Translate

Thursday, February 26, 2015

ልታሰር ነው 3

ልታሰር ነው 3
(አሌክስ አብርሃም)
ሰው እንኳን መታሰር ይሞት ይለ እንዴ ? ብየ ራሴን አበረታታተሁ …ሰዎች ስንባል መቸም ንፅፅር ስንወድ …በቃ አንድ ችግር አፍጥጦ ሲመጣብን ያንን ችግር እንቢ ብለን ማምለጥ ሲያቅተን የባሰ ነገር እየመዘዝን ችግራችንን ‹‹ምናላት ይች›› ብለን ማቃለል እንወዳለን ! ጉንፋን ሲየዘን ‹‹ሰው ቲቢ ይያዝ የለ እንኳን ጉንፋን ተመስገን ነው ›› አንድ ጣታችን ሲቆረጥ …‹‹ሰው እግርና እጁ በፈንጅ ይቆረጥ የለ እንኳን ጣት ›› እግርና እጃችን ቢቆረጥ ‹‹ሰው አንገቱ ይቆረጥ የለ …›› ሚስታችን ጥላን ብትሄድ ‹‹ትሂዳ ደሞ ለዛች ጣሙጋ ስንት ልእልት የመሳሰሉ ቆንጆዎች በሞሉበት አገር ›› …..አንድ ቀን እንኳን ከማወዳደር መለስ ብለን ለምን ይሄ ይሆናል ብለን መጋፈጥ እንዴት ያቅተናል ….!! ይሄው እኔም ልታሰር ተጠራሁ….. ግን ምን ይደረግ ሰው እንኳን መታሰር ይገደል የለ (ሃሃሃ)
ሜላን ልነግራት ወሰንኩና በእኩለ ሌሊት ስልክ ደወልኩላት
‹‹አብርሽየ በሰላም ነው ?›› አለችኝ
‹‹ሰላም ነው ሜላየ ይቅርታ ረበሽኩሽ በሌሊቱ ››
‹‹ፊልም እያየሁ ነበር ችግር የለውም ….ምነው? ››
‹‹ እ…..ላግኝሽ …? ›› አልኳት ያው ባሏ እንደሌለ አውቃለሁ መቸስ ! ሜላ እንቅልፋም ነበረች እስካሁን በመቆየቷ እግዜር ተሰነባበቱ ሲለን ነው ብ አሰብኩ !
‹‹እንዴ በደንብ ነዋ ! እኔ ልምጣ ወይስ ትመጣለህ ?…››
‹‹ኧረ እመጣለሁ ….›› ብየ ተነሳሁ በሯ ሲከፈት ተሰማኝ ….
**** **** *****
ሜላ በቀይና ቢጫ አበባ የተንቆጠቆጠ ስስ የሌሊት ጋውን ለብሳለች ….. ጋውኑ አጠር ስለሚል ጥርት ያሉ ውብ እግሮቿ የገነት አእማድ መስለው ቁመዋል …ጡቶቿ በተንቀሳቀሰች ቁጥር በከፊል ብቅ እያሉና እየተሸፈኑ ድብብቆሽ ከአይኔ ጋር ይጫታሉ …ጫፎቻቸው በስሱ ጋውን ላይ የፍቅር አይን መስለው አፍጥጠዋል ….. ወገቧ ላይ በማሰሪያው እንደነገሩ ሸብ ያደረገችው ካውን ዳሌዋን ክፉኛ አጋኖታል ….እንደው ወገቧ ላይ ለይስሙላ አሰር ያደረገችውን የዐርቅ ቀበቶ ጫፎን ሳብ ባደርገው …የሚል ሃሳብ ሽው አለብኝ …መቸም ከጋውኑ ውስጥ ምንም አትለብስም ….አለኝ ይሄ ነገረኛ ልቤ …. የወንድ ልጅ ልብ ውስጥ ደርሶ እንደርችት የሚፈነዳ ((ሰይጣን)) ሳይኖር አይቀርም …የሴት ልጅ ውበት ደግሞ መለኮሻው ክብሪት ! (ሰው አሁን በዚህ ሰዓት ይፈላሰፋል )
‹‹ሜላ ››
‹‹ወይየ አብርሽ›› አለችኝ ፊት ለፊቴ እየተቀመጠች …. የምለውን ነገር ለመስማት ጓጉታ ….ኤዲያ ታፋዋ ተጋለጠ ….አቤት ቅላት … አቤት ጥራት ግን ወንዶች ለምንድነው የማናምረው ?የፈለገ ብናምር የሆንን ፍልጥ ነገሮች ነው የምንሆነው ከምር …እግዜር በእኛ ተለማምዶብን ሴቶችን የፈጠረ እስኪመስለኝ ! ወንዶችን ወክየ በሚላ አፈጣጠር ቀናሁ ! ሴቶች በየቀኑ መስተዋት ላይ እያፈጠጡ ራሳቸውን አለማፍቀራቸው ይገርማል !
