Translate
Tuesday, February 24, 2015
ልታሰር ነው !!
(አሌክስ አብርሃም)
አዳሜ ቀልጅ ….እኔ እንደሆንኩ ልታሰር ነው ! በቃ ግልግል … ምን ታመጫለሽ…. ሁለት ቀን ከግማሽ ‹‹አሌክስ ይፈታ ›› ትያለሽ ከዛ በሶስተኛው ቀን …‹‹ባፍ ይጠፉ በለፈለፉ …ተው እያልነው ሲቀባጥር ….›› እያልሽ እኔኑ ትወርጅብኛለሽ ! አለቀ !! ከዛ አለም ይረሳህና ሚስኪን ቤተሰብ የተቋጠረ ሰሃን ሲያመላልስ ይኖራል !!ቢመርም እውነቱ ይሄ ነው ! ቢበዛ የሆነ አገር አምባሳደር ይመጡና እስረኞቹን ጎብኝተው አገራቸው ላይ መግለጫ ሊሰጡ ነው ይባላል ‹በቃ አሳሪዎች ጉዳቸው ፈላ› ተብሎ መግለጫው በጉጉት ሲጠበቅ ‹‹ሚስተር አምባሳደር ›› እንዲህ ይላሉ
‹‹ ኢትዮጲያ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ አገሪቱ በመልካም የእድገት ጎዳና ላይ መሆኗን ታዝቢያለሁ … ይሁንና አንድ ቅር ያለኝ ነገር ታሪካዊ ቅርሶቿን ለመጎብኘት ለሚሄዱ የውጭ አገር ዜጎች በቂ ሆቴሎች የሏትም ….አገራችንም በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች ስልጠናና ድጋፍ እንደምታደርግ ገልፀንላቸዋል ›› በቃ!
‹‹እንዴ ስለእስረኞቹስ ክቡር አምባሳደር ?›› … ይባል የለ...?ሚስተር አምባሳደር ኮስተር ባለ አነጋገር ‹‹የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ.. ሃዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ !›› ብለው በእንግሊዝኛ ቅኔ ይዘርፉብናል ሃሃ ! ፍርድ ቤት ስቀርብ መጀመሪያ አስር ሰው ፍርድ ቤቱ በር ላይ ቁሞ አያለሁ …‹‹ውይ ይሄ ሁሉ ሰው ለኔ ነው የመጣው …ህዝቤ አገሬ እንኳን መታሰር ቢሞትላትስ ምናምን›› ስል …አንዱ እስረኛ ወደጆሮየ ጠጋ ብሎ …
‹‹ባክህ ላንተ የመጡ አይደሉም ! አንድ ሰውየ ከአራት ሴቶች የወለዳቸው ልጆች ናቸው… ሰውየው በቅርቡ ስለሞተ ያለችውን ላዳታክሲ ውርስ ሊያሳውጁ መጥተው ነው ›› ብሎ ኩም ያደርገኛል !! ወይ ነዶ ! ለዚች አገር እንኳን ለአመታት መታሰር ይቅርና ለደይቃ ዜብራ ላይ መቆም እንኳን አያስፈልግም !! እያልኩ ወደችሎት እገባለሁ …..‹‹ በእነ እከሌ የክስ መዝገብ ….አስራአራት ቀን የጊዜ ቀጠሮ !›› ይላሉ ዳኛው ! በቃ!! በነገራችን ላይ ‹‹ በእነእከሌ የክስ መዝገብ የተከሰሱት አስር ተከሳሾች ›› ሲባል ይሄ አስሩ ሰዎች የተከሰሱበት መዝገብ በስሙ የተሰየመው ሰው ‹አምበል› ይመስለኛል !
