ አይችልም !! አሁን እየሆነ ያለው ግን ይህ ነው ! ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ማስፈራሪያ ዛቻ እንዲሁም የተወሰኑ ሰዎችን ከህዝቡ እየመዘዙ ለብዙሃኑ ችግረኛ እንቆቅልሽ ማለትና የህዝቡን ቅሬታ ማድበስበስ የተለመደ የገዥው ፓርቲ ስራ ሁኗል ፡፡
በተለይም ኢቲቪ (EBC) ‹‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ›› በማለት የሚያቀርባቸው ሰዎች ግራ እያጋቡን ነው ! እስቲ ኑሮ ተወዶብናል ስንል እነዚህ ‹‹አንዳንዶች ›› ኑሮ አልተወደደም የሚል በደፈናው ይዘው ህዝቡን ማበሳጨት ምን ይጠቅማል ?ለማንስ ነው የሚመሰክሩት …መብራት ጠፋብን ስንል አንዳንዶቹ ‹‹ኧረ በጭራሽ›› ይሉናል ፡፡ አንዳንዶች ብዙሃኑን ‹‹ውሸታም ነህ ›› ይሉታል ፡፡ይሄ ህዝብን መናቅ ነው …እንደውም በኑሮ ውድነት ከሚሰቃየው ህዝብ በመሰረተ ልማት አውታሮች እጥረት ፍዳውን ከሚበላው ህዝብ የሚፈጠሩ ህፃናት ወደፊት
‹‹ስታድጉ ምን መሆን ትፈልጋላችሁ›› ሲባሉ
‹‹ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መሆን እንፈልጋለን ›› እንዳይሉ እሰጋለሁ ፡፡ ….በአሁኑ ሰዓት ያለምንም ምሬት በተድላ እንደሚኖሩና ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ እንደሆነ የሚመሰክሩ ኢትዮጲያዊያን ቢኖሩ እነዚሁ ‹‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች›› ብቻ ናቸውና ምኞቱ እንዲህ ቢሆን አይገርምም ፡፡ ብሄራዊ ቴሌቪዥናችን ‹‹ራበን ›› ብሎ ሰልፍ ለወጣው ህዝብ ‹‹ለምን ኬክ አይበሉም ›› እንዳለችው ልእልት ሁኖብናል ፡፡ ስራ አጣን ስንል ቴሌቪዥናችን ለምን ስራ አትፈጥሩም ይለናል …ኑሮ ለማሻሻል ተሰደድን ስንል …አይ ጥጋብ ፈንቅሏችሁ እንጅ አገራችን ማሩ ወተቱ ይለናል …እንኳን ማርና ወተት የግዜሩንም ውሃ በስንት ጉድ ጥበቃ እንደማንዳረስ ሁሉ !
ችግሩ ይሄ ብቻ አይደለም በመልካም አስተዳደር ላይ ተቆጥሮ የማያልቅ ችግር ውስጥ ነን ፡፡ ሙስና ቁጥር አንድ ጠላታችን ሁኗል …ሙስና ደግሞ በባህሪው ስልጣናቸውን ገንዘብ ላለው ሰው የሚያከራዩ ባለስልጣናትና የስራ ሃላፊዎች ዘንድ የሚፈጠር አደገኛ ተግባር ነው ፡፡ መንግስት ህዝቡን ጠቁም አትጠቁም ጨዋታ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ‹‹ደህንነት›› ተብሎ ለአገር ደህንነት ሲባል ጓዳ ጎድጓዳውን እሰልላለሁ እንደሚለው የመንግስት አካል በዚህም ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ‹‹የደህንነት አካል ›› ቢቋቋምና መዘረፋችን ባይቆም እንኳን አሟጠው እንዳይነጥቁን ሃይ ቢባሉ መልካም ነው ፡፡መቸም ሚስኪን ፀሃፊና ጋዜጠኞችን ከማሳደድ ይሄ የተሸለ ስራ ይመስለኛል ፡፡
ሌላው የህወሃት አስጊ ችግር በብሔሮች መሃል የፈጠረውና አሁንም እየፈጠረው ያለው ቁርሾ ነው ፡፡ በተለይ በትግራይ ህዝብና በሌላው ኢትዮጲያዊ መካከል …በተደጋጋሚ ህወሃት በጉድለቶቹ ሲወቀስ የራሱን ችግርና በድርጅቱ ላይ የሚሰነዘረውን ጥላቻም ይሁን ነቀፋ በትግራይ ህዝብ ላይ እንደተሰነዘረ በማስመሰል የትግራይ ህዝብን ከጎኑ ለማሰለፍ የሚያደርገው ጥረት በተደጋጋሚ የሚታይ የአደባባይ ሚስጥር ነው !! ይህ ነገር የትግራይን ህዝብ ከእህትና ወንድሞቹ ጋር እያቃቃረው ከስርአቱ ልዩ ተጠቃሚ የሆነ እያስመሰለው ይገኛል ፡፡ የትግራይ ህዝብ በህወሃት የስልጣን ዘመን ከሌላው የኢትዮጲያ ህዝብ የተለየ ተጠቃሚ ሁኗል አልሆነም የሚለው ጥያቄ አወዛጋቢ እንደሆነ አለ !!
ይህን ያልኩበት ምክንያት ደግሞ ህወሃት እራሱ እንደሚለው ኢፈርት ወይም ትእምት እጅግ በጣም ግዙፍ እና በኢትዮጲያ ውስጥ( አንዳንዶች እንደውም በአፍሪካም ይላሉ) በሀብት የሚወዳደረው የሌለ የንግድ ተቋም ነው ፡፡ ባለቤትነቱ ደግሞ በተለይ እንደተቀመጠው የትግራይ ህዝብ ነው ! እንግዲህ ይህን የሚያክል ትልቅ ተቋም በስሩ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ፋብሪካዎች የማእድን ማውጫወች የኮንስትራክሽን ተቋማት የትራንስፖርት ድርጅቶች የእርሻ ድርጅቶች ያሉት ባለፀጋ ድርጅት ባለቤቱ የትግራይ ህዝብ ነው ከተባለና በትክክል ለትግራይ ህዝብ ገንዘቡ ከዋለ የትግራይ ህዝብ በደንብ ተጠቃሚ ነው ለማለት ያስደፍራል !! ይሁንና እዚሁ ፌስቡክ ላይ የኢፈርት ነገር ላም አለኝ በሰማይ ነው እንደሚሉን በርካታ የትግይ ወንድሞቻችን አባባል ከሆነ ግን የትግራይ ህዝብ በተለይ ከስልጣኑም ከበረከቱም የሌለበት ሚስኪን ነዋሪ ያው እንደሁሉም ኢትዮጲያዊ ነው !!
ዋናው ነገር ተጠቀሙም አልተጠቀሙም አሁን ባለው በርካታ ኢትዮጲያዊ አመለካከት በተለያየ መንገድ እንደምንሰማውም ህወሃትና የትግራይን ህዝብ አዳብሎ የማየት ነገር ጎልቶ ይታያል ፡፡ ህወሃትም ቢሆን የትግራይ ህዝብና ህወሃት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው አይነት ዳርዳርታ ማብዛቱ በቀሪው የኢትዮጲያ ህዝብ ልብ ውስጥ ጥሩ ነገር ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም ! ህወሃት የፖለቲካ ድርጅት ነው ሊጠላም ሊወደስም ይችላል፡፡ እራሱን ችሎ መቆምና ከህዝብ የሚሰነዘርበትን ጥላቻም ሙገሳም ህዝቦችን ሳያነካካ መቀበል ይኖርበታል ፡፡ መልካም አስተዳደር ያሰፈነ ገዥ ፓርቲ የዚህኛው ብሔር የዛንኛው ዘር ነው አይባልም ጥሩ ድርጅት የሚያስተዳድረው ሃገር ድርጅት ነው !! አምባገነን እና ፀረ ህዝብ መንግስት ግን ከማንም ይጠጋ በማንም ይጠለል ህዝባዊ አይደለምና ብሔር የለውም !! አዎ የመላውን የሰው ልጆች ነፃነት ሰበዓዊና ዲሞክራሲ መብት ገፋፊ ከሆነ አምባገነን ብሄር የለውም!!
ይሄ ህወሃትን የነካ የትግራይን ህዝብ ነካ ጨዋታ በ1993 እና 1997 ላይ በተለይ በአዲስ አበባ የተከሰቱትን ተቃውሞች ላይ ነህዝቦች መካከለል አስነስቶ የነበረውን ተገቢ ያልሆነ መዘዝ በማየት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መታዘብ ይቻላል ፡፡ ያ ጊዜ የዚህ የጥላቻ ዘር ውጤት ፈጦ የታየበት ነበር ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂው ህወሃት ነው !! ለምን ቢባል በህዝቦቹ መካከል ወንድማማችነትን ለማጎልበት በቂ ስራ አልሰራም … (ፍላጎቱም ያለው አይመስልም) በመንግስት ስራ ውስጥም ሆነ በሌሎች ስራዎች የተሰማሩ አንዳንድ የአካባቢው ተወላጆች የትጥቅ ትግሉን ታሪክ የግል ጀብዷቸው ብቻ አድርገው ሲደነፉና ስለታገሉ ብቻ ልዩ ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳላቸው በተለያየ መንገድ ሲጠቅሱ መንግስት መስመር ለማስያዝ ያደረገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም !!
አንዳንዴ እኮ ተራ መጠጥ ቤት ውስጥ ሳይቀር በሚነሳ አምባጓሮ ‹‹ደሜን አፍስሸ ባቀናኋት አገር ›› የሚላችሁ እንጩጭ ብሔረተኛ ያጋጥማችኋል ፡፡ እዚህ ፌስቡክ ላይ በፀያፍ ስድብ ታሪክና ታላላቅ ሰዎችን በማጠልሸት ከእኛ በላይ አዋቂ የለም በማለትና አሳዛኝ ድርጊቶችን በመፈፀም የሚታወቁትም ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው !! ይህ ከተጋነነ እውቀት ላይ ሳይሆን ትእቢት ላይ ከተመረኮዘ መጥፎ በራስ መተማመን የሚፈጠር በሽታ ከእኔ በላይ ላሳር የሚያስብላቸው እነዚሁ ሰዎች ናቸው !!
ለዚች አገር መሳሪያ አንስቶ የተዋጋው ብቻ ሳይሆን ግንበኛውም ሃኪሙም አስተማሪውም ላቡን አፍስሶላታል !! አበቃ !! ማንም ስለታገለ ደሙን ስላፈሰሰ ለህዝብ ነፃነት በጎ ነገር እንዳደረገ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንደተወጣ ያስብ እንጅ ለፈሰሰ ደሙ ከኢትዮጲያ ህዝብ ካሳ የመጠየቅ መብት እንዳለው ወይም ልዩ ተጠቃሚ የሚደርገው የይለፍ ወረቀት እንደያዘ አድርጎ ማሰብ ነውርም አሳፋሪ አስተሳሰብም ነው !! ሚሊየኖች እየወደቁላት እዚህ የደረሰች አገር ለሟችም ለገዳይም ነፃነትን እንጅ ካሳን የከፈለችበት ዘመን የለም ! ደሜ ለፈሰሰበት ይከፈለኝ የሚል እሳቤ ያለው ዜጋ ቅጥረኛ ወታደር እንጅ በምንም መስፈርት ጀግና ሊባልና ሊሞካሽ አይገባም !! የመስዋእትነት ክፍያው ነፃነት ብቻ ነው !! ነፃነቱም ለሁሉም ህዝብ በእኩልነት !!
መንግስት ለምን የፃፉትን ሁሉ ያስራል .. ለምን በተናገሩት ቁጥር ያኮርፋል … ዜጎቹን አኩርፎ ከውጭ አገር ሽማግሌ እስኪመጣለት አለያም አስሮ የሚያሰቃያቸው ዜጎቹ ያውም በካርዳቸው ድምፃቸውን ሰጡኝ የሚላቸው …ይቅር በለን ብለው እግሩ ስር እስኪወድቁለት የሚጠብቅ ስርዓት ምን አይነት መንግስት ሊወጣው ይችላል …ሁልጊዜ ስለመንገድ አውሩ ሁልጊዜ ስለፋሲካ ብቻ አውሩ የሚል መንግስት እንዴት የህዝብ መንግስት ሊሆን ይችላል ! መፅሄት ላይ ኮሽ ሲል በህዝብ ላብ በህዝብ ግብር በተማሩ ወታደሮችና ደህንነቶች ዜጎቹን የሚያሳፍስ ዘመድ ወዳጅ እንዳይጎበኛቸው የሚከለክል መንግስት ማንን ነው የሚመራው ….