‹‹ባክሽ የሆነ ሰው ደውሎ ነገ ልታሰር እንደሆነ ነገረኝ እና ያው ልሰናበትሽ ብየ ነው ››
‹‹እ???????????????? ›› አለች አይኗ ፈጦ
‹‹አዎ››
‹‹እንደፈራሁት አብርሽ…… እንደፈራሁት …… ተው እያልኩህ …አትፃፍ እያልኩህ ….ገብስ ገብሱን ፃፍ እያልኩህ አብርሽ…. ልማት ልማቱን ፃፍ እያልኩህ …. መንገድ መንገዱን …. ግድብ ግድቡን ፃፍ እያልኩህ …. ዲሞክራ ዲሞክራሲውን እድገት እድገቱን ፃፍ እያልኩህ …. በዓል በዓሉን ፃፍ እያልኩህ እምቢ ብለህ …እንደፈራሁት …›› ሳታስበው ተነስታ ቆመች መልሳ ተቀመጠች …ከምር ከእኔ ይልቅ እሷን የሚያስሯት ነበር የምትመስለው ….ተጨናነቀች በመጨረሻ መሃላችን የነበረውን ጠረንጴዛ ዙራ እኔ ጎን ተቀመጠች ….ጠረኗ የእስር ቤት አጥር ያዘልላል !! በልቤ እንዲህ ገጠምኩላት
እኔ ምልሽ ውዴ
ሻወር የምትወስጅው በሽቶ ነው እንዴ ?
‹‹ እስቲ አሁን ምን አደረካቸው ? ….አርፈህ እቤትህ ቁጭ ብለህ በፃፍክ …እሽ የት እንሂድላቸው … በአገራችን ላይ ካልፃፍን የት ሂደን እንፃፍ … እሽ መንግስታችንን ካልወቀስን ካልከሰስን የማንን መንግስት እንውቀስ …ኦባማን ውሃ ጠፋብን ብለን እንክሰስላቸው ?…ፑቲንን መብራት ያጠፋህብን አንተ ነህ እንበል ?… ኢሳያስ አፈወርቄን የትራንስፖርት ችግር ለምን ፈጠርክ እንበል? …. አንጌላ ሜርክልን የቤት ኪራይ ዋጋ አናታችን ላይ ወጣ ይህን ማስተካከል ካልቻሉ ስልጣን ይልቀቁ እንበል ? …. አልበሽርን የታሰሩትን ፍታልን እንበለው …. ስለአገራችን ችግር ግብፅ ታህሪር ሂደን ሰልፍ እንውጣ ?…. የራሳችንን መንግስት በተሰማን መንገድ በጎደለን ነገር ሁሉ መውቀስ ካልቻልን እሽ ምን እናድርግ ? ….. ትናገሩኝና ዋ የሚል መንግስት ምን ጉድ ነው …..? ››
እንዴዴዴ ሜላ እንዲህ የመረረ ነገር መናገር ትችላለች እንዴ ? ….ከምር እንዳያስሯት ፈራሁ ! ሃሃሃ ‹‹በቃ ሜላየ ተይው እሱ ያመጣውን መቀበል ነው ›› አልኳት !
