Translate

Thursday, April 30, 2015

“ሞት የዘመኑ ዕለት እንጅ የመነኑ ዕለት አይደለም” (መነገር ያለበት ቁጥር 8)

ቤልጅግ አሊ – ከፍራንክፈርት

“ከመሸ ተነሳሁ ከተፈታ በሬ፣
እደርስ አይመስለኝም ከእንግዲህ ሃገሬ።”

አገኘሁ እንግዳ
ጀርመን ፍራንክፈርት በሚገኘው የመድኃኒዓለም ቤተክርስትያን ውስጥ በሊቢያ ለተሰው ዜጎቻችን ጸሎተ-ፍትሃትና ከዛም ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ ተገኝቼ ነበር። በደቡብ አፍሪካም ይሁን በሊቢያ በደረሰው ችግር ሁላችንም ሃዘን ገብቶናል። በዚህ ግፍ እንባ ያነባንም አለን። ከልባችንም ያዘንን ብዙ ነን። ቄሱ ትምህርት ሲሰጡ እነዚህ ለሃይማኖታቸው ሲሉ በወጣትነት የሞትን ጽዋ የተቀበሉ ሰማዕታት ትልቅ በረከት አግኝተውበታል ነው ያሉት። አዎ ለእምነት መሞት ትልቅ በረከት ነው። ጥንትም ለአመኑበት መሞት ታሪክ መስራት ነው፤ ሕይወትን በሌላ ፈርጅ መቀጠል ነው፤ ዳግም ትንሳዔ፣ ዳግም ልደት ነው። አሁንም ቢሆን የተቀየረ ነገር የለም።
ቤተክርስትያን ውስጥ ሆኜ ጸሎተ-ፍትሃቱን በመከታተል ላይ እያለሁ ለማነው የምናለቀሰው? ለምንስ ነው የምንላቀሰው? የሚለው ጥያቄ አዕምሮዬን አጣበበው። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ችግሩ ባለ ብዙ ፈርጅ ነውና እያንዳንዳችን የችግሩን ምንጭ ማሰባችን አይቀርም። የስደቱ ምንጭ ሃገራችን ውስጥ ያለው ቅጥ ያጣ የዘረኝነት ሥርዓት መሆኑ ግልጽ ነው። ምንም እንኳን የምናለቅስው አሁን በወገኖቻቸን ላይ በደረሰው ችግር ቢሆንም የችግሩ መንስዔ ግን ሃገራችን ውስጥ ያለው አገዛዝ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም። ለዚህ አስከፊ ሥርዓት መቀጠል የእኛም አስተዋፅዖ ትንሽ አይደለም። እንዲውም ከፍተኛው ቦታ ሊይዝ ይችላል።

ሁኔታውን ልብ ብለን ስናጤነው ለዚህ ሁሉ መንስዔ የሆነውን ወያኔ እንዳይወድቅ በተለያየ ምክንያት አቅፈን ደግፈን የያዝነው እኛው ነን ማለት ይቻላል ። የሕዝብ ሰቆቃና ስቃይ ያራዘምነው እኛው፤ የስደት አዙሪት ያባዛነው እኛው ነን። ውል የለሾች፣ ማተባችንን የበጠስነው እኛው መሆናችንን ሳስበው ከተለቀሰ መለቀስ ያለበትማ ለእኛ ነው እንጂ ለተሰውት መሆን የለበትም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። እነርሱማ ለእምነታቸው ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል።
እውነትም መለቀስ ያለበት ለእኛ ነው። የግፍን ዓይነት ለምንመርጠው፣ ሰው በወገንተኝነት እየለየን ለአንዱ ለምናለቅስ፣ ለሌላው ጆሮ ዳባ ለምንለው፤ ለባለጊዜ ጉልበተኛ ለምንሰግደው፤ በዘር፣ በሃይማኖት ለምንከፋፈለው፤ ራሳችን ያቋቋምነውን (ቤተክርስትያን፣ ማህበር፣ የፖለቲካ ድርጅት፣ የሲቪክ ድርጅት . . . ወዘተ) ራሳችን ለምናፈርሰው፤ አቋማችንን በየወቅቱ ለምንለዋውጠው፤ የሃዘናችን ዳርቻ ከፌስ ቡክ ዋይታ ለማይዘለው፤ የሃይማኖታችን ብጽእና ሻማ ከማብራት አልፎ ወደ ላይ ለማያርገው፤ የምንኩስና ቆባችንን በፖለቲካ እራፊ ለምንጥፈው፣ ሽምግልናችን የእንጨት ሽበት ለሆነብን፤ መክረን ለማንመልሰው፣ ዘክረን ለማንቀልሰው፣ ላለው እምናሸረግድ፣ ለሌለው ፊት እምንነሳ፤ ሞልቶ ለተረፈው የምንሰጥ፤ ድሃውን ለምናሽጓጥጠው፤ የደሃን መጠለያ ጎጆ እያፈረስን መሬት ለምንመራው፤ ማልቀስማ ለእኛ ነው፣ አለን እያልን ለጠፋነው፣ በቁማችን ለሞትነው፤ በእኩይ ምግባራችን ገልሙተን ባህሪያችን ለሸተተው፣ ቀባሪ ዕድር አጥተን እንጂ ከሞትንማ’ ለቆየነው፣ ማልቀስ ለኛ ነው።
የለም! የለም! ዛሬ ለእኛ ነው መለቀስ ያለበት። ሃዘናችን ከቫይበር ስዕል ፣ ከፌስ ቡክ RIP ያለፈ ቁም ነገር ለማይፈይደው፤ ምን አልባትም ለአንድ ቀን “እኔም እነርሱን ነኝ“ ከሚል መፈክር በላይ ለማንሄድ፤ ነገን ለኛ ለምናልም ጉድጓዳችን የተማሰ አዛውንቶች፤ በድሃው አናት ላይ ግራውንድ ፕላስ . . . ቤት ለመስራት ለምንስገበገብው። በሰጥቶ መቀበል ቀመር በደራው የወያኔ ገበያ በዜጎች ሕይወት በዜጎች መብት ለምንነግድ፤ ለምናተርፍ ለእኛ ነው መለቀስ ያለበት።
ጎበዝ! ይለቀስ እንጂ ለእኛ በዘር፣ በድርጅት ተከፋፍለን መነጋገር ላቆምነው፤ የድርጅት መሪ ሆነን በሥልጣን ጥም ጠኔ ለምናጣጥረው፤ ከሕዝብ የተዋጣ ገንዘብ ለምንመዘብረው፤ ትላንት ተቃዋሚ ዛሬ የወያኔ ጋሻ ጃግሬ፤ ትላንት ዓለም አቀፋዊ ዛሬ ጎጠኛ ለሆነው፤ ትላንት ኮምኒስት ነን ብለን ካፒታሊዝምን ያብጠለጠልን ፣ ዛሬ ካፒታሊዝምን ወደን ሶሻሊዝምን የምንረግም፣ ትላንት የተቃዋሚ ሊጋባ ዛሬ የወያኔ አልባሽ አጉራሽ ለሆነው። መለቀስ ያለበትማ ለእኛው፤ ለገበያ ኢኮኖሚ ልማታዊ ባለሃብቶች፣ ፔንዱለሞች፤ አንዴ እዚህ አንዴ እዚያ ለምንዋትት፣ የሁለት ዜጋ ሰዎች፣ በሁለት ካራ በላዎች፣ ማተብ የለሽ ክርስትያኖች፣ ሶላት ለማንሰግድ ሼኮች። ደረት ይመታልን ለእኛ።
