ኤርምያስ ለገሰና የመለስ-ዳቪንቺ ኮድ አሰባበሩ ! ርዕስ ከሰጠሁት ዝርዝር ጉዳይ በጥልቀት ከመግባቴ በፊት ፣ ብዙ ጊዜ ወያኔያዊው አገዛዝ ከጥንቷ ኮሚንስት ሶቭየት ህብረት ጋር መንግሥታዊ መዋቅሩም ሆነ የአገዛዝ ስልቱ ስለሚመሳሰልብኝ ፣ ዘና አርገው ወደ ሚያዝናኑኝ የሶቭየቶች ቀልድ ቤት ዘው ማለቴ አልቀረም ፡፡ ከገባሁ አልቀረም በየአምስት አመቱ ፣ በአገራችን እና በህዝቧ ላይ የሚሰራውን ቀልዳዊ ምርጫ አስመልክቶ የሚደሰኮርልን የአምስት ዓመት ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከጥንቷ የሶቭየት ህብረት የቅድ ፕላን ጋር ፍጹም ስለተመሳሰለብኝ በዚህ ምጸታዊ ቀልድ አሃዱ ልበል ፡፡
አንድ ጊዜ ብሬዥኔቭ ወደ ሶቭየት ህብረት የኮምፕዩተር ማዕከል ጎራ ብሎ ፣ ሶቭየት ህብረት ከኮምኒዝም በምን ያህል ርቀት ላይ እንደምትገኝ አስልተው እንዲነግሩት ለኮምፕዩተር ጠበብተኞቹ ትእዛዝ ይሰጣል ፡፡ ሳይንቲስቶቹም ያሏቸውን ዳታዎች ሁሉ ኮምፕዩተሩን አጉርሰውት ውጤቱን ይጠባበቁ ጀመር ፡፡ ቀን አለፈ ፥ ሁለተኛውም ቀን ተተካ ፥ ሶስተኛውም ቀን ሰለሰ ፡፡ ቀን ቀንን እየወለደ በመጨረሻው ላይ ኮምፕዩተሩ ምጡን ተገላገለ ፡፡ ውጤቱንም እንዲህ አስመዘገበ ፡፡ሶቭየት ህብረት ከኮሚንዝም መዳረሻ በአስራ ስምንት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች ፡፡ ሳይንቲስቶቹ አድናቆታቸውን ለኮምፒዩተሩ ቢሰጡትም ልባቸው ግን ፈራ ፡፡ ይህ ሊሆን አይችልም ! ኮምፕዩተሩ ተሳስቶ መሆን አለበት እያሉ ፣ የብሬዥኔቭን ጡጫ በመፍራት እንደገና ኮምፕዩተሩ ስሌቱን እንዲያሰላ አዘዙት ፡፡ በድጋሚ የታዘዘው ኮምፕዩተር ካለፈው አቋሙ አንዲትም ጋት ሳይጨምር ያችኑ ውጤት ቁጭ አደረገ ፡፡
በስተመጨረሻም የተቋሙ አዛውንት ኃላፊ አብረውት ለተጨነቁት ሳይንቲስቶች ጓዶች! ኮምፕዩተሩ ሳይሳሳት እቅጩን ነው የተናገረው ምንም ስህተት አላደረገም ፡፡ ጓድ ብሬዥኔብ በየአምስት ዓመቱ የምናደርገው አንድ እርከን ወደ ኮሚንዝም ለምናደርገው ጉዞ አንድ ደረጃ ይራምደናል ስላሉ ፣ አምስት አመትን በአስራ ስምንት አመት ስናባዛው 5×18 = የምናገኘው ውጤት 90 ዓመት ነው እንዳለው ቀልዱ ወያኔም ምርጫ በቀረበ ቁጥር የአምስት አመት የትራንስፎርሜሽን እቅዱን እየጋተን እነሆ አገዛዙ ወደ ሃያ አራተኛው አመት ጭካኒያዊ አገዛዙ እያስገባን ነው ፡፡ በዚህም ላይ በተደጋጋሚ እንደሚነግረን የህወሃት/ ኢህዴግ አገዛዝ ለመጪዎቹ ሃምሳ ዓመታት ጭምር አውራ ፓርቲ ሆኖ እንደሚገዛን በግልጽ እየተናገረ ነው ፡፡ ኧረ እንደብሬዥኔብ 90 ቢልስ ማንን ፈርቶ ! ዝንጉ ነን እንጂ ከምርጫው በፊት እኮ አንድ የአምስት አመት እቅድ አውጪ ኮሚቴ ሰሞኑን አዋቅሯል ፡፡