በዚች በአርባኛ አመት በዓል ላይ የሚታየው ሌላው አሳዛኝ ነገር ደግሞ የትግራይን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጲያ ህዝብ በላይ ጀግና አድርጎ የማቅረቡ ነገር ነው …እውነታውን ማስቀመጥ ይኖርብናል … ደርግን ለመጣል የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጲያዊያን ወገኖቹ በላይ መስዋእትነት ከፍሏል ይሄ የማይካድ ሃቅ ነው …. ይህ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ከሰማየ ሰማያት የተለየ ጀግንነት ስለተቸረው ሳይሆን የትጥቅ ትግሉ በወቅቱ ለሁሉም ኢትዮጲያዊ በሚመች መልኩ ስላልተደራጀ ነበር ፡፡ እንጅኮ ደርግ ሲወድቅ ከአስራ ስምንት በላይ ብረት ያነሱ ተፋላሚዎች በኢትዮጲያ ነበሩ ! ቀደም ብለን ካየነውም በርካታ ኢትዮጲያዊ ደርግ አፍንጫ ስር ቁሞ በመፋለም ለህወሃት ትጥቅ ትግል መንገድ ከፍቷል …ተማሪዎች ለነፃነት ደማቸውን አፍስሰውላታል … ግለሰቦች ጨካኙን ስርአት ፊት ለፊት ተቃውመው ተሰውተዋል ….
… ደግሞ በህወሃት የትጥቅ ትግል ውስጥ ‹‹አምስት ሁነው ትግሉን ጀመሩ›› የሚለው የታሪክ መነሻ አምስት ሁነው ትግሉን ጨረሱ ማለት አለመሆኑን ማወቅም ተገቢ ይመስለኛል !! ሁሉም ኢትዮጲያ አንጀቱ አሮ በየቤቱ በተቀመጠበት ሰአት እንኳን አምስት አንድ ሰውም ተከተሉኝ ቢል እልፍ ያኮበኮቡ ኢትዮጲያዊያን ስርዓቱን ለመፋለም ዝግጁ ነበሩ …. ነበሩ ብቻ ሳይሆን ከህወሃት በፊት ብረት አንስተው ስርዓቱን እንቢ ያሌ ነበሩ ፡፡ ምሬት ፅዋዋ ሞልቶ ነበር ህዝብ አገዛዙን አክ እትፍ ብሎት ነበር … ህወሃት አሁን ቁጭ ብሎ ማሰብ ያለበት የሚመስለኝ አምስት ሁኖ የትጥቅ ትግሉን መጀመሩን ሳይሆን አሁን የኢትዮጲያ ህዝብ ባጠቃላይ አምስት የሚወዳቸው የሚምናቸው መሪዎች ህወሃት ውስጥ አሉ ወይ የሚለውን ነው !!
በነገራችን ላይ ህወሃት ባለፈበት ጎዳና ሁኑ መላው የኢትዮጲያ ህዝብ ከጎኑ ነበር !! የትግራይ ህዝብ ብቻው ከኢትዮጲያ ህዝብ የተለየ ጀግና ሊሆን አይችልም!! …ከወንድሞቹና ከእህቶቹ በላይ ጀብዱ እንዳለውም ማሰብ አይኖርበትም !! ይሄ እጅግ የተጋነነና የተዛነፈ እሳቤ ነው በኋላ ያልሆኑትን አድርጎ የማይገፉት ተራራ ጋር የሚያጋጨው …ሩቅ ሳንሄድ ሻእቢያ ከእኔ በላይ ጦርነት አዋቂ ከኔ በላይ ተኳሽ ላሳር ብሎ በእብሪት ከወረረን እኮ ገና አስራ አምስት አመት አልሞላውም … ይሁንና የቱንም ያህል ራሱን ጀግና ያድርግ የቱንም ያህል ራሱን ብልህና ጥበበኛ አድርጎ ያስብ ከመላው ኢትዮጲያ እንደአሸዋ የተዘረገፈው ህዝብ ነበር የከፈለውን ያህል መስዋእትነት ከፍሎ አገርን የታደጋት !! እውነቱን እናውራ ከተባለ የሻእቢያን ወረራ የትግራይ ህዝብ ብቻውን ይቋቋመው ነበር ?
መንግስት በቀረው እድሜ ሁሉ በብሔሮች መሃል በሃይማኖቶች መሃል እንዲሁም በፖለቲካ ድርጅቶች መሃል ታየም አልታየም ታወቀበትም አልታወቀበትም ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት ባይኖረው መልካም ነው ፡፡ የፈለገ ቢከፋፈል ቢለያይ ገዥውን የጋራ ጥላት ያደረገ ህዝብ በአንድ ላይ መቆሙና መልሶ ችግር መሆኑ አይቀርም ! ዛሬ 40ኛ አመት በዓሉ ሲከበርም ይሄንኑ ታሳቢ ማድረጉ የሚበጅ ይመስለኛል !