‹‹እሱማ ባንቀበልስ ምን እናደርጋለን ? ….ወይኔ ሴት መሆኔ ! …… ነገ ስንት ሰዓት ነው የቀጠሩህ … ?››
‹‹ወደሶስት ሰዓት አካባቢ ››
‹‹ ይገርማል በቃ አብርሽየ እንዳትጨናነቅ … መታሰር እኮ መሸነፍ አይደለም ማንም ተራ ሰው አይታሰርም … ቢያንስ ሁሉም ቦታ መኖርህ የሚያስፈራቸው ከሆነ አይናቸው ስር አስቀምጠው ለመጠበቅ ሲሉ አሳሪዎች የሚያስሩት ፍርሃታቸውን ነው አይዞህ … ማንዴላ አምሳ አራት ዓመት ታስረው የለ እንዴ ››
‹‹ኧረ ሚላየ ማንዴላ የታሰሩት ሃያ ሰባት ዓመት ነበረኮ ››
‹‹ያው ነው … ከወጣትነት ላይ የተቀነሰ አንድ ቀን እንደሁለት ቀን ነው የሚቆጠረው … እ….ደግሞ ማነው ስሙ ታስሮ አልነበር …በቃ ታላላቅ ሰው ተብሎ ያልታሰረ የለም ….ምን ሩቅ አስኬደህ አባቴ ራሱ ሁለት አመት ታስሮ ነው የተፈታው… ››
‹‹እንዴ አባትሽ ደግሞ ምን ሰርተው ታሰሩ ? ››
‹‹እሱ እንኳን እናቴን በቅናት ተነሳስቶ በመደብደቡ ነው ›› ልስቅ ነበር ተውኩት …ሚላየ የኔ ቆንጆ ተጨንቃ ማፅናናቷ እኮ ነው ! ‹‹ሲሪየስ እናቴን ለምን እንደደበደባት ታውቃለህ …ወንዶችኮ ጥጋበኛ ናችሁ››
‹‹ለምን ደበደቧት ››
‹‹ልደቱን ረስታው መልካም ልደት ስላላለችው በቃ ልብሽ ይሄን የጠፋው ሌላ ሰው ልብሽ ውስጥ ገብቶ ነው አለና በቃ ደበደባት ›› ብላ ትክዝ አለች ፡፡ አባቷ እውነትም ጥጋበኛ ነበር ብየ አሰብኩ ! ሞልቃቃ ! ኢትዮጲያዊያን ሚስቶች በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልጋቸው የባላቸውን የልደት ቀን ከማወቅ በላይ የባላቸውን ትክክለኛ ደመዎዝ ማወቅ ነው !ረስተንም ሆነ ደብቀን የደመወዛችንን መጠን በደበቅን ቁጥር ሴቶች ቢደበድቡን ሁሉ በየወሩ አገር ጦር ሜዳ በሆነች ነበር !
‹‹አብርሽ በጧት ተነሳና ፂምህን ተስተካከል …ሻዎር ውሰድ …ፅድት በል …የት አባታቸው! እነሱ እያሸማቀቁና ተስፋ እያስቆረጡ የበታችነት ተሰምቶህ ዝም እንደትል ነው ፍላጎታቸው …ዝንጥ እምር በል ….አለባበስም ከፅሁፍ በላይ ይናገራል …መልክ መፅሄት ነው ሁሉም በየቀኑ ተሸምቶ የሚያነበው …ኑሮህን የሚዘግብ መፅሄት ነው …ተራቡ ብሎ መፃፍን ቢከለክሉ ይሄ ሁሉ ረሃብተኛ ነብስ ያለው ጋዜጣ እኮ ነው አይደበቅ ! መብራት ጠፋ ብላችሁ አትናገሩ ቢሉ ጨለማው እራሱ አፍ አውጦ ለአለም ያውጅ የለ …. ! ተዋቸው ….ብቻ አንተ ማንን ደስ ይበለው ብለህ ትጎሳቆላለህ …ቆንጆ ሁን !!››
‹‹እንዳንች ›› አልኩ አምልጦኝ