ይሄ እንኳን ከታሰርኩ በኋላ የሚደርስ ጉዳይ ነው …..አሁን ማን እንዴትና መቸ ነው የሚያስረኝ የሚለውን ለእናተ ለጓደኞቸ ማሳወቅ ይኖርብኛል .. ምንም ቢሆን አብረን ኑረናል … ተሰዳድበናል ተመሰጋግነናል ተደናንቀናል በሰርግ በልደት መልካም ምኞት ተገላልፀናል ….ምንስ ፌስ ቡክ ቢሆን ዝም ብሎ ከርቸሌ ይወረዳል እንዴ…. ይሄማ ጨካኝነት ነው …. ሲሆን ሲሆን አጠር ያለ ንግግር ማድረግ ተገቢ ነው…. አለ አይደል ‹‹ የዘንድሮውን እስር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ልዩ የሚያደርገው ባቡሩ በተመረቀበት ማግስት …›› አይነት ንግግር ! ሃሃሃ
ወደዝርዝሩ ልግባ … ወሬ አባዛሁባችሁ መሰል …አትቀየሙኝ ሰው ሲታሰር የረሳው ነገር ሁሉ ትዝ ይለዋል ! ((አንድ ጥናት በቅርቡ ይፋእንዳደረገው ከሆነ)) ‹መታሰር አእምሮን ይከፍታል …› ወደራስም ይመልሳል (ቻይና ውስጥ የተሰራ ጥናት ነው) …እንደውም ማንኛውም ዜጋ ከስምንት ወደዘጠኛ ክፍል ሲያልፍ ሁለት ሁለት ወር ቢታሰር ለአገር እድገት በዛውም እስራት በፍትሃዊ መንገድ ለሁሉም ዜጎች እንዲዳረስ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ይላል ጥናቱ ! አትፍረዱብኝ ሰው ሲታሰርኮ አንዳንዴ ይዘባርቃል ….ነብስ አይደል ያስጨንቃል ! በቃ ወደዋናው ጉዳይ ልግባ !
ትንሽ ቆይቷል … ኧረ እንደውም ወራቶች አለፉት አንድ ቆፍጠን ያለድምፅ ያለው ሰው ደወለና (በዛ ድምፁ ግጥም ቢያነብበት ብየ ተመኝቻለሁ)
‹‹አሌክስ አብርሃም ነህ ?›› ይለኛል
‹‹አዎ ነኝ ማን ልበል ››
‹‹እኔን አታውቀኝም … ምንተስኖት ተረፈ ባህሩ እባላለሁ ….ምንተስ ቢሮ በምንትስ ማስከበር የፀረ ምናምንና የፀረ እንትን ጥምር ኮሚቴ አባል ነኝ ….. ሰሞኑን ትንሽ የምትፅፋቸው ነገሮች ተንኳሽ ስለሆኑ እና ትእግስታችን እንደደሃ ድስት ስለተሟጠጠ ልናስርህ ነው ›› አለኝ ! ቀልዱን እንዳልሆነ እንዲሁ ገብቶኛል ! መጀመረያ ደንገጥ አልኩ …ሳስበው ማንን ደስ ይበለው ብየ ነው የምደነግጠው እንደውም ዘራፍ ማለት አለብኝ …ወንድ ልጅ ቆራጥ ነው !! (ለሚመጣው ትውልድ ፍርሃትን አናወርስም …የራሱ ፍርሃት ይበቀዋል ብየ በቃ ተደፋፈርኩ…(ሲመጣብኝ እኮ ቀላል ሰው እንዳልመስላችሁ ሃሃ) በነገራችን ላይ ‹‹የሚመጣው›› ትውልድ በጣም ፈሪ ከመሆኑ የተነሳ ‹‹አልመጣም›› እንዳይል ፍርሃት አለኝ )
‹‹ማነህ ለመሆኑ እንዲህ በምሽት ደውለህ አስርሃለሁ ምናምን የምትለኝ ባክህ … እዛ ሂደህ በሬህን እሰር…አልበዛም እንዴ !! ›› አልኩት ነብር … ግስላ …. ፍም እሳት ሁኘ ! …ቁጣየ ለራሴም አኮራኝ …ወንድ አብርሽ ! አያቶችህ እስካሁን በመቃብራቸው ውስጥ ሁነው በዚህ ወንዳወንድነትህ እየፎከሩ ያንቡሌ ቡሌ እየጨፈሩ ነው …. እንደውም የአባትህ አባትማ መቃብሩ ጠቧቸው ነው እንጅ ደርደር ብለው ሊፎክሩ ነበር …. ‹‹ማነሽ አልጣሽ ጎራዴና ጋሻየን አቀብይኝ ›› ሊሉም አስበው ነበር ….መሞታቸው ትዝ ሲላቸው ተውት ! ምናምን አለኝ ልቤ !
