ጥር 21/2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ የምርጫ ቦርድ የሚባል ተቋም ያለበትን ደረጃ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህ ደረጃ እንዲዋራድ ከጀርባ ሆኖ አመራር የሚሰጠው ገዢ ፓርቲም ሆነ መንግሰት በዚያው ልክ የሚገባቸውን የተዋረደ ደረጃ የያዙበት ዕለት ነው ብለን እናምናለን፡፡ አንድነት ፓርቲ አንድም የህግ ጥሰት ሳይፈፅም የሚያደርጋቸውን ሁሉ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና በሀገሪቱ ህግ እየፈፀመ ባለበት ሁኔታ በህግ ሽፋን የገዢው ፓርቲ ልሳን የሆነው ፋና ሬዲዮ፣ የመንግሰት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር የከፈቱት ዘመቻ የመጨረሻ የሆነውን አንድም ህጋዊ መሰረት የሌለውን ህገወጥ ውሳኔ በአንድነት ፓርቲ እና አባላት ላይ አሰተላልፈዋል፡፡
ገዢው ፓርቲና መንግሰት በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲነበብ ያደረጉት የፖለቲካ ውሳኔ በኢትዮጵያ ሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ከወረቀት አልፎ በተግባር እንዳይታይ ግብዓት መሬቱን ፈፅመዋል፡፡ በዚህ ፀያፍ ተግባር ከፊትም ሆነ ከጀርባ ሆነው የተሳተፉ ግለሰቦችም ሆኖ ተቋማት በታሪክ ተገቢው የውርደት ቦታ እንደሚይዙ እምነታችን ነው፡፡ ይህ ህገወጥ አካሄድ ህጋዊ መሰመር እንዲከተል የበኩላቸሁን ድርሻ የተወጣችሁ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች በሀገር ውሰጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ ሁሉ በተለይ በገዢው ፓርቲ እኩይ ሴራ በሀስት ተወንጅላችሁ በወህኒ ቤት ለምትማቅቁ ታጋዮች ታሪካችሁ በወርቅ ቀለም ተፅፎዋል፡፡ በቀጣይም ያለምንም መዘናጋት እና ተሰፋ መቁረጥ በምናደርገው ሰላማዊ ትግል በሀገራችን ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሰርዓት ትንሳኤ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለንም፡፡
የምርጫ ቦርድ ተብዬው ተቋም በህገወጥ መንገድ ለሆዳቸው ባደሩ ጥቂት አንድነት ፓርቲ አባላት እና በአንድነት አባልነት በማይታወቁ የገዢው ፓርቲ ጥርቅሞች ለተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ ዕውቅና ሰጥቻለሁ ማለቱን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት ያነገብነው የነፃነት መንፈስ በምርጫ ቦርድ በሚሰጥ ሰርተፊኬትና ዕውቅና ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ ስለአልሆነ ለነፃነት የምናደርገውን እልህ አስጨራሽ ትግል የምንቀጥል ሲሆን፤ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የአንድነት መዋቅሮች እና የአንድነት አባላት ለዚህ ህገወጥ ቡድን በግልፅ እውቅና እንዲነሱ እንጠይቃለን፡፡
ፓርቲያችን በመጨረሻ ሰዓት እንኳን ተፈትነው ለወደቁ ተቋማት እድል ለመስጠት ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ወሰኖ እንቅሰቃሴ በማድረግ ላይ ቢሆንም፤ በዛሬው ዕለት ጥር 22/ 2007 ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ የፓርቲያቸን ፅ/ቤት በፖሊስ ተወሮ የፓርቲው ንብረት ያለምን ህጋው ርክክብ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጎዋል፡፡ በአሰተዳደር የተሰጠን ውሳኔ በፍርድ ቤት የማሰለወጥ ህጋዊ ሰርዓት እንዳለ ቢታወቅም ህገወጥ አስተዳደራዊ ውሳኔን በፖሊስ ወረራ ለማሰፈፀም የተሄደበት መስመር ገዢው ፓርቲና መንግሰት አሁንም ከጫካ አሰተሳሰብ ያለመውጣቸውን እና የአውራ ፓርቲ ፍልስፍናቸውን በማናለብኝነት ለመተግበር መቁረጣቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ህገወጥ ድርጊት ተጠያቂው ትእዛዙን ያስተላለፈው ክፍል መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ሰለሆነም በሀገር ውስጥ እና በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅቶች፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሰርዓት እንዲጎለብት ፍላጎት ያለችሁ ሁሉ ይህን እኩይ ተግባር በማውገዝ ተጨባጭ እርምጃ እንድትወሰዱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ድል የህዝብ ነው!!!
ጥር 22/ 2007 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment