Translate

Wednesday, April 22, 2015

የምትሞትለት ሰው ከሌለህ አንተ ሞተሃል ( ሄኖክ የሺጥላ )

የምትሞትለት ሰው ከሌለህ አንተ ሞተሃል ( ሄኖክ የሺጥላ )
የምትሞትለት ሰው ከሌለ ለምን ትኖራለህ ። ለሰው እና ለነጻነት ሲሉ መሞት ሁሌም ክብር ነው ። ይህንን ሶቅራጥስ አድርጎታል ፣ ክርስቶስ አድርጎታል ፣ ይስሐቅ ለጥቂት የተረፈው ከሰማይ በወረደለት በግ እንጂ እሱም አባቱን ለመሰማት ሲል ለጥቂት አድርጎት ነበር ። ቴዎድሮስ አድርጎታል ፣ አሰፋ ማሩ አድርጎታል ፣ አስራት ወልደየስ አድርጎታል ። አሳፋሪው ነገር
ለሰው ሲሉ መሞት ሳይሆን ፣ ለመኖር ሲሉ ሰው መግደል ነው ። ለሆድ ሲሉ መግደል ብርቅ አይደለም ፣ ሰው ይበላ ዘንድ መሞት ግን ተአምር ነው ! ሞትን አስፈሪ ያደረገው ፣ ነብስን የተሸከማት ኗሪው ነው ። ለጀግና ሰው ፣ የሌሎች መኖር ከሱ መኖር ለሚበልጥበት ሰው ፣ ሞት ገለባ ነው ።
በባህላችንም ሆነ በማንኛውም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የሚታወሰው አንዲት ስንጥር ሳይነካው ፣ የግንብ ውስጥ ስዳሃርታ ( የግቢ ውስጥ ቡድሃ ) ሆኖ የኖረና የሞተ ሰው አይደለም ፣ ታሪክ ለሆዳቸው ሲሉ ህዝባቸውን የጨቆኑ ፣ ህሊናቸውን የሸጡ ፣ ሀገራቸውን ያዋረዱ ፣ ሆድ አደሮች መዘክር አይደለም ። ይልቁንም ታሪክ ከነዚህ ሆድ አደሮች ጋ ታግለው ፣ ወጥተው ፣ ወርደው ፣ ከስተው ፣ ጠቁረው ፣ አይሆኑ ሆነው ፣ ከሰውነት ጎዳና ወጥተው ፣ ለራሳቸው አንዳችም ( ቅንጣት ) ታህል ቅሪት ሳያካብቱ ይወታቸውን ለሰው ልጅ ነጻነት ፣ ለሀገራቸው አንድነት ፣ ለህዝባቸው ክብር አሣልፈው የሰጡ ባለታሪኮች አምድ ነው ።
እንደ ጥያቄ የምትሞትለት ከሌለ ለምን ትኖራለህ ? የምታየው በሙሉ የሚያስፈራህ ፣ የምያንቀጠቅጥህ ፣ አንገትህን የምያስደፍው ከሆነ ፣ እወቀው መኖር ካቆምክ ቆይተሃል ። ሰውነት የሚለካው በቁሳዊ በረከትህ ፣ ወይም በሥጋ ክብደትህ፣ ወይም በዓለማዊ እውቀትህ አይደለም ። ሆኖም አያውቅም ። እንኳንስ በዓለማዊ በመንፈሳዊው እውቀትህ ሰውነት አይለካም ። የሰውነት መለኪያው ፣ ሰው ነኝ ባልከው ማንነትህ ላይ ያካበትከው እውነትህ ነው ፣ የተሸከምከው ኃላፊነት እና የተገበርከው መልካም ግብር ነው የሰውነት መለኪያው ። የጀግንነት መለኪያው 17 ዓመት ጫካ መቆየት ፣ ደርግን መደምሰስ አይደለም ። የጀግንነት መለኪያው ፣ ሕይወት ለመልካም ነገር አጋጣሚ በሰጠቻት ሕይወትህ ውስጥ ምን ያህል ቁም ነገር ሰራህባት የሚለው ነው ። 

የጀግንነት መለኪያው አልእቅት በልቶ ፣ በጊንጥ ተነክሶ ፣ በዘንዶ ተውጦ ፣ በእባብ ተነድፎ ፣ በሞርታር ተቆርጦ ከተማ ከደረሱ በሗላ ፣ ይህንን የመከራ ታሪክ በቴሌቪዥን መስኮት እያብለጨለጩ ፣ ወይም እንደ አብሪ ጥይት ብልጭ እያደረጉ ሕዝብ ማስፈራራት አይደለም ፣ ጀግንነት ዋጋ የሚኖረው ፣ በጊንጥ መነከሱም ሆነ በእባብ መነደፉ ታሪክ የሚሆነው ፣ ያ ሁሉ መከራ ለውስኪ መራጫና ፣ ማን አለብኝ አምባ ገነን ስርዓት ለመመስረት ሳይሆን ለሰው ልጆች ክብር ሲባል የተደረገ እንደሆነ ብቻ ነው ። ጀግና ባንደበቱ ስለ ጀግንነቱ አያወራም ፣ ጀግና ጠላቱን በመጣል ብቻ ሳይሆን ጠላቱን በማስተማር የሚታወቅ ነው ። እኛ ሀገር የማየው ጀግንነትን ሳይሆን ፍርሃትን ነው ። ፈርቶ ጫካ የገባ ቡድን ፣ እንደፈራ ከተማ ደረሰ ፣ አሁንም እንደፈራ ይኖራል ። የፍርሃት ምልክቱ ደሞ ምክንያት አልባ ቁጠኝነት ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ ሁሉንም ነገር በጉልበት ለመዳኘት ማሰብ ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ አረጋዊ እና ህጻንን አንድ ላይ ጨፍልቆ መቅጣት ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ ስርዓተ አልበኝነት ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ ከመጠን ያለፈ መታበይ ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱን ልጣጩንም ፣ ፈሬውንም ፣ ገለባውንም ማግበስበስ ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ ፣ የተናገረን እና የጻፈን አሸባሪ ብሎ ማሰር ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ ፣ ከ ሽሮ መነገጃ እስከ ነዳጅ መሸጫውን ባንድ ቡድን መቆጣጠር ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ ሥስታምነት ፣ የፍርሃት ምልክቱ ራስ ወዳድነት ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ አእምሮን ለእውቀት እና ለስልጣኔ አለመክፈት ነው ፣ የፍርሃት ምልክቱ የስነ ልቦና ሽባነት ፣ ደመ ጨፍጋጋነት ነው ። እና ታዲያ ጀግና ካልሆንክ ለምን ትኖራለህ ። ደፋር ነኝ የምትል ከሆነ ፣ ከላይ የጠቀስኳቸውን ነገሮች ( ነጻነት ( ስል እኩልነት ፣ የመናገር መብት ፣ የመጮኽ መብት ፣ ቢያንስ ባግባቡ የማልቀስ መብት )) ለሕዝቦች መስጠት ለምን ትፈራለህ ? እና እንደ ሰው ፣ በራሽ ጭንቅላት ሳታስብ ፣ ሳታገናዝብ ፣ አንድም ቀን ለአፍታ እንደ ሰው ሳትተነፍስ ፣ ኑረህ ኑረህ ኑረህ ስትሞት ምን ይሰማሃል ?
ጥያቄው የምትሞትለት ሰው ፣ የምትሰዋለት ሀገር ፣ የምትኮራበት ታሪክ የሌለው ሰው ከሆነክ ለምን ትኖራለህ ነው ?

No comments:

Post a Comment