ኤርትራዊው በረከት ስምዖን በሕወሓት የምስረታ በዓል ላይ እኛ ብአዴኖች (የአማራውን ድርጅት ማለታቸው ከሆነ) ወያኔዎች ነን አሉት:: ሙሉ ንግግራቸውን አስቀምጠናል ያንብቡትና ትዝብትዎን ይስጡ::
ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የለውጥ ፍላጎቶች ዘመናትን ያስቆጠሩ ናቸው። የብዙ ትውልዶች የትግል ውጤትም ናቸው – ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚደረግ የቅብብሎሽ ትግል ሆኖ ኢትዮጵያን ለማሻሻልና
ለመለወጥ ኢትዮጵያዊያን ዋጋ የከፈሉበት ሂደትም ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የካቲት አስራ አንድ የተመሰረተው ህወሓት በዚህ ሂደት ውስት የሚጠቀስ አንዱ ድርጅት ነው። በዚያን ጊዜ ከተመሰረቱት ድርጅቶች ህልውናውን ጠብቆ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ተሳክቶለት በአሸናፊነት የወጣ ድርጅት ነው።
ህወሓት የሰራቸው ስራዎች ምንድን ናቸው ብዬ ሳይ፣ የመጀመሪያው በ1967 ዓ.ም ሲደራጁ ከዚያ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አካባቢ የነበረው ሁኔታ ማስታወስ ጠቃሚ ይመስለኛል። ለውጥ ውስጣችን እንዲቀሰቀስ፣ እኛ ጋር የነበረው የለውጥ ስሜት በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ውስጥም እንዲኖር፣ ብዙ ትውልድ መስዋዕትም እንዲከፍል ያደረገው የዴሞክራሲ የልማት እና የመለወጥ ብሎም የህዝቦችን ፍላጎት የሚያረካ ብቃት ያለው ሥርዓት ስላልነበረ ነው። እንደዚህ አይነት ስርዓት በሌለበት፣ በተለይ ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ የማይችል፣ የሃይማኖት፣ የብሔር መብት በአግባቡ ማክበር የማይችል የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና የልማት ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ የማይችል ስርዓት ባለበት እና በወቅቱ የነበረው ስርዓት የቆመው ከምንም ነገር በላይ በአፈና ስርዓት ተደግፎ በሆነበት፣ በጣም ግዙፍ ወታደራዊ ተቋም፣ በጣም ግዙፉ የስለላ ተቋም፣ በመላ ሀገሪቱ በተንሰራፋበት ሁኔታ እንዴት ነው ይህ የአፈና ስርዓት አሰወግዶ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ማምጣት የሚቻለው? ግዙፉን የአፈና ተቋምስ በታሰበው መልማስወገድ ይቻላል ወይ? እንደሚታወቀው በኢትዮጵያስርዓት ውስጥ የመጨረሻ ትልቁን አፋኝ የደርግ አገዛዝ 500ሺ ጦር ሰራዊት የነበረው፣ በጥቁር አፍሪካ በትጥቁም በወታደራዊ ብዛቱም የሚስተካከለው አልነበረም። ይህን ሃይል አስወግደህ ብቻ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ሊመጣ የሚችል የነበረው። ይህ ሃይል ባለበት ቀይ ሽብር ነበር የነበረው። ይህ ሃይል ባለበት አፈና ነበር የነበረው። ስለዚህ ይህን ግዙፍ ሃይል እንዴት ነው የምናስወግድነው? የሚለው ጉዳይ በጣም ብዙ መሰረታዊ ጥያቄዎችን መመለስ ይጠይቅ ነበር። ከሁሉ በፊት የጠራ ዓላማ መያዝንም ይጠይቃል። የት ነው የምደርሰው? መዳረሻየስ የት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ማስፈን፣ ለልማት የተመቸ ከባቢያዊ ሁኔታዎች መፍጠር፣ ዴሞክራሲያዊ አዲስ የሆነ አንድነት መፍጠር እነዚህን የመሳሰሉት ግልፅ ዓላማዎችን መያዝም ይጠይቅ ነበር። ሁለተኛ፣ ብቃት ያላቸው የትግል ስልቶች፤ ትክክለኛ አቅጣጫዎች መተለምና እነሱንም ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቅም ነበር። ስለዚህም ህወሓት ይሄን (ከላይ የሰፈሩትን) ይዞ ነበር የተነሳው። ህወሓትን ከሌሎች ድርጅቶች የሚለይበት ወሳኙ ነገርም ይህ ነው። ጥርት ያሉ ነገሮችን፣ ሊያታግሉ የሚችሉ፣ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ፣ ሃሳቦችን ይዞ መምጣት።
ላለፉት ሰላሳ አራት ዓመታት ከህወሓት ጋር አብረን ታግለናል። ድርጅቱን በቅርቡ እናውቀዋለን፣ ህወሓት ለሃሳብ ልዕልና ትልቅ ቦታ ያለው ድርጅት ነው። ጥርት ነገር ያለ መያዝ። ነገ ከነገወዲያ በምናያቸው ቦታዎች ሃሳብን እንዴት እንደማጥራት የሚችል ድርጅት ነው። ለትግሉ መነሻና መድረሻውን ጥርት አድርጎ በደንብ ማስቀመጥ በመቻል ላይ ትልቅ አቅም አለው። ስለዚህም ግልፅ የትግል ዓላማ ይዞ የተንቀሳቀሰ ድርጅት ነበር። ይህንን ዓላማ ይዞ በመጀመሪያዎቹ የደርግ ዓመታት የመሃል ሀገር እንቅስቃሴ በተዳከመበት ጊዜ ሸክሙ እዚህ ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ነበር። በጣም ከባድ ሸክም ነበር የተቋቋምነው። የትግራይን ሕዝብ ይዞ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በጣም ብዙ ዘመቻዎችን አልፏል። እኛ በለሳ እስከምንመጣ፣ በስድስተኛ ዘመቻ ላይ ነበር ትግራይ የደረስነው። እነዚህ ማዕበሎች ነበሩ። የደርግ ሰራዊት ይመጣል፣ ድርጅቱን ለማጥፋት ይሞክራል። ድርጅቱ ጥቃቱን ይቋቋማል፣ ወደአዲስ ምዕራፎችም ይሻገራል። በዚህ መንገድ የደርግ ማዕበሎችን እየተቋቋመ የዘለቀ ድርጅት ነው ፤ህወሃት። የሰው ሃይል እየተጠናከረ ሲመጣ በጋራ እየተፋለምን ኢሕአዴግን መስርተን ግዙፉን የደርግ ሰራዊት ለመደምሰስ ችለናል።
ስለዚህም የህወሓት አንዱ ትልቁ ሚና ተብሎ መጠቀስ ያለበት ምንድነው ከተባለ በኢትዮጵያ የአፈና ስርዓትን ማስወገድ ነው። ያንን የአፈና ስርዓት ማስወገድ ባይቻል ኖሮ፣ ከዚህ ግዙፉ የአፈና ተቋም ጋር ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት አትበቃም ነበር። ይህ በታሪክ የተለየ ተደርጎ መታየት ያለበት ነው። ሊከበርም፣ ሊገለጽም፣ ሊፃፍበትም የሚገባ ነው። የጦርነቱ ሂደት፣ የተከፈለው መስዋዕትነት፣ ትግሉ መሃል ሃገር ሲዳከም እዚህ ጫፍ ላይ እንደምንም ሕዝባዊ ትግሉን ጠብቀህ የመቀጠል ነገር ትልቅ ትልቅ መስዋዕትነትን፣ አስተዋይነትን፣ በዚህ ደረጃ ሕዝባዊ ልቦናን የሚጠይቅ ነበር። ለዚህም ነው የህወሓት ትልቅ ሚና፣ የነበረውን የአፈና ስርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ላይመለስ አድርጎ መታገሉ ተጠቃሽ የሚሆነው።
