Translate

Thursday, April 9, 2015

“ምስክር ፈላጊው ችሎት” – 27ተኛ የፍርድ ቤት ውሎ (ዞን 9)

በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ከጎንዬሽ ጉዳዬች ውጪ ለ25ተኛ ጊዜ (በአጠቃላይ ለ27ተኛ ጊዜ) የተሰየመው ችሎት ዛሬም የደረጃ ምስክሮችን ሲያሰማ ውሏል፡። ከሳምነትት በፌት የተሰየመው ችሎት አቃቤ ህግ 41 ምስክሮች አሉኝ ነገር ግን ላገኛቸው ስላልቻልኩ ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ቆይተው ተጨማሪ ማፈላለጊያ ጊዜ ይሰጠኝ በማለት ጠይቆ ለዛሬ የተቀጠረ ቢሆንም ዛሬም “የሽብር ተግባሩ “ ዋና ምስክሮች ባለመገኘታቸው ፍተሻ ላይ ተገኝተናል ያሉ አምስት ምስክሮች ተሰምተዋል፡። የምስክሮቸን ቁጥርም 35 ነው በማለት ቀይሮታል፡፡Ethiopian arrested zone 9 bloggers
ባለፈው የተሰሙት 13 ምስክሮች ሲሆኑ በዛሬው ችሎት ባልተካደ ነገር ላይ ሲመሰክሩ የዋሉት የደረጃ ምስክሮች
14ተኛ ምስክር ተወዳጅ ኃ/ማርያም ይባላሉ፡፡ እድሜያቸው 34 ሲሆን የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡ የምስክርነት ቃላቸውም ‹‹የመጣሁበት ኬዝ ግንቦት 7/2006 ዓ.ም በምኖርበት ልደታ 5ኛ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ታዛቢ ሁነኝ ብሎ ጠይቆኝ በታዛቢነት ያየሁትን ለመመስከር ነው፡፡ ማህሌት ጤና ጥበቃ ሚ/ር ትሰራለች መሰለኝ፣ እዚያ መስሪያ ቤት ፖሊስ ማህሌት ኮምፒውተርና ጠረጴዛ ላይ ያለውን ሲበረብር አይቻለሁ፡፡ መንግስት መስሪያ ቤት የምትጠቀምበት ኮምፒውተር ላይ የተገኙ ሰነዶች ላይ ማህሌት ስትፈርም እኛ ታዛቢዎችም ፈርመናል፡፡
የፈረምነው ግንቦት 7/2007 ዓ.ም ነበር፡፡ የገጹን ብዛት አሁን አላስታውስም፤ ወደ 40 ገጽ ይሆናል፡፡ እንግሊዝኛና አማርኛ ጽሁፎች አሉበት፡፡ የተወሰነ የፖለቲካ ይዘት የነበረው አለ፡፡ የፖለቲካ ፕሮግራም ማኒፌስቶ አይቻለሁ፡፡ ፖሊስ ማህሌትን ሲጠይቃት ከኦነግ የወጣው የሌንጮ ፓርቲ ፕሮግራም ነው ብላለች፡፡ ጎስፕ ንግግሮችም አሉ›› ብሏል፡፡ ዳኛው ጎሲፕ በአማርኛ ምንድነው ሲላቸው ምስክሩ ‹‹ሽሙጥ ንግግር ነው›› ብለው መልሰዋል፡፡ ምስክሩ የተገኙ ሰነዶች ላይ ፌደራል ፖሊስ ሄደው እንደፈረሙና ይሄን ያደረጉትም ግንቦት 9/2006 ዓ.ም ነው ብለዋል፡
15ተኛ ምስክር ፀሐይ ብርሃኔ እድሜያቸው 33 የሆኑ የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡ የምስክርነት ቃላቸውም ‹‹ግንቦት 7/2006 ዓ.ም ከቀኑ 4፡00 ፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አሳይቶ ቢሮ ሲፈተሽ ታዘብ ተብዬ ተገኝቼ ነበር፡፡ ሲ.ዲ እና ዲክሜንት ሲወሰድ አይቻለሁ፡፡ ከዚያ ፖሊስ በ9/2006 ዓ.ም ሄጄ በሶፍት ኮፒ የነበሩት ሰነዶች ፕሪንት ተደርገው ማህሌት የፈረመችባቸው ላይ ፈርሜያለሁ፡፡ በእንግሊዝኛና አማርኛ የተጻፉ ናቸው፡፡ በግምት ወደ 40 ገጽ ይሆናል፡፡ አብዛኛው የፖለቲካ ነክ ጽሑፎች ናቸው፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽሑፎች አሉበት፡፡ ያየናቸው መረጃዎች ከእሷ ኮምፒውተር ላይ ስለመገኘታቸው አይተን ፈርመናል፡፡››
