Translate

Sunday, February 1, 2015

አንዳርጋቸው ጽጌ በእኔ እይታ

በየትናዬት (Awash_43)
አንዳርጋቸው ለኔ እንደ ሙሴ ነው። እንዴት ብትሉ እንዲህ እላችኋለሁ። ሙሴ ምቾት ከበዛበት ከፈርኦን ቤት ይልቅ የወገኖቹን ስቃይና መከራ እቀበላለሁ ብሎ በእምነት ለቆ ወጣ። ሙሉ ታሪኩን በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ታገኙታላችሁ።Andargachew Tsige, Ginbot 7 secretary
አንዳርጋቸው ከወያኔ ቤት ይልቅ የወገኖቹን ግፍና መከራን እጋራለሁ ብሎ በእምነት በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን ለቀቀ። እንዳውም ለማስታወስ ያህል “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭ” ብሎ በፃፈው መፅሀፍ ቂም ተቋጥሮበት ቂምን አርግዞ መገላገል ያቃተው ወያኔ አሰረውም፣ ደበደበውም። ከዛም አገር ለቆ ከወጣ በኋላ እጁን አጣጥፎ በቃኝ ብሎ እንደሌሎቹ አልቀመጠም። የአገሩ ጉዳይ እረፍት ስለሚነሳው ቅንጅት ከተፈጠረ በኋላ በዛው ውስጥ ሆኖ ተሳትፎውን አበርክቶ በዝዋይ ማረሚያ ታሰረ።
እምቢ ለሀገሬ ብሎ ገና ለጋ ወጣት እያለ ልጓዝ በድል ጎዳና የዘመረውን ዝማሬውም በድል ስላልተወጣው እንደገና ሊያድሰው ብሎም ለመታገል ግንቦት ሰባት (7) ተብሎ የሚጠራውን ንቅናቄ ከመሰረቱት አንዱ ሆኖ በዛም ብቻ ሳይወሰን የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል ሲመሰረት በግንባር ቀደምነት በኤርትራ በርሃ ዱር ቤቴ ብሎ ገባ።