ይህም ብቻ አይደለም። ደርግ በወደቀ ማግስት ምንድን ነው የተደረገው ብለን ከመጀመሪያው እንይ። የካቲት 11 ድርጅቱ እዚህ ቦታ ትጥቅ ትግል ሲጀምር ይዞት የነበረውን ዓላማ በፍጥነት ወደ ተግባርመተርጎም የደመረበት ወቅት ነው። የአፈናው ስርዓት ተቋም ከተገረሰሰ በኋላ አዲስ መሰረተ ሰፊ ዴሞክረሲ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ የተዘረጋው። ስለዚህም ይህ መስዋዕትነት ባይኖር ኖሮ ያንን ማድረግ ይቻል ነበር ወይ? በብሔር ጥያቄ ዙሪያ በወቅቱ ብዙ አማራጮች ነበሩ። በኦሮሚያ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር የነበረው ኦነግ ነው። በደቡብ ኢትዮጵያም ብዙ ተመሳሳይ ድርጅቶች ነበሩ። በሶማሌም በአፋርም ተመሳሳይ ድርጅቶች ነበሩ። በመሐል ሀገር ኢሕፓ ሞካክሮ የተወው ትግል አለ። ተስፋ መቁረጥ በተዛባ አካሄድ የመሄድ እድሎች ሰፍተው የነበረበት ሁኔታ ነበር የነበረው። ይህን ተቋቁሞ በትክክለኛ መስመር ተመርቶ ጥሩ አጋሮች ካገኘ በኋላ የአጋርነት እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ላለፉት አርባ አመታት የታገለ ድርጅት ነው።
በሌላ መድረክ ከዴሞክራሲው ባሻገር በልማት ሥራዎች ላይ ያለውን አስተዋፅዖ እንመሰክራለን። ሆኖም ግን የህወሓት አስተዋፅዖና ሚና በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ ትውልድ በቅብብሎሽ ትግሉን ዳር ያደርሳል ብሎ የተነሳበት ሁኔታ በልዩ ሁኔታ መታየት ያለበት ይመስለኛል። ይህን ትግል ከመነሻው የመሩት እዚህ ያሉት ጓዶች ናቸው። ከእነሱ ጋር በመሆን አብረው ሲመሩት የነበሩት ምንአልባትም በአስተሳሰብ ልቀት ሁላችንም የምናከብራቸው አቶ መለስ ለዚሁ ትግል ያበረከቱት ትልቅ አስተዋጽኦም አለ።
ህወሓት የአስተሳሰብ ጥራት የነበረው፣ አስተሳሰቡንም በተጨባጭ ተግባር ላይ ማዋል የሚችል ድርጅት ነው። ይህም በመሆኑ ነው ብዙ ንቅናቄዎች ተጀምረው በከሸፉበት ሁኔታ ሃሳብን ተግባራዊ በማድረግና በተለይ ህዝብን ይዞ በብቃት በመታገል ረገድ ይኸው ድርጅት ውጤታማ የሆነውና እዚህ ደረጃም የደረሰው።
ብአዴኖችም ሁሌም ቢሆን ራሳችንን ከህወሓት ነጥለን ያየንበት ጊዜ የለም። ሁላችንም “ወየንቲ ኢና” (ወያኔዎች ነን) ነው የምንለው በዚህ ሁሉ ሂደት ጠንካራ ሠራዊት ገንብቷል። እኛ ደጀን ነው የምንለው፣ ከሕዝቡ ጋር የፀና እና ጥብቅ ግንኙነት ነበረው። ለሕዝብ ታዛዥ ሕዝብን የሚያከብር ድርጅት ነበር። በዚህ መንገድ እየታገለ ቆየ። እኛ በ1972 ዓ.ም. ከኢሕአፓ ተለይተን ህወሓት ወንድም ድርጅት ይፈልግ በነበረበት ጊዜ፣ ከበለሳ የመሐል ሃገሩ አልመች ሲለን ወደ ትግራይ እንሂድ ብለን መጣን። ከህወሓት ጋርም ተገናኘን፣ ከተገናኘን በኋላ በብዙ ነገሮችም አብረን ሠርተኛል፤ታግለናል። በወቅቱ እኛ ቁጥራችን ትንሽ ነበር። እነሱ ደግሞ በአንፃሩ ግዙፍ መሆን ጀምረዋል። እኛ መስዋዕትነት እንዳንከፍል ከእኛ በፊት እነሱ ለመሰዋት ብዙ ብዙ ነገሮች እያደረጉ እያገዙን፣ የእኛ ሃይል እንዳይመታ እንዳይመናመን ከፍተኛ እገዛ አድርገውልናል። በኋላ የእኛ እኛ ብአዴኖችም ሁሌም ቢሆን ራሳችንን ከህወሓት ነጥለን ያየንበት ጊዜ የለም። ሁላችንም “ወየንቲ ኢና” (ወያኔዎች ነን) ነው የምንለው። ስለዚህ ይህንን ምስክርነት የምሰጠው እንደ ብአዴን ሆኜ አይደለም፤ እንደ አንድ ወያናይ ሆኜ ነው። እንኳን ለዚህ በቃችሁ፤ እንኳን ለዚህ በቃን እላለሁ።
No comments:
Post a Comment