ለእኒህ ምስክር መስቀለኛ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር፡፡
የጠበቆቹ መስቀለኛ ጥያቄ፡- ሲዲውን ማን እንዳመጣው
ታውቃለህ…ውስጡ ምን ነበረበት…
የምስክሩ መልስ፡- እኛ ራሳችን ቼክ አድርገናል፤ ባዶ ሲ.ዲ ነው፡፡
ጥያቄ፡- የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብለሃል….ስንት ናቸው
መልስ፡- አንድ ብቻ አይደሉም
ጥያቄ፡- የተለያዩ ፓርቲዎች ሰነዶች ብለዋል እኮ….እነዚህ ላይ ሁሉ ፈርመዋል
መልስ፡- አሁን በትክክል የማስታውሰው የሌንጮ ፓርቲ ሰነድ ላይ መፈረሜን ነው፡፡ ሌሎች ላይ አልፈረምኩም፡፡
(አንድ ሰነድ ቀርቦላቸው ፊርማው የእሳቸው ስለመሆኑ እንዲለዩ ተደርገው የእሳቸው መሆኑን አረጋግጠው የፈረሙበትን ሰነድ ይዘት ግን እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡)
ፍርድ ቤቱ ‹‹40 ገጽ ማየትህን ተናግረሃል፤ 40 ገጽ ላይ ፍርመሃል፣ ይዘቱንስ ታውቃለህ›› ብሎ ጠይቋቸው ምስክሩ ‹‹እያንዳንዱ ሰነድ ላይ ፍረሜያለሁ፤ ግን አላነበብኩትም፡፡ ክፍት የስራ ማስታወቂያ የሚል ግን አይቻለሁ›› ብለዋል፡፡ በተለየ የትኛውን ነው ያነበብከው ለተባሉት ደግሞ ‹‹አሁን አላስታውስም፤ የሌንጮ ሰነድ ላይ ፈርሜያለሁ፡፡ ማህሌት ፖሊስ ሲጠይቃት ሌንጮ የራሳቸውን አዲስ ፓርቲ እያቋቋሙ እንደሆነ ስትናገር ሰምቻለሁ›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
16ተኛ ምስክር ዳግማዊ እንዳለ 25 ዓመታቸው ሲሆን የመንግስት ሰራተኛና የአ.አ ከተማ የካ ክ/ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በ5ኛ ተከሳሽ አጥናፍ ላይ ለመመስከር እንደመጡ ተናግረው የአባቱን ስም አላስታውስም ብለዋል፡፡
“ሚያዝያ 17/2006 ዓ.ም 11፡00 ገደማ ከስራ ወደ ቤት ስሄድ 22 ትራፊክ ፖሊስ ጀርባ ፌደራል ፖሊስ የፍርድ ቤት ወረቀት አሳይቶ ታዛቢ ሁነኝ ብሎኝ ተገኝቻለሁ፡፡ አጥናፍ ቤት ገብተን ሰነዶች ሲገኙ አይቻለሁ፡፡ ፍላሽ፣ ሴኪዩሪቲ ኢን ኤ ቦክስ የሚል መጽሐፍ፣ ሲ.ዲ ተገኝተዋል፡፡ ሌሎች ታዛቢዎችም ነበሩ፡፡ ሰነዶቹ ላይ አጥናፍ ሲፈርም እኛም ፈርመናል፡፡›› ብለዋል፡፡
17ኛ ምስክር፡- ሳምሶን ሲሳይ ይባላሉ፤ 29 ዓመታቸው ሲሆን በግል ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ አድራሻቸው አ.አ የካ ክ/ከተማ ነው፡፡ አጥናፍ ላይ ለመመስከር መምጣታቸውን ተናግረዋል ‹‹ሚያዝያ 17/2006 ዓ.ም 11፡00 አካባቢ ትራፊክ ጽ/ቤት ጀርባ ፖሊሶች ታዘብልን ስላሉኝ ታዝቤያለሁ፡፡ ሲ.ዲ፣ ፍላሽ፣ የተለያዩ ዶክሜንቶች፣ ላፕቶፕ፣ ማስታወሻ ደብተሮች መገኘታቸውን አይቻለሁ፡፡ በዝርዝር አላስታውስም፡፡ ግን 150 አካባቢ መጽሐፍ ቆጥረናል፡፡ ፋክት መጽሔት ተገኝቷል፡፡ መጽሐፎቹ በእንግሊዝኛና አማርኛ የተጻፉ ናቸው፡፡ አጥናፍ የፈረመባቸው ላይ እኛም ፈርመናል፡፡›› ብለዋል፡፡