የምርጫው ገብስማ ዶሮ ቀድሞ ታርዷል ፡፡ ባለቦቃው በግም ቀድሞ ተሰውቷል ፡፡ የቀድሞዋ ኢትዮጵ ጋዜጣ ባለቤትና የአሁኑ ኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና « ኢሳት በዚህ ሳምንት እያለ የሚያቀርበውን ውይይት » በአንክሮ ከሚከታተሉት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ ፡፡ በዚህች አጭር ጽሁፌ ውስጥ የሲሳይ አጌናን ክህሎት ማንሳት በቂ ላይሆን ይችላል ፡፡ መነሻዬ ሲሳይ ባይሆንም ፣ አቶ ኤርምያስ ለገሰን ወደ መድረክ አምጥቶ ከህዝብ ጋር እንዲቀራረብ መድረኩን ከከፈተለት ወዲህ ፣ የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚንስቴር ደኤታ የአቶ ኤርምያስና የሲሳይ መናበብ ግን እጅግ መስህብ ያለው በመሆኑ ፣ ተመልካች ኢሳትን ከቦ በመመሰጥ እንደሚመለከት ማረጋገጥ ይቻላል ፡፡ ይህ ፕሮግራም አፍቃሪ ኢሳትን ብቻ ሳይሆን አፍቃሪ ህወሃቶችንም ጭምር በዙርያው እንዳስኮለኮለ ያሳብቃል ፡፡ ብላቴናው ሚንስቴር ዴኤታ ኤርምያስ ለገሰ የወያኔ /ኢህአዴግን ጉዋዳ ፥ ጎድጓዳን ባዛዥነትም ሆነ ናዛዥ ዘመነ ስልጣኑ ውስጡን በደንብ አውቆት ከልምዱ ህወሃት ሊሠራ የሚችለውን ስውር ሴራ ደረጃ በደረጃ አስቀምጦ በመጽሃፉ ቢያስነብበንም ፣ ከልምዱ ከቀሰመው ችሎታው አልፎ ፣ ወያኔ ወደፊት ሊሠራው ይችላል ብሎ ያሰባቸውን መሰርያዊ መለሳዊ-ዳቪንቺ ኮዶች ጭምር ኮዳቸውን እየፈነከተ በኢሳት ላይ አሳይቷል ፡፡ አሁንም እያሳየ ነው ፡፡ የአቶ ኤርምያስ ለገሰን ምልከታዊ አቅጣጫዎችን የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች አድምጠው ምን ያህሉን ተጠቅመውበታል የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ ሰሞኑን ወያኔ ኢሃዴግ ከጨዋታ ውጭ ያደረጋቸውን አንድነትንና ፥ መኢአድን ጨዋታቸውን እንዲያውቁ በዚህ መሳይ ፕሮግራም ላይ ከሁለት ወይም ሶስት ሳምንት በፊት የሰጠውን ምክሩን ተቃዋሚዎች ወይም አልተረዱትም ወይም አላደመጡትም የሚል ስጋት አለኝ ፡፡ አቶ ኤርምያስ ከልምዱ ያጋራንን ነጥቦች አንዳንዱን ካስታወስኩት ላውሳ ፡፡ ፓርቲዎቹ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ አንድ ቃለ አቀባይ ብቻ ፣ ሁሉም በጋራ የተስማሙበትን ቃላት ሳይጨምር ወይም ሳያዛባ ያቅርብ የሚለው ሃሳብን የተከተሉ አይመስልም ፡፡ በስሜትና በንዴት እየተመራን ፣ የፓርቲው አመራሮች የሆኑ ሰዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ ማዕከላዊነትን የያዙ ሃሳቦች ስለሚረሱ ፣ ለወያኔ ኢህአዴግ በር መግቢያ ቀዳዳ ስለሚሰጡት በቃላት ጨዋታ ከደጋፊዎቻቸው ጋር እንዲላተሙ መንገድ ስለሚከፍት እንጠንቀቅ ያለው ማስገንዘቢያ በቅጡ ተቃዋሚዎቻችን መንደር የዘለቀ አልመሰለኝም ፡፡ በሰሞኑ አንድነትን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ወያኔያዊ ብተና ላይ ተጠባባቂው ቃል አቀባይ አቶ አሥራት አብርሃም የደረሰባቸውም ድብደባ እንደጠጠበቀ ሆኖ ስንት ዘመን የተደከመበት አንድነት በወያኔ ስውር ሴራ እንኩቶ ሆኖ መውደቁ ስላበሳጫቸው ፣ፓርቲው መቃብሩ ላይ ጉንጉን አበባ እንዳስቀመጠና ከንግዲህ አመራሩ የፈለገው አርፎ ሥራውን እንዲሰራ ፣ የፈራም ልጁን ቁጭ ብሎ ማሳደግ እንደሚችል ፣ ያልፈራም የራሱን አማራጭ እንዲወስድ ያደርገዋል ያሉት አባባል እምብዛም አልተዋጠልኝም ፡፡ እረዳለሁ ! በተደጋጋሚ ለአገር አንድነት ሲሉ ከመለስ አገዛዝ ጋር ጥርስ ለጥርስ ተያይዘው ፥ የመለስንም የአገር ክህደት በጥልቀት በመጽሃፍ አሳትመው ፥ በአረናም ውስጥ ታግለው ፥ እንደገና ያቅሜን ብለው ወደ ህብረ ብሄር ፓርቲ ታቅፈው ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈሉ ፡፡
በዚያን ወቅት ግን የተናገሩት ቃላት ታጋዩን ተስፋ እንዲቆርጥ የሚያደርግ ቃላት ስለሆነ አብረው ተመካክረው የ… እንደሚሉት ተረት ፣ ቃል አቀባዮች የሚሰጡት መግለጫ በተቻለ መጠን ታጋዩን ትጥቁን የሚያጠነክርበት ሁኔታ እንዲፈጠርና እንዲበረታ እንጂ ጨዋታው አለቀ ዳቦ ተቆረሰ ከሚለው አቅጣጫ እንዳይዘም ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል ፡፡ ለዚህ ፓርቲ ሲሉ ዘብጥያ የወረዱትን ፥ አንዱአለምን ፥ ሃብታሙን ናትናኤልን ፥ እንዲሁም በቆርጥነት ግንባሩን ሳያጥፍ መከራ የሚቀበለውን አብርሃ ደስታ ጭምር… የመሳሰሉ እልፍ አእላፍ ታጋዮችን ለአውሬው አሳልፎ ሰጥቶ ወደ የፈለግንበት አቅጣጫ እንሂድ ማለቱ ተገቢ አይደለም ፡፡ በመለስ-ዳቪንቺ ኮድ አሰባበሩ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ወያኔ በዚህ ምርጫ እንኳን ወንበር ሊሰጥና ምራቂ ኮሾ ከረሜላም ለተቃዋሚዎች እንደማይሰጥ አስረግጦ ነግሮን ፣ ጭራሽ እንደብሬዥኔብ የአምስት ዓመቱን ፕላን የሚነድፉና የሚያጸድቁም ካድሬዎቹን እያሰለጠነ እንደሚገኝ አውግቶናል፡፡ ወያኔ በእቅዱ ለሚቀጥሉት ሃምሳ አመታት እንደሚገዛ ጭምር እቅድ እንዳለው የነገረንን ነገር ባለማስተዋል ይሁን በመዘናጋት ፣ ከየፓርቲዎቹ ትዕግስቱን ከአንድነት ፥ አበባውን ከመኢአድ አስነስቶ አቧራ እንደሚያስጨስና ፓርቲዎቹ ቶሎ ቀዳዳዎችን እንዲደፍኑም ጭምር ምክሩን መለገሱን አስታውሳለሁ፡፡ ምርጫ ቦርድ ወያኔያዊውን ሴራውን ባለፈው ሃሙስ የፖለቲካ ውሳኔውን ሲያሳልፍ ፣ አንድነትም ሆነ መኢአድ ጽህፈት ቤታቸውን ጭምር በግድ ማስረከብ እንዳለባቸው የተረዱ ባልመሰለ መልኩ ፣ ሳያስቡት ወረራ ተደርጎባቸው ሰነዶቻቸውን እንኳ በአግባቡ ሳይሰበስቡ እንደተዘረፉባቸው ፓርቲዎቹ ተናግረዋል ፡፡ በዚህ መሃል የአባላትም ሆነ ረጂዎች ዝርዝር ስለሚገኝ ለዘንዶው ወያኔ ግብር ምላሽ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም ፡፡ አሁን ጽህፈት ቤት የላቸውም በየክልሉም ያሉትን ደጋፊዎቻቸውንና መዋቅሮቻቸውን የሚያሳየውንም ፍኖተ ካርታ አስረክበዋል ፡፡
የግኑኝነታቸውም እዝ ሰንሰለት የተበጠሰ ነው የሚመስለው ፡፡ ዘንዶው ደግሞ አሁን ርምጃውን አዲስ አበባ አካባቢ አይደለም የሚወስደው ፡፡ በየክልሉ ያሉትን መዋቅሮችና ግለሰቦችንም ጭምር ነው የሚያድነው ፡፡ በኢሳት በዚህ ሳምንት ፕሮግራም አቶ ኤርምያስ ለፓርቲዎቹ ምክር በሚመስል ጉዳይ ትላንት የጠቆማቸው ጉዳዮች ሚዛን የሚደፉና ፓርቲዎቹም አጥንተው በአስቸኳይ ሊተገብሯቸው የሚገባ ጉዳይ ነው ፡፡ የአንድነትም ሆነ የሰማያዊ ፓርቲዎች አንዳንድ አመራሮች አብዛኛዎቹ ከመኢአድ ቤት የተገኙ ሰዎች ናቸው ፡፡
በሂደት ነገሮች ሳይጥማቸው ተለያይተው የየራሳቸውን ፓርቲዎች መስርተዋል ፡፡ የሶስቱም ፓርቲዎች ፕሮግራም ባብዛኛው ሚዛን በሚደፋ መልኩ ተመሳሳይ ናቸው ፡፡ የርስ በርስ ኬምስትሪያቸው ምናልባት አልተጣጣመ ሊሆን ይችላል ፡፡ የርስ በርስ ኬሚስትሪ ደግሞ ከሃገር በላይ አይሆንም ፡፡ ምናልባት ትክል- ወያኔ ሰዎች ስላሉ አብረን ልንጓዝ አንችልም የሚል ስጋቶች እስከዛሬ ስለነበሩ በአንድ ላይ ግምባር ፈጥሮ መጓዝ አልተቻለ ይሆናል ፡፡ አሁን በሶስቱም ፓርቲዎች ውስጥ ያሉት አመራሮች አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው ፡፡ በዚህ አደገኛና መስቀለኛ ጉዞ ላይ ባስቸኳይ ተገናኛኝተው የጋራ እቅድና ፍኖተ ካርታ ነድፈው ለቀጣዩ ወሳኝ ትግል በጋራ መቆም ይገባቸዋል ፡፡ ልደቱ ፥ ትግስቱ ፣ አበባው፥ኢንጀነሩ በራሳቸው ጊዜ ለወዳጃቸው እጃቸውን ሰጥተው ወጥተዋል ፡፡ ቀሪዎችም ሊኖሩ ይችላሉ ፡፡ ይህ አያሸብርም ፡፡ ጉንጉን አበባ ሊያስገዛም አይችልም ፡፡ ለታሪክና ለአገር አንድነት ሲባል በአስቸኳይ ተጠራርቶ መፍትሄውን መፈለግ ነው ፡፡ ማነው ባለሳምንት ደግሞ በይቅርታ አልጠይቅም ጉዳይ ሰማያዊ ፓርቲ ስለሆነ በቶሎ ከአንድነትና ከመኢአድ ሰዎች ጋር መምከር ያለበት ጉዳይ ነው ፡፡ በስተመጨረሻ አጅግ የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን የምርጫ ቦርድ ሰዎችን በተለይ ሁለቱን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ከፊት አጋፍጠው ፥ የህወሃቶቹ ዶክተር አዲሱና የወይዘሮ አዜብ ወንድም በሂልተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አለመገኘታቸው ነው ፡፡
እስከመቼ ድረስ የአባዱላ ቅጥቅጦች በታላቁ የኦሮሞ ህዝብ ስም ይሳለቃሉ ! _? እባካችሁ ተቃዋሚዎች የመለስ-ዳቪንቺ ኮድ ተሰብሮ በአቶ ኤርምያስ እየተነገረ ነውና ይህን ቃለ መጠይቅ ቢቻል ደግግማችሁ ስሙት ፡፡
No comments:
Post a Comment