ድሮም ይሄ ቀብር ለአያቶቻችን ይጠባል ….ራሳቸው ከወራሪ ባተረፉት መሬት ለምን ይጨናነቃሉ ሰፋ ተደርጎ ይቆፈር ብየ ነበር ….ሰሚ አጣሁ ! ይሄው እንዲህ ለደስታ ቀን እንኳን የሚፎክሩበት ቀብር ጠበባቸው !! ወይኔ አያቶቸ ! አረብ ለሩዝ እርሻ በገፍ በሚገዛው መሬታችሁ እንዲህ ለመፎከሪየ እንኳን መሬት ይጥበባችሁ ….ብየ እንባየ በአይኔ ግጥም አለ ! ግን አሳሪየ እስሩን ፈርቸ ያለቀስኩ መስሎት ደስ እንዳይለው ብየ እንባየን ዋጥ አደረኩና
‹‹እኮ ለምንድነው በአገሬ ላይ ፃፍክ ተብየ የምታሰረው አልበዛም ….›› አልኩት
‹‹አብርሃም ይሄ የአገር ጉዳይ ነው …የህዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማስከበር ስንል ማንኛውንም እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለብን ደግሞ የፃፈውን ሁሉ ታስራላችሁ በማለት ስማችንን ማጠልሸት ተገቢ አይደለም ይሄው እዚህ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ራፖርት ፀሃፊዎች ሲፅፉ ይውሉ የለም እንዴ ማንን አሰርን ….ይሄው ስንትና ስንት የመንግስት ጋዜጦች ይፃፉ የለ ማንን አሰርን …. ይሄ ስም ማጥፋት ነው ! አንተንም ቢሆን መክረናል ዘክረናል አንተ ግን ሰው ከሳቀልኝ ብለህ አፍህ ያመጣውን ስትዘላብድ ይሄው በመጨረሻ ህገ መንግስቱ ላይ በግልፅ የተደነገገውን አንቀፅ መቶ ስምንት በመተላለፍ ለዚህ በቃህ .. ›› አለኝ !!
‹‹ አሃ ህገ መንግስታችን መቶ ስድስት አንቀፅ ብቻ አልነበር እንዴ ያለው … ወይስ ያገራችን እድገት አንቀፁንም አሳደገው ….ወይስ ሳንሰማ ተጨመረበት…??የለም የለም ስነዜጋ ላይ ባልተማርነው አንቀፅማ አንከሰስም …እንዴት ባልተማርነው ማትሪክ ባልተፈተነው አንቀፅ እንከሰሳለን ? ›› ብየ ጠየኩ !(እውቀት ለመቸ ነው መዘዝ አደረኳት ያስቀመጥኳትን …ዝም ካልናቸውኮ ገና ማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ አስራ ሶስት ቁጥር ሁለትን በመተላለፍ ተከሰሃል ሳይሉን አይቀቀሩም ፡))
‹‹ ኦኦኦኦ አታድርቀኝ እንግዲህ…. መጀመሪያ ታሰር ….ከታሰርክ በኋላ ህገመንግስቱን አንብበን እንደሚሆን ክስ እንፈልግልሃለን …..አሁን ሌላ ጣጣ አልፈልግም …አስሬ እንዳመጣህ የታዘዝኩት እኔ ነኝ … ዛሬ ነበር እንደውም የታዘዝኩት ሚስቴን ድንገት ምጥ ይዟት ሆስፒታል ስለሄድኩ ነገ ጧት አይናለም ሻይ ቤት ሜክሲኮ ጋ ብትመጣልኝና ባስርህ ውለታህን አረሳም ›› ሲል በአሳዛኝ ድምፅ ጠየቀኝ !
‹‹ውይ እህቴን ….አሁን እንዴት ናት ታዲያ ባለቤትህ? ›› አልኩ ከልቤ አዝኘ …ምንስ አሳሪየ ቢሆን ‹‹ሁለታችንም አንዲትም እናት በወሊድ አትሙት ›› የሚል አገራዊ መፎክር ፎክረን የለም እንዴ?! …መታሰር ሌላ እናት ሌላ !በዛ ላይ ማን ያውቃል የሚወለደው ልጅ አባቱ ያሰራቸውን የሚያስፈታ ጀግና ቢሆን ???? …ትውልድ እኮ ትልቅ ተስፋ ነው !አባት ባጠፋው ልጅ ላይ ድንጋይ የሚወረውርማ አናቱ ላይ የጥላቻ ታሪክ የሻገተበት ቁሞ ቀር ነው !
‹‹ ምን አውቃለሁ …ዶክተሮቹም ብር መበዝበዝ ነው እንጅ ልጁ ለምን ቶሎ እንደማይወለድ አይናገሩ … ማሰር ነበር ወደዛ ጠራርጎ ›› አለና ተማረረ
‹‹ግዴለም እንዳትሳሳት ጓድ … ባይሆን አዋልደው ሲያበቁ ታስራቸዋለህ ….በቃ እኔ ራሴ ለምን እዛው ሆስፒታል አልመጣምና በዛውም ባለቤትህን ጠይቄ ወደእስርቤት አንሄድም ?? ›› አልኩት… እውነቴን ነው ምጥ የተያዘች ሚስትን ያህል ነገር ትቶ ለእኔ ሲል ከሚመጣ …እዛው ብሄድለት ይሻላል … ማን ያውቃል ያኔ ሚስቱ ያረገዘችባት ቀንም እኮ ለስራ ይደወልልኝ ይሆን በሚል ስጋት በግማሽ ልብ ይሆናል(( የተቃቀፉት )) …ይሄማ ተገቢ አይደለም አለቃዎቹ ባያስቡለት እኔ አንደአንድ ዜጋ ላስበለት ይገባል !