18ኛ ምስክር፡- እኒህ ምስክር ደግሞ በረከት ብርሃኔ የሚባሉ ሲሆን እድሜያው 29 ነው፡፡ በግል ስራ ላይ የተሰማሩና የአ.አ አራዳ ክ/ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ 6ኛ ተከሳሽ ዘላለም ላይ ለመመስከር እንደመጡ በመግለጽ ዘላለምን በአካል ለይተው አሳይተዋል፡፡ ‹‹ግንቦት 16/2006 ዓ.ም ማዕከላዊ ለግል ጉዳይ ሄጄ ፖሊስ በጠየቀኝ መሰረት ታዝቤያለሁ፡፡ ሰነዶች ልናይ ስለሆነ እይልን አሉኝ፡፡ እሺ ብዬ ወደ ቢሮ ገባሁ፡፡ ከቀኑ 8፡00 ይሆናል፡፡ እኛ ከገባን በኋላ ዘላለም ተጠርቶ መጣ፡፡ ላፕቶፑን ራሱ ፓስወርዱን ከፈተው፡፡ ከዚያ ከላፕቶፑ የወጡ ሰነዶች ፕሪንት ተደርገው ፈረምንባቸው፡፡ እንግሊዝኛም አማርኛም ነበር፡፡ ደሞ ምሳ ተጋብዘናል፡፡ ዘላለም ብላ ሲባል አልበላም አለ፡፡ አሁን ሰነዶቹ ምን እንደሆኑ አላውቅም፡፡ ዘላለም የፈረመበት ላይ ነው እኔ የፈረምኩት፡፡ ለማንበብ ግን ጊዜ አልነበረኝም፡፡ ስለዚህ ይዘቱን አላውቀውም፤ እሱ የፈረመበት ስለሆነ ብቻ ፈርሜያለሁ፡፡ አልፈርምም ያለው ሰነድ አልነበረም፡፡ ሌሎች ታዛቢዎችም ነበሩ፡፡ እነሱም ፈርመዋል›› ብለዋል፡፡
ምስክሮች ከመሰማታቸው አስቀድሞ አቃቤ ህግ ባለፈው የተሰጠው ቀጠሮ አጭር በመሆኑ ሌሎቹን ምሰክሮች ለማግኘት ረዘም ያለ ጊዜ ቀጠሮ አንዲሰጠው አንዲሁም አስመዝግቤያለው ካላቸው ሲዲዊች ውስጥ 7ቱ አንዲሰሙለት የጠየቀ ሲሆን የቀሩት ግን ሲዲውን የያዘው ባለሞያ ከአገር ውጪ በመሆኑ ማቅረብ አልቻልንም ብሏል፡፡ የተከሳሾች ጠበቆች ተከሳሾች ከታሰሩ አንድ አመት ሊሞላ ጥቂት አንደቀረ ምስክሮቸን ማዘጋጀት ቀደም ብሎ መሰራት የነበረበት የአቃቤ ህግ ስራ መሆኑን ነገር ግን በተደጋጋሚ እድል እየተሰጠው አንዳልተጠቀመበት በመጥቀስ ዛሬ የቀረቡት የሰው ምስክሮች መጨረሻ አንዲሆኑ እና የቀሩ ማስረጃዎቸን ለመስማት አጭር ቀጠሮ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ “ፍርድ ቤቱ” የአቃቤ ህግን ክርክር በመደገፍ የሚቀጥለውን ቀጠሮ ከአንድ ወር በላይ በማራዘም ግንቦት 18-21 2007 አም ድረስ እንዲሆን አንዲሁም የሲዲ ማስረጃዎቹ በወቅቱ ተሟልተው አንዲቀርቡና ቀሪ ምስክሮቹም በዚያው ቀን ወስኖ ችሎቱ ተጠናቋል፡፡
የዞን9 ማስታወሻ
አንደሁልጊዜው ሁሉ የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ክስ ፓለቲካዊ ነው ያልተሰራ ወንጀል ምስክር አይገኝለትምና ፈጣን ፍትህን የማግኘት መብትን መቀለጃ ላደረገው ፍርድ ቤትም ሆነ የመንግስት ስራ አስፈጻሚ ጓደኞቻችንን ለመፍታት አሁንም ጊዜው አልረፈደም የሚለውን መልእክት ለማስተላለፍ አንወዳለን፡፡

No comments:

Post a Comment