Translate

Monday, June 3, 2013

የኢትዮጵያውያን የ15ኛው ክፍለ ዘመን ገዳማት በሊባኖስ ተገኙ

• በዋሻው የተገኙት የግእዝ ጽሑፍና ሥዕሎች ማረጋገጫ ሆነዋልየኢትዮጵያውያን የ15ኛው ክፍለ ዘመን ገዳማት በሊባኖስ ተገኙ
ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በ15ኛው ክፍለ ዘመን በሊባኖስ ቀዲሻ ሸለቆ (Holy Valley) ይገለገሉባቸው የነበሩ አራት ገዳማት ከግእዝ ጽሑፍና ሥዕሎች ጋር ተገኙ፡፡
ኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲና ካፑቺን ፍራንቸስካዊ የምርምርና የሥልጠና ማዕከል ግንቦት 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በጋራ ባዘጋጁት የግእዝና የሱርስጥ (የሶርያ ቋንቋ) ጥናቶች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት አብዶ በድዊ፣ በገዳማቱ በድንጋይ ላይ የተጻፈው ጽሑፍና የቅዱሳንና የመስቀል ሥዕሎች መገኘታቸው ገዳማቱ የኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ያሳያሉ ብለዋል፡፡ 
‹‹አሕባሽ›› የሚል መጠርያ የተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን መነኮሳት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መሆናቸውንና በ15ኛው ክፍለ ዘመን በሰሜን ሊባኖስ ተራራዎች በተለያዩ አጥቢያዎች የኖሩ ናቸው፡፡ ገዳማቱም ማር ያዕቆብ በኢሕደን (Ehden)፣ ማር ጊዮርጊስ በሐድቺት (Hadchite)፣ ዴር ኤል ፍራዲስ እና ማር አስያ ናቸው፡፡
ጂኢአርኤስኤል የተሰኘ የጥናት ቡድን እ.ኤ.አ በ1991 የግእዝ የድንጋይ ላይ ጽሑፍና የተለያዩ መንፈሳዊ ሥዕሎች ማግኘቱን ሊባኖሳዊው አብዶ በድዊ ተናግረዋል፡፡ 
መነኮሳቱ በደብረ ሊባኖስ እንዴት ሊገኙ እንደቻሉ የተለያዩ መላምቶች እንዳሉ ያወሱት አጥኚው፣ አንዱ በእምነት የሚመስሏቸውን የግብፅ ኮፕቲኮችን የወንጌል መልዕክተኛነትን ለማገዝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 
መነኮሳቱ ሊባኖስ ተራራ (ደብረ ሊባኖስ) የደረሱት በ1470 እና 1488 መካከል መሆኑን በሥፍራው የነበሩትን የማሮናይት እምነት ተከታዮችን በስብከታቸው ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት መለወጣቸው ይነገራል፡፡ ከነዚህም አንዱ በኋላ ላይ የያዕቆባውያን ፓትርያርክ የሆኑት የብቆፋው ኖኅ (Nouh of Bqoufa) ይገኙበታል፡፡ 
በአካባቢው አጠራር ኢትዮጵያውያንን ለመጥራት በሚጠቀሙበት አሕባሽ የሚጠሩት ኢትዮጵያውያን በ15ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ከደረሰባቸው ጥቃት የሸሹ ደቂቀ እስጢፋኖስ መሆናቸውን ተመራማሪዎች እንደደረሱበት አብዶ በድዊ ተናግረዋል፡፡ 
‹‹በርካቶች እንደሚያምኑት፣ ከነዚህም መካከል ኢቫ ዊታኮውስኪ (Eva Witakowsky) እንደሚሉት መነኮሳቱ ደቂቀ እስጢፋኖስ ናቸው፡፡ በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ወገኖቻቸው ከደረሰባቸው ፍጅት አምልጠው ኢየሩሳሌም፣ ቆጵሮስ፣ ሊባኖስ፣ ሶርያና አርመን ድረስም የተሰደዱ ናቸው፡፡ ሊባኖስ እንደደረሱ በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል በተለያዩ አጥቢያዎች ቀዲሻ (ቅዱስ) ብለው በሰየሙት ቦታ መኖር ጀምረዋል፡፡›› 
የግድግዳ ላይ ሥዕሎችና የግእዝ ጽሑፍ ከሱርስት ቋንቋ ጽሑፍ ጋር የተገኙት በማር አስያ፣ ማር ጊዮርጊስና ማር ዮሃና ገዳማት መሆኑን ያወሱት አቅራቢው፣ ከተገኙት ሥዕሎች አንዱ የፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ ምስል ላሊበላ ይምርሃነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ካለው ጋር ይመሳሰላል ብለዋል፡፡ በማር ሙሳ አልሐበሺ ያለውም ጋይንት ቤተልሔም (ደቡብ ጎንደር) ካለው ጋር ተመሳስሎ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡ 
የግእዝ ጽሑፉ ከፊሉ የጠፋ ሲሆን፣ ያሉትን የግእዝ ቃላት የቋንቋው ፕሮፌሰሮች ባደረጉት ጥናት ኃይለ ቃሉ ጸሎት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹መሐረነ እስከ ለዓለመ ዓለም አሜን›› (ለዓለም እስከ ዘለዓለም ማረን አሜን) ይላል፡፡ 
በጉዳዩ ላይ ቀጣይ ጥናት እንደሚደረግበትም አብዶ በድዊ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
አስኮ በሚገኘው የካፑቺን ፍራንቸስካዊ የምርምርና የሥልጠና ማዕከል ከግንቦት 19-22፤ 2005 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው የግእዝና የሱርስጥ ጥናቶች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ከኢትዮጵያ ሌላ ከሩቅ ምሥራቅ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የመጡ ምሁራን 25 ጥናቶችን አቅርበዋል፡፡  

No comments:

Post a Comment