‹‹አትቀልድ …ደግሞ ቲሸርት ለብሰህ ነጠል ነጠል እያልክ እንዳትሄድ … የምን ቀድሞ እስረኛ መምሰል ነው … ሽክ ብለህ ትካሻህ ከበድ ብሎ ቢሯቸው ትሄድና ‹ፈለጋችሁኝ› ማለት ነው ቀብረር ብለህ …አገርህ ነው … ህዝብህ መሃል ነህ … ልዩነቱ እነሱ መሳሪያ ይዘዋል አንተ አልያዝክም መሳሪያቸውን የማይፈራ ሰው ሌላ ምናቸውን ሊፈራ ይችላል መቸስ ፍቅራቸውን አይፈራ …..›› ኧረ ሚላ
‹‹ደግሞ አብሬህ ነው የምሄደው …››
‹‹እንዴዴዴዴ አንችማ እኔጋ መታየት የለብሽም ››
‹‹ቀላል እታያለሁ …ብቻህን እንዳልሆንክ ህዝብ ከጎንህ እንደሆነ ይወቁ …እነዚህ ነጠላዎች መነጣጠል እንጅ አብሮነት ያማቸዋል …ስብሰባ አይወዱ አንድነት አይወዱ …››
‹‹እንዴ አንች ታዲያ ህዝብ ነሽ እንዴ ሜላ ›› አልኩ እየሳኩ
‹‹ነኝና …ከአንንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አንዷ ነኝ ! በቃ አሁን ግባና ተኛ … እንዳትፈራ … ደግሞ እግዚአብሔር ፍርሃታችንን ገልብጦ ራሱ ደስታ ላይ ማዋል ያውቅበታል አይዞን ›› ብላ በትኩስና ለስላሳ ከንፈሯ ጉንጨን ግጥም አድርጋ ብትስመኝ … እስከዛሬ አለመታሰሬ ቆጨኝ !ሃሃሃ ! ከምር ግን ነፍሴ የሆነ ምቾት ተሰማት ሴት የላከው ወላ ጅብ ወላ አንበሳ ወላ …አሳሪ አይፈራም !! ዘራፍ የሚላ ጎረቤት !
*** **** *****
በቀጣዩ ቀን ጧት ሚላ እንደነገረችኝ ሽክ ብየ ዘነጥኩ …. ሰርግ የተጠራሁ ነበር የምመስለው ! ሚላ እቤት ስትመጣ ራስ የሚያስት ውበት ደፍቶባት ሽክ ብላ ነበር … የለበሰችው አጭር የእራት ልብስ ውብ እግሮቿን ከወትሮው የባሰ አርዝሟቸዋል … በዛ ላይ ተረከዙ ረዥዥም ጫማ ! ደረቷ እንደ ፀሃይ እያበራ ቀጭን የወርቅ ሃብል ….የሃብሉ ማጫወቻው የተሳሳሙ ጡቶቿ መሃል ለመግባት ወደታች እየተንጠራራ … ከምር ቅድም የዘነጥኩ መስሎኝ ነበር ሜላን ሳያት በሌሊት ልብስ የቆምኩ ነገር መሰለኝ … አንፃራዊ ነው !! ደግነቱ ትንንሽ እና ቆንጆ ከንፈሮቿን አሞጥሙጣ
‹‹ዋው …የኔ ወንድም እኮ ቆንጆ ነህ ›› ስትለኝ … ተረጋጋሁ ! እንዲህ ((በህዝብ ታጅቦ )) መታሰር ማን አጋጥሞት ያውቃል ….በሰደፍ እየተዳፋ በዱላ እየተወገረ በካቴና ተጠፍንጎ እየተጎተተ እኮ ነው ስንቱ የታሰረው …እግዚአብሄር ይመስገን ይህን ክብር የሰጠኝ ሃሃሃ! መንገድ ላይ እኔና ሜላን የማያየን ሰው የለም …እየተሳሳቅን እያወራን ስንሄድ ሰው ሞቅ ያለ ድግስ የሚጠብቀን ፍቅረኞች አድርጎ ሳያስበን አልቀረም …አንዳንዱ ሲያፈጥ ‹‹ምነው የኔን ቦታ ሰጥቶህ ሚላ በሸኘችህና በተቀፈደድክ ›› እላለሁ በውስጤ ! የኛ ሰው ቆንጆ ሴቶች ሁልጊዜ ወደገነት ዝቅ ሲልም ወደአልጋ የሚሸኙ ይመስለዋል ! የዋህ !