ያኔም በየካቲት ዛሬም በግንቦት የነበረው የህዝብ አመፅ በደርግም በወያኔም ስለተነጠቀ እና የሰፈነው የጨለምተኝነት ጉዞ በተለይ አሁን በባሰ መልኩ ብሎም ህልውናን የሚፈታተን አስከፊ ሁኔታዎች በአገራችን ሰማይ ላይ ስላንዣበበ ወያኔ በምርጫ በሚባል ቋንቋ ቦታውን እንደማይለቅ ስለታወቀ የትጥቁን ትግል ሊመራ ቤቱን በበርሀ አሸዋው ወስኖ ሁሉ አይገባኝም ብሎ መሸገ። ለዚህም ወያኔ አብረው የነበሩትና ዘረኞቹን አገር አውዳሚነቱን ትውልድ ገዳይነቱን፣ ሉዓላዊነትን አሳልፎ ሰጭነቱን ሲያውቁ የከዱት ላይ ዱላው እጥፍ ድርብ የሚሆነው ለዚህም ይመስለኛል። ብዙዎቹ ታስረው ስቃይ በዝቶባቸው ከተለቀቁና ወደ ውጭ ሲወጡ እንኳን ወያኔን ሊበቀሉት ሊታገሉት ቀርቶ አንድም ትንፋሽ ሳይተነፍሱ ምንም እንዳልተደረገ ዝምታን መርጠው ቁጭ ያሉት። አንዳርጋቸው ግን በተቃራኒው ነው። ታጋይ አስመስለው እስካለበት ኤርትራ በርሃ ድረስ ቅጥር ነፍሰ-ገዳይ የተላከበት መሆኑ የቅርብ ቀን ትውስታችን ነው። ይህ የሚያሳየው ምን ያህል እንዳስጨነቃቸውና ፋታ እንደነሳቸው ልብ ይሏል።
ግን ያች ክፉ፣ ዓመት ክፉ ወር፣ ክፉ ቀን፣ ክፉ ሰዓት፣ ክፉ ደቂቃና ሰኮንድ አንድ ላይ ተጋጥመው ይህን ለዓእምሯቸው እረፍት የነሳቸውና በቃላት ሳይሆን አምርሮ እንደሚታገላቸው ብሎም እንደሚፋለማቸው የተረዱትን ሰው ብዙ ብር አፍስሰው እጃቸው ላይ እንዲወድቅ ያደረጉት። ቀን ሲጥል እንደሚሉት ዓይነት።
አዎ ብዙዎች ታስረዋል። እየታሰሩም ግፍንና መከራን ተቀብለዋል። አሁንም እየተቀበሉም ነገም እንደሚቀበሉ ይታወቃል ስርዓቱ እስካለ ድረስ። አንዳርጋቸውን ልዩ የሚያደርገው ግን አንድም ከአለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አለማቀፍ ህግን በጣሰ መልኩ መታፈኑ፣ ሁለትም የታሰረበት ቦታ አለመታወቁ ሶስትም በቤተሰብና በዘመድ አለመጎብኘቱ አራትም የህግ ጠበቃ አለመኖሩ ልዩ አድርጎ የኢትዮጵያዊያንን እይታ የሳበው።የሚገርመው ከህዝብ ጋር ቢያገናኙት እንጅ ባያገናኙት ባይጠይቁት አይደንቅም ምክንያቱም የፋሽስት ወያኔ ባህሪ ነውና። አንዳርጋቸው የቀደምት አርበኞችን ገድል ለአድሱ ትውልድ ለማስተላለፍ ድልድይ የሆነ ጎልማሳ አርበኛም ስለሞነ ይፈሩታል።
የህይወት ውርስ ሆኖ የህይወትን ፀጋነቱን ለወጣቱ አስተላልፏል። ልክ እንደቀደሙት ወይም እንደጥንቶቹ አበው። ለዚህ ነው አንዳርጋቸው በህይወቱ የተቀሰተ ለአላማው የፀና የአገር መድህን የሆነው። ወጣቱ፣ ጎልማሳው፣ አረጋዊያኑ በተለያዩ ድህረ-ገፆች ስሙን እየጠሩ የተቀባበሉት። ስለዚህ አንዳርጋቸው የአበው የትግል ታሪክ በትውልዱ ተቀበለ! ለአዲሱም አሻገረ!
የኢትዮጵያዊያን ለዘላለማዊነቱን በራዕዩ አሳደረ!
ከሀዲዎችን አራቆተ ህይወታቸውን አከሰረ!
ለትግል ተጣራ እውነትን አበሰረ!
ነፃነትን እስካልተገኘ ድረስ የሚፈነዳ የዘላለም ቦምብን ቀበረ!
አንዳርጋቸው የአንድነትን መስመር አሰመረ!
በልደቱ አማረ! 
በስራቱም ገመረ!
አንዳርጋቸው አንድ አደረገን የአንድነትን ቃል ተናገረ!
አበበ ካሴን፣ እስክንድርን፣ ርእዮትን፣ አቡበከርን፣ በቀለ ገርባን፣ ኦልባና ሌሊሳን፣ ውብሸት ታዬን፣ አበበ ቀስቶን፣ ኦኬሎ አኳይን የዞን ዘጠኝ ጦማርያንን፣ አብረሃ ደስታን፣ ጋዜጠኞችን፣ እንዲሁም ብዙ ሽህ እስረኞችን አቀፈ አስተባበረ።
አንድ- አርጋቸው የነፃነት አርበኛ ስለሆነ ይፈሩታል። ሁሌም ለባንዳ ፍርሀቱ አርበኛ ነው።
አንድ- አርጋቸው ስጋውን ቢያስሩትም ህሊናውንና መንፈሱን መቸም ቢሆን አያስሩትም። ተወደደም ተጠላም በህይወቱ የአገር አርበኛ ሆኖ ቢሞትም ህያው ሰማእታችን ሆኖ ይቀጥላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ አንድ ነገር ይለናል። “ከእስረኞች ጋር እንደታሰረ ሆናችሁ እስረኞችን አስቡ” ስንቶቻችን አስበን ይሆን?
ለምን ነካኩብኝ ይህን እጄ ቋያ!
ሲጀምር ህይወቱን የሰጠ ለኢትዮጵያ።
ለካስ ሲፈጠር እናቱ ስም ሰጥታው፣
ሁን የሀገር መድህን ብላ መረቀችው፣
እሱም አላወቀው እናቱ ስትቀባው፣
ሆኖ ሲገኝ እንጂ ምስጢሩ የገባው።
ይህ February 9 ለሚከበረው 60ኛ አመት ልደቱ ማስታወሻ ትሁንልኝ

No comments:

Post a Comment