ለእኛ ይለቀስ እንጂ! ትላንት አማራዎች ከየቦታው ሲፈናቀሉ አይተን እንዳላየን ለሆነው፤ ስንት የፖለቲካ እስረኞች ቤተሰቦች ሲበተኑ ሰምተን ላለመስማት ለጣርነው፤ በ97 ምርጫ የተገደሉትን ወጣቶች ለረሳነው፤ ወያኔና ሻብዕያ ወጣቱን በጅምላ ለማይረባ ጦርነት ሲማግዱ ለደገፍነው፤ ከክልላችን ይውጡ እያልን ያዙን ልቀቁን ለምንለው፤ ማልቀስ ለኛ ነው በቁማችን ለሞትነው። እንጂማ በሃይማኖቱ ጠንቶ! በዜግነቱ ኮርቶ! ታሪክ ሰርቶ፣ ስም ተክቶ፣ ለሞተው ጀግና ወገንማ ምን ብለን እናለቅሳለን። ለዚህ መሰሉ የሃገር ክብር መግለጫ፣ ለዜግነት ኩራት ለተከፈለ መስዋዕትነት ለማውራትም ይሁን ለማልቀስ ከቶ ስንቶቻችን የሞራል ብቃት ይኖረን ይሆን?
“ሞት የዘመኑ ዕለት እንጅ የመነኑ ዕለት አይደለም“።
ከውጭ ለቃቅመንና ተበድረን በሄድነው ገንዘብ ሃገርቤት ሄደን አሽሼ ገዳሜ ለምንለው፤ በአስረሽ ምችው ዋልጌነት መጥፎ ባሕልን ለምናስፋፋው፤ በማስመሰል ስብእና የድሆችን ቀልብ እያማለልን ስደትን ለምናስፋፋው፤ ጸረ ዘረኝነት ትግልን ለምናጥላላው፤ በየመሸታ ቤቱ በጨበጥነው የድራፍት ብርጭቆ ስፍር የሀገር ልማትን ለምንለካ፣ አዳዲስ የተገነቡትን ሕንጻዎች እንጅ በህንጻው ስር የወደቁትን አዳዲስ ድሃዎች ለማናስተውል፤ የተሰራውን ቀለበት መንገድ ስናደንቅ ጫማ የሌለውን ምስኪን ረግጠን ላለፍነው፤ በተቀዳደዱ እራፊ ጨርቆች ውስጥ ሾልኮ የሚታየውን አቧራ ጸሐይና ቁር የጠገበን ያገር ልጅ ገላ ያላሳሰበን፤ የውስኪውን ጣዕም እንጅ ጥሪኝ ውሃ የሌለውን ወገን ያላስተዋልን፤ የክትፎውን ጣዕም፣ የጥሬውን ስጋ ጮማነት እንጅ . . . እኛ ጠግበን ከጣልነው የእጅ ማበሻ ሶፍት ውስጥ ፈልቅቆ ከትራፊያችን አጥንት ጋር የሚታገለውን ታዳጊ ወጣት የረሳን፤ በሚቀያየር የቀለም መብራት ደንሰን ሻማ መግዥያ የሌለውን ያልተመለከትን፤ አንድ የዕለት ጉርሻ ለመግዛት ገንዘብ ያጣውን ለረሳነው፤ የሃገርን እድገት በሃብታሞች የብር ጥራዝ ለለወጥነው፣ የሆቴሎቹን ማማር፣ የኮረዳዎችን ውበት፣ የሪዞርቶችን ምቾት በየመንገዱ ለምንቆጥረው። ለቅሶ የሚገባው ለእኛ ነው ልማታዊ ቱሪስቶች ለሆነው።
አሁንማ ተራው የእኛ ይሁን እንጂ! ለእኛ ይለቀስ እንጂ፣ የቁም ተዝካራችንን እናውጣ እንጂ፣ የምራዕብውያንን የራስ ጥቅም አሳዳጅነት እያወቅን በየኤምባሲው፣ በስቴት ዲፓርትመንት፣ ነጻነታቸንን ይቸሩናል ብለን 23 ዓመታት ሙሉ ለሰገድነው፤ በሃገራቸን ሕዝብ እምነታችንን ላጣነው፤ ሳንታገል ሳንሰዋ ድል እንደ ኬክ በሳህን ከምዕራብውያን እንዲታደለን ለምንቋምጠው፣ በጣት የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አስከትለን በአንድ መሪ አምላኪነት በድርጅት ስም መግለጫ እያወጣን በብዙሃን ትግል ለምንነግደው፤ ሃገርንና ሕዝብን ለስልጣን ጥም በጥቅም ለቀየርነው። መለቀስስ ያለበት ለኛ ነው። በቁም መሞት ከዚህ በላይ ምን አለና!?
ኧረ ሙሾ ደርድሩልን ለእኛ! ከሕዝብ የተዋጣን ገንዘብ ለምንበላው፤ ለጥቅም ስንል ስንት አባላት የተሰውበትን ትግልና ድርጅት እያመከንን ላለነው፤ የውሸትን ፕሮፖጋንዳ እየደሰኮርን ለደጋፊዎቻችን መደለያ ለምናደርገው፤ በድርጅትና በትግል ስም ገንዘብ ለምነን ለግል ጥቅም ለምናውለው፤ ማልቀስ ለኛ ነው ጥሩ እድር አጥተን ላልተቀበርነው ።
ወገን አልቅሱ ለእኛ የስምንተኛው ሺህ የጥፋት ምልክቶች ለሆነው፣ እንደ ቄስ መስፍን (የሙኒኩ) ከህዝብ የተዋጣ 150 ሽህ ዩሮ በላይ የደብሩን ገንዘብ አጥፍቶ “ቀድሼ እከፍላለሁ“ እንዳለዉ በእግዚአብሔርም በዜጋም ለምንቀልድ፣ እንደ(ፕሮቴስታንቱ) ፓስተር ተከስተ የእንስትን ራቁት ፎቶ በስልክ እየበተን ለምንዝናና፣ እንደ አባ ግርማ (የለንደኑ) በሕዝብ ገንዘብ የተገዛን ቤተ-እግዚአብሔር ለግል ጥቅምና ለሹመት ስንል ለዓመታት ለዘጋን፣ ማልቀስ ለኛ ነው እንጅ የስምንተኛው ሺህ ምልክቶች ለሆን፣ ቀብራችን ለተማሰ ግብዓተ መሬታችንን ለምንጠብቅ።
እናልቅስ ከተባለ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ እናልቅስ! ካልሆነ ግን ለራሳችን እናልቅስ!
ሰሞኑን አዲስ አበባ ለተደበደቡት እናልቅስ፤ የወያኔ ቅልብ ለወንድሞቻቸው ሐዘን የወጡትን ሲደበድቡ እኛም እንቢ እንበል፤ በደቡብ አፍርካ የተደረገውን ግፍ እንዳወገዝን የሃገራችንን አፓርታይድ የክልል አገዛዝንን እናፍርስ፤ ዛሬም ለእነ እስክንድር ቤተሰቦች እናልቅስ ፣ ለነተመስገንም ቤተሰቦች እናልቅስ ፣ ከአንዳርጋቸው ጽጌ ልጆች ጋር አብረን እንነሳ . . . ወዘተ ፣ ለሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንታገል። ለፍትህ እንቁም፣ ለዜጎች መብት እንጋደል፣ ለዲሞክራሲ እንትጋ፣ ለአንድነት በአንድነት እንቁም። በሉ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ አብረን እናልቅስ።
መታገላችን ካልቀረ፣ ማልቀሳችን ካልቀረ የግፍ ሁሉ ግፍ፣ የስደት ሁሉ ስደት ምክንያት የሆነውን ወያኔን ለማስወገድ፣ ዘረኝነትን፣ ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን የሃብት ክምችት፣ ጎጠኝነትን፣ የስርዓት ንቅዘትን፣ ፅንፈኝነትን፣ ብሄራዊ ውርደትን፣ የሉዓላዊነት መደፈርን፣ የአንድነታችን መሸርሸርን ከምንጩ ለማንጠፍ እንታገል። የስርዓቱን ሰለባዎችን ለመታደግ፣ የወገንን ውርደት እንዲያከትም፣ እንነሳ። ሳንከፋፈል ስር የሰደደውን ቀንደኛ የሃገር የሕዝብ ጠላት ወያኔን ለማስወገድ አብረን እንታገል፣ አብረን ተግተን ከልብ እናልቅስ፤ ያኔ ስደትም ይቆማል ሰቆቃችንም ያከትማል፣ እኛም ማልቀሳችንን እናቆማለን ።
ስለ ሰማዕታቱ የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ።
beljig.ali@gmail.com
ፍራንክፈርት

No comments:

Post a Comment