‹‹ጎሽ ተባረክ አብርሃም …እኔ እንጀራ ሁኖብኝ እንጅ አንተኮ የምትታሰርም አይነት ልጅ አልነበርክ … ይገርመሃል እንድትታሰር ከመወሰኑ በፊት ስልክህን ጠልፈን ስናደምጥ …በቃ አንጀቴን ነበር የምትበላው ›› አለኝ ! ስላደነቀኝ ደስ አለኝ ! ለነገሩ ድምፁ ያስታውቃል ደግ ሰው ነው ! ግን ስልኬ መጠለፉን ሲነግረኝ ….
‹‹እንዴ ስልኬንም ጠልፋችሁት ነበር እንዴ? ›› አልኩት ተበሳጭቸ
‹‹ አዎ …ማናት ስሟ ያች በስልክ ስታወራ የምታስለው ልጅ ….እሷ ጋር ከተዋወክበት ቀን ጀምሮ የምታወራውን እንሰማ ነበር …ማናት ደግሞ ያች ማታ ማታ የአሰፉ ደባልቄን ዘፈን በስልክ የምትዘፍንልህ …እሷ ልጅ ጠፋች በሰላም ነው ? …ደግሞ ያ የዱቤ የስልክ ቀፎ የገዘሃው ሰውየ በደወለ ቁጥር አንዴ ባህር ዳር አንዴ ሃዋሳ ነኝ እያልክ የምትሸውደው …አንዴማ አዝነን የቢሮ ጓዶቸ አዋጥተን እዳህን ልንከፍልልህ ነበር ›› ሲል እንደልብ ጓደኛ ሚስጥሬን ሁሉ ዘከዘከው
‹‹ከምር ታበሳጫላችሁ …ይሄ ብልግና ነው … የመብት ጥሰትም ነው …..›› አልኩ በብስጭት
‹‹ አይ ይሄኮ የሰለጠኑት አገሮች ሁሉ እነቻይና ..አሜሪካ ….እንግሊዝ ….ፈረንሳይ …..የሚያደርጉት ነው አብርሃም…. ተው እንጅ …. እኛ ላይ ሲሆን ብቻ ነው እንዴ ብልግናና የመብት ጥሰት የሚሆነው ?? …የስልክ ጠለፋን ቃል በቃል ነጥብ ኮማ ሳይቀር ከአሜሪካ ነው የወሰድነው …..አልሰማህም በቅርቡ አሜሪካ የጀርመኗን ጃንስለር አንጌላ ሜርክልን ስልክ ጠልፋ ሴትዩዋ ባሏ ጋር ስታወራ ሲአይ ኤ ሲሰማት ከርሟልኮ …አንተ ከአንጌላ ሜርክል ትበልጣለህ ??……›› አለኝ ከኔ የባሰ ቆጣ ብሎ ! ምናባቴ ልበለው …ዝም አልኩ !
ቀጠለ ‹‹ አይዞህ አትተክዝ ካሁን በኋላ ስልክህ አይጠለፍ ያንን ፃፍክ ይሄንን ተናገርክ አትባል…ወላ የምታስልብህ ወላ ያሰፉ ደባልቄን ዘፈን እየዘፈነች ካርድህን የምትጨርስ ሴት አትኖር … የሚያሳድድህ የዱቤ ባለዳህ የለ …. በቃ ትታሰራለህ እረፍት ! …..በል እንግዲህ ጧት እንገናኝ ወዳጀ መልካም አዳር …..እንዳታረፍድ ልክ ሶስት ሰአት ላይ ናልኝ አደራ ›› አለኝ …ድምፁን ስሰማው ማሰር የሰለቸው ይመስላል !
‹‹ በል እሽ ጓድ ….ሚስትህን ምህረቱን ያውርድልሽ በሰላም ይገላግልሽ በልልኝ ›› አልኩና ስልኩን ዘጋሁ !! ለነገ ቀጠሮየ ለመዘጋጀት ያህል ‹‹ለእስር ቤት የሚያስፈልጉ እቃዎችዝርዝር ›› ብየ ፃፍኩ
ይቀጥላል !!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment