ዛሬ ደግሞ…
ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም
ለፍቅር መተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለጠብም መተዋወቅ ያስፈልጋል፤ የተሟላ መረጃ ቢኖረን የጥንት ታሪክ እየጠቀስን ሰዎችን ለጦርነት እንቀሰቅስም ነበር ብዬ አምናለሁ፤ ስለዚህም አንዳንድ አስፈላጊ መረጃዎችን ላቅርብ፤ —
1. የግብጽ የጦር ኃይል በዓለም አሥረኛ ነው፣ በአፍሪካና በመሀከለኛው ምሥራቅ የሚወዳደረው የለም፤ አንድ ሚልዮን ተኩል ያህል የጦር ኃይል አለው፤ በዓየር ኃይልም ከዓለም አሥራ አራተኛ ነው፤ በታንክ ብዛት አራተኛ ነው፤ በባሕር ኃይል ሰባተኛ ነው፤ በጦር በጀት አርባ ሦስተኛ ነው፤
2. በኢትዮጵያ ዙሪያ ጂቡቲ፣ ሶማልያ፣ ሱዳን የአረብ ማኅበር አባሎች በመሆናቸው ለግብጽ ማኅበረተኞች ናቸው፤ በወያኔ ፈቃድ የተገፋችው ኤርትራም የዚሁ ማኅበር ታዛቢ አባል ነች፤ ከቀይ ባሕር ማዶ ያሉት አገሮች ሁሉ ሀብታሙንና ኃይለኛውን ሳኡዲ አረብያንም ጨምሮ የግብጽ ማኅበርተኞች ናቸው፤ በዚህ ሁሉ መሀከል የተከታተፈች ኢትዮጵያ ብቻዋን ነች፤
3. የቤንዚን ሀብትና ከሀብቱም ጋር የሚገኘውን ወዳጅና ጡንቻ አንርሳ፤
ይህ ማስታወሻ ለማስፈራራት አይደለም፤ ማስፈራራትን አላውቅበትም፤ እንዲያውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ‹‹አትፍሩ›› ብሏቸዋል ተብዬ ተከስሼ ታስሬአለሁ፤ ስለዚህ አላስፈራራም፤ ጦርነት ከመጣብን ልናስቀረው እንሞክር፤ ሌላው ቢቀር እንድንዘጋጅ ጊዜ እናገኛለን፤ ገፍቶ ከመጣ ግን እንቋቋመዋለን፤ ለጦርነት አንቸኩል፤ ለኤርትራም ጊዜ ተናግሬ ነበር፤ የሰማኝ የለም፤ ጥጋብ ላይ ያሉ የሚርባቸው ዝና ነው፤ የሚያገኙት ግን ውርደትን ነው፡፡
No comments:
Post a Comment