ጉዳየን ስቋጭ እራሱ የህወሃት 40ኛ ዓመት ምስረታ በዓል አከባበር ላይም ታሪካዊ ጥያቄ በማንሳት ነው …
1965 ዓ/ም የወሎ ህዝብ በእረሃብ ሲረግፍ ከታች ጀምሮ እስከላይ እስከንጉሱ ርሃቡን በመደበቅና በማድበስበስ ስለረሃቡ የተነፈሱትን ሁሉ በማሰር ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ የ80ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ለማክበር አዲስ አበባን በከፍተኛ ወጭ እያሽቆጠቆጧት ነበር ..የዜና አውታሮችም አገር ጥጋብ እንደሆነ ምርትም እንደተትረፈረፈ እየዘገቡ ነበር (እንዳሁኑ EBC) በዓሉም ሃምሌ 1965 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ ተከበረ … ይሄንና ይሄ የታፈነ ግፍና ሌላም የህዝብ በደል ተዳምሮ ንጉሱን በብርሃን ፍጥነት ከነዙፋናቸው አንኮታኮተ ኢትዮጲያንም ለሰሚው ወደሚዘገንን ወታደረዋ አገዛዝና ደም መፋሰስ ዳረጋት !!
ደርግ …በተመሳሳይ በርካታ ኢትዮጲያዊያን በተራቡበትና በእርሃብ በሚረግፉበት ወቅት የፓርቲ ምስረታ ገለመሌ በዓሉን መላዋን አዲስ አበባ በመብራትና በመፎክር አንዎጥቁጦ ሲያከብር ነበር ! ደርግም በተመሳሳይ ‹‹ጠላቶቸ …ሻእቢያ ገንይ ምናምን ከማለት ውጭ ስለውስጥ ችግሩ ትንፍሽ ሳይል ፌሽታውን አከበረ ….ዛሬስ ምን እያደረግን ነው … የእውነት ህዝባችን ፌሽታችንን ህዝባችን በዓላችንን የሚጋራበት የተረጋጋ ኢኮኖሚ ሰላም እና ዲሞክራሲ ላይ ነው …..? እንደኔ እንደኔ አዎ አገራችን በርካታ የልማትና የሰላም እምርታዎችን አስመዝግባለች ግን …በአደገኛ ሁኔታዎች ያሽቆለቆለችባቸው ሁነቶች ይበዛሉ … ስደቱ አሳሳቢ ነው …ከአገር ውጭ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ክፍለሃገራት ወደአዲስ አበባ የሚፈልሰው ህዝብ ሲታይ ‹‹እድገቱ የፈጠረው›› እያልን ማላገጡ መፍትሄ አይመስለኝም !!
አሁን ያለው የህዝብ ብሶት ቢዘረዘር ማለቂያ የለውም ግን ህወሃትን እንደአንድ ዜጋ የምጠይቀው …ቅን ብልህና ከቂምና በቀል የፀዳ ስርዓት ለመገንባት ይነሳ … በገፍ እየጓፈፈ በየምክንያቱ በየእስር ቤቱ ያጎራቸውን ጋዜጠኞች ጦማሪያን ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅት አባላትና የሃይማኖት ሰዎችን ይፍታ ! መንግስት እንኳን ውሃ ቀጠነ ብሎ ያሰራቸውን ንፁሃን ቀርቶ በብዙ ጥፋት ውስጥ ያለፉ የህግ ታራሚዎችን በምህረት መልቀቁ ህዝባዊነት ሰበአዊነት ነው !! አዎ ‹‹ 40ኛ አመት የምስረታ በዓሉ ግማሹን አስሮ ግማሹን አስጨፍሮ ›› ሊሆን አይገባም !! ከየትኛውም ድግስ ከየትኛውም ጭፈራና ንግግር በላይ ሁሉም ኢትዮጲያዊ ከህወሃት ኢህአዴግ የሚጠብቀው መሰረታዊ የአገሪቱ ችግሮች ያለምንም ምክንያት ድርደራ እንዲፈቱለት እንዲሁም ሃሳባቸውን በመግለፃቸው ብቻ የተለያየ ስም ተለጥፎባቸው ያታሰሩ ልጆቹን ጓደኞቹን የስራ ባልደረቦቹንና ወንድምና እህቶቹን እንዲፈታለት ነው !!
ሰላም !!
No comments:
Post a Comment