Translate

Tuesday, December 9, 2014

መድረክ፣ የጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና አገኘ

መድረክ፣ የጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና አገኘ 

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ጥላሁን እንደሻው ለፍኖተ- ነጻነት ገለጹ፡፡

Photo File
ሰልፉ ታህሳስ 5 ቀን 2007 ዓ.ም ከጥዋቱ 3፡00 ጀምሮ እስከ ከቀኑ 7፡00 የሚዘልቅ ሲሆን፤ መነሻውን ግንፍሌ ድልድይ አድርጎ መዳረሻውን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ታቦት ማደርያ ያደርጋል፡፡
በሰልፉ ከሚነሱት ዋና ዋና አጀንዳዎችም መካከል በ2007 ዓ.ም የብሄራዊ ምርጫ ጉዳይን በተመለከተ ኢህአዴግ የያዘውን ግትር አቋም አለዝቦ፣ ለድርድር ዝግጁ እንዲሆን መጠየቅ፤ የ2007 ብሄራዊ ምርጫ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ይሆን ዘንድ በገለልተኛ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች እንዲፈፀም፣ ምርጫ ቦርድ ከገዢው ፓርቲ ተላላኪነት ነፃ እንዲሆን፤ ኢህኣዴግ በምርጫ ዋዜማ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ማሳደድና ማሰር እንዲሁም ምርጫውም ማወኩን እንዲያቆም፣ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ. ኢህአዴግ ነፃ ፕሬስን ማፈንና ጋዜጦኞችንና ጦማርያንን ማሳደድና ማሰር እንዲያቆም፣ ኢህኣዴግ ላፀደቀው ህገ-መንግስት ተገዢ እንዲሆንና እንዲያከብረው እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ የትራንስፖርት እና የውሃ እጥረት እንዲፈታና የከተማው የቴሌኮሚኒኬሽን እና የመብራት መቆራረጥን የመሳሰሉ ጥያቄዎች እንደሚነሱ መድረክ አስታውቋል፡፡
መላው የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ፤ ፍትህና ነፃነት የጠማቸው ኢትዮጵያውያን፤ በኑሮ ውድነት ተማረው ከሰው በታች የሚኖሩ ዜጎች፤ በመብራትና በውሃ መቆራረጥ የተሰቃየው ነጋዴ፤ በአጠቃላይም መላው የከተማው ነዋሪ ለዚህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ስኬት እንዲረባረብ መድረክ ለፍኖተ ነፃነት በላከው መልዕክት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉ በአዲስ አበባ መስተዳድር እውቅና እንዳገኘም ለማወቅ ተችሏል፡፡

No comments:

Post a Comment