Translate

Monday, June 10, 2013

አንድ ብስጭት፤ ጉድ በል ሰላሌ ኢትዮጵያ አይደለህም ተባልክ…

946655_4270475898383_1063122582_n
ABE  TOKCHAW

አበበ ቶላ ፈይሳ እባላለሁ፡፡ አባቴ አቶ ቶላ ፈይሳ ልጅነቱን በኦሮምኛ ቋንቋ ተረት እየሰማ፤ ወጣትነቱን በኦሮምኛ ቋንቋ እያዜመ፤ ጉልምስናውን በኦሮምኛ እየፎከረ፤ እርጅናውን በኦሮምኛ እየመከረ የኖረ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ አባቴ የአባት እና እናቱ ቋንቋ ኦሮምኛን አጥብቆ እንደሚወደው ያህል እኔ ልጁን እና እናት ሀገሩ ኢትዮጵያንም ከመውደድ በላይ ይወደናል፡፡
ጣሊያን ሀገራችንን ሊወር የመጣ ጊዜ እርሱ የአስራ ሶስት አመት ልጅ ነበር፡፡ በዛን ጊዜ አባቱ እና በርካታ ጓደኞቻቸው በሰላሌ ጫካ መሽገው ነበር፡፡ አባቴ እና በርካታ ጓደኞቹ ደግሞ ልጅነታቸውን ተጠቅመው ቀን ከብቶች ሲጠብቁ እግረ መንገዳቸውን ጣሊያንን እየሰለሉ ሌሊት ለአባቶቻቸው ጣሊያን በዚህ ገባ በዚህ ወጣ የሚል ወሬ ያቀብሉ ነበር፡፡
ይህ በአንድ አንቀጽ ሲነገር ቀላል ይምሰል እንጂ በውስጡ ብዙ ፈተናዎች ብዙ መከራዎች ነበሩት፡፡ ግን ለሀገር የተከፈለ ነበርና እረኛው አባቴም አርበኛው አያቴም መላው ቤተሰቡም በእልህ እና በወኔ ነበር የሚያደርጉት፡፡ በወቅቱ ይህ ከዳር ዳር ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያደርጉት የነበረ የተባበረ ተጋድሎ እንደሆነ አባቴም ነግሮኛል መፅሀፍ ላይም ተፅፏል፡፡

እርግጥ ነው በየወቅቱ ከሁሉም ማህበረሰብ አባላት ለጠላት የሚያድር ባንዳ አይጠፋም፡፡ አባቴ እና መላው የሰላሌ ህዝብ፣ የወለጋም፣ የኢሊባቡርም፣ የገናሌም፣ የጎንደርም፣ የጎጃምም፣ የመቀሌም፣ የአዲሳባም፣ የጋምቤላም ህዝብ ባንዳን ይጠየፋል፡፡ እኔም ለጠላት ያደረ ሰው ደስ አይለኝም… ምክንያቱም “ኢጆሌ ቶላ ፈይሳ” ነኝና! ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነኝ እና፡፡
ትላንት አንድ ዜና አየሁኝ፡፡ በጣም ቅስም የሚሰብር ዜና ነው፡፡ በግብፅ ውስጥ የሚገኙ በአባት እና በእናታቸው ኢትዮጵውን የሆኑ ነገር ግን እናት እና አባቶቻቸው የነገሯቸውን ልብ ብለው ያልሰሙ ግለሰቦች እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ኦሮሞዎች ነን እንጂ የሚል መፈክር ይዘው ኢትዮጵያ የአባይ ግድብን ለመስራት መጀመሯን እንደሚቃወሙ በግብጽ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ደጃፍ ላይ በሰልፍ ገለፁ፡፡
በየዘመኑ፤ ውስጥ ውስጡን ለጠላት የሚያድር ባንዳ እንደሚያጋጥም ይታወቃል፡፡ እንዲህ በአደባባይ ግን ዜግነቱን ክዶ “የሚበነድድ” ባንዳ መኖሩን አባቴም አልነገረኝም በህይወቴም አይቼ አላውቅም፡፡
ጀነራል ከማል ገልቹ (እኔ ትክክለኛው የምለው) ኦነግ ሊቀመንበር ደጋግመው እንደነገሩን ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ ነው፡፡ “እኛ ኦሮሞ ነን እንጂ ኢትዮጵያ አይደለንም” የሚሉት ሰዎች ካሉበት የስደት ሀገር ጀነራል ከማል ገልቹን አግኝተው ቢጠይቋቸው ካለ ኦሮሞ ኢትዮጵያን ካለ ኢትዮጵያን ኦሮሞን ማሰብ እንደማይቻል በደንብ ያስረዷቸው ነበር፡፡
ለነገሩ ሰሚ ጆሮ ቢኖራቸው እኔ አባቴ እንደነገረኝ ሁላ እናት እና አባታቸው ኢትዮጵያ ማለት ማን እንደሆነች በኦሮምኛ ደጋግመው ሳይነገሯቸው አይቀሩም፡፡
አዎን፤ ኢትዮጵያ ማለት የአበሻ ጀብዱ መጽሀፍ ላይ ያሉት እነ አብቹ ዋጋ የከፈሉላት የሰማኒያ ብሄረሰብ ሀገር ነች፡፡ በሀገራችን መንግስት የተበደልንም ያልተበደልንም ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት፡፡
በግብጽ ያየናቸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የሆኑ ኢትዮጵያውን በህግ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ መገንጠል ከፈለጉ ግን አሁን በግላቸው ሊገነጠሉ መብታቸው ይመስለኛል፡፡ ሰላሌን ለመገንጠል ማሰባቸውን የአባቴ ዘመዶች ቢሰሙ ግን “ጉዲ ሰዲ!” ይሉ ነበር፡፡ ወለጋን ለመገንጠል ቢነሳሱ የእናቴ ዘመዶች “ዴሚ አሲ” (በአራዳ ቋንቋ “ላጥ በሉ”) ይሏቸዋል እንጂ ጆሮ አይሰጧቸውም ባሌ፣ አርሲ፣ ጅማ እና ከሚሴ ሁሉም ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለህም ከሚሉት “ሲቀሉ” (ልረድህ) ቢሉት ይመርጣል፡፡ ኦሮሚያ ኢትዮጵያ አይደለችም የሚለው ቅዠት የህዝብ ጥያቄ ቢሆን ይሄኛው ኦነግ አርባ አመት መታገል ሳያስፈልገው ህዝቡ በአርባ ቀን እውን ያደርገው ነበር፡፡
ለማንኛውም፤
የአባይን ግድብ መቃወም ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የአባይን ግድብ ለሌላ ሀገር ጥቅም ሲባል መቃወም ግን፤ ኦሮሞውም፣ አማራውም፣ ደቡቤውም፣ ትግራዩም፣ ጋምቤላውም፣ ቤንሻንጉሉም፣ ሃረሪውም፣ አፋሩም፣ እኔውም የምንሞትለት ጉዳይ ነው፡፡
ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽም ያስደፈረሽም ይውደም!

No comments:

Post a Comment