*** **** *****
‹‹ሄሎ ›› አልኩ ልክ የተቀጣጠርንበት ቦታ ስንደርስ ለአሳሪየ ደውየ
‹‹ሄሎ አብርሃም መጣህ ጎሽ ….እኔማ ይሄ ልጅ ሌሊቱን በሱዳን አድርጎ ኮብልሎ ይሆን እንዴ እያልኩ አሰብኩኮ ››
‹‹ኧረ ምን አስኮበለለኝ ››
‹‹ እየውልህ ሚስቴ በሰላም ተገላገለች ››
‹‹ኧረ እንኳን ደስ ያለህ ….››
‹‹እንኳን አብሮ ደስ ያለን ወርቅ የመሰለ ወንድ ልጅ ወለደች ››
‹‹በጣም ደስ ይላል ››
‹‹አዎ …ከነቃጭሉ ዱብ አደረገችው …የኔ ሚስት ጀግና ናት መቸም ›› ሳቄ መጣብኝ ‹‹ …አሁንኮ በቃ እሷን እቤት አድርሰን እስቲ ቁርስ ልብላ ብየ እዚህ ካስት ሬስቱራንት ቁርስ አዝዠ እየጠበኩህ …ነበር …. ና ቁርስ በልተን በዛው እወስደሃለሁ ››
‹‹ እሽ›› ብየ … ወደካስት ሬስቶራንት አመራን ብዙ አይርቅም… እዚህ ባለ ዘጠኝ ፎቁ ህንፃ አንደኛ ፎቅ ላይ ነው … ወይ ጉድ ሰው እያሰረ እንዲህ ፀዳ ያለ ሬስቶራንት ቁርስ ይበላል ….
ሚላ ክንዴን ይዛኝ ቀስ እያልን ደረጃውን ወጣን …ካለወትሮዋ ዝም ብላለች የፈራች መሰለኝ …. ጧት ስለሆነ ሰው የሚባል የለም … ሬስቶራንቱ ጋ ደርሰን ወደውስጥ እጥፍ ስንል ….ያየሁትን ነገር ማመን አልቻልኩም ….. ማመን አልቻልኩም ….. እደግመዋለሁ ማመን አልቻልኩም !
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
..
.
.
.

ባጭሩ ሁሉም የማውቃቸው ጓደኞቸ በዛ ነበሩ…የሚላ እህት እራሷ እዛው ነበረች እና በአንድ ላይ ምን ብለው ጮሁ ……..‹‹ ሃፒ በርዝ ደይ …. …….››
‹‹አአአአይ ይሄማ የደስታ መግለጫ አይደለም …28 ስለሞላኝ ተበሳጭታችሁ ከዚች እድሜ አናሳልፈውም ብላችሁ ድፍት እንድል ….በማሰብ የተሴረ ነገር ነው ! አይ እንኳን ይችን …..ስንት እናውቃለን ! እንዴ እንዴት አይነት ነገር ነው ይሄ ? ሰው ላይ ስንት ነገር አለ? … እስቲ ሌሊቱን እጀን አልሰጥም ብየ እንደ መይሳው ካሳ ሽጉጤን ጠጥቸ ብሞትስ ?? …. ምናይነት ነገር ነው ይሄ ??….›› እያልኩ ግራ ተጋብቸ ስቀባጥር ሚላ ጠጋ አለኝና
‹‹ተው እንጅ የኔ አንበሳ አቡቹ .... እንኳን የሚጠጣ የሚታይ ሽጉጥ ከየት አባትህ ታመጣለህ ? ሽጉጥ ራሱ አፍህ ላይ እንዴት እንደከበደህ ባየህ ሂሂሂሂሂ…..…ለማንኛውም ሃፒ በርዝ ደይ ›› ብላ ጉንጨን በስሱ ስትስመኝ … ተረጋጋሁ !! እንደውም አቤት ይሄ እድሜ እንዴት ይሮጣል አንዱንም ሳንሰራው 28 ብየ ቁጭ !
‹‹ ሃፒ በርዝ ደይ …. …….››
ልክ እንደትልቅ ሰው ረገምኳቸው ‹‹ እድሚያችሁ ይጠር ! ›› ይሄ ሁሉ ጭንቀት በጓደኞቸና በሚላ ዋና አዛጋጅነት የተቀናበረ የልደት በአሌ ነበር …. 28 አመቴን የሚያበስረውን ሻማ እፍ ብየ አልነበረም ያጠፋሁት ….እፎፎፎፎፎፎፎፎፎይ ስል የታመቀ የጭንቀት ትንፋሸ እሳቱን ድርግም አድርጎ አጠፋው … ይሄ ህዝብ መቸ ይሆን እንዲህ ጭንቀቱን አውጥቶ የሚተነፍሰውና የብሶት ነበልባሉን ከውስጡ ድርግም አድርጎ የሚያጠፋው …አቦ ቀን ይምጣለት!

No comments:

Post a Comment