Translate

Thursday, April 2, 2015

ስልጣን ላይ አድሮ ለመገኘት ሃገርን መሽጥ፤ ህዝብን መሸፈጥ ለምን? እስከመቼ?

እስከ ነጻነት
1. ስልጣን ላይ አድሮ ለመገኘት ሃገርን መሽጥ፤ ህዝብን መሸፈጥ ለምን? እስከመቼ?
የህወሃቱ መሪ መለስ ዜናዊ ሰሜን አፍሪቃ የተነሳሳው ህዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያኖች ዘንድ መወያያ ርዕስ እንዳይሆንና አመጹም እንዳይዛመት “ዛሬን ስልጣን ላይ አድሮ መገኘት፤ ቀኑን እንዳመጣጡ ለማለፍ ስልት መቀየስ” በሚል እምነቱና ስልጣንን ከህዝብም ከሃገርም በላይ አምላኪነቱ የተነሳ: ለነገ ምን ችግር ያመጣል? ጉዳቱስ መጠኑና ስፋቱ ምን ያህል ይሆናል? ሃገር ሉዓላዊነትና ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የሚኖረው አዎነታም ሆነ አሉታ ተጽዕኖ ሳያሳስበው: ብልጭ ባለለት ማምለጫ መንገድ ብቻ የሚንቀሳቀሰው መለስ “አባይን እገድባለሁ” የሚል ቅዥት ይዞ ብቅ እንዳለ ሁላችንም እናስታውሳለን። ይህን ያልታሰበበት፤ ያልተጠና፤ ህዝብ ያላወቀውና መክሮ ያልተስማማበትን ቅዥት በየሙያው ዘርፉ አንቱ የተባሉና የሃገራቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው ተናገረውበታል፤ ጽፈውበታል አስጠንቅቀዋል፡ ህወሃት ግን የዕለት ስልጣንና ከስልጣን የሚገኝ ጥቅም እንጂ የህዝብ ስሜትና ፍላጎት ስለማያስጨንቀው ሊሰማ አልቻለም፡ በምጣኔ ዘርፍ፤ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ፤ በህግ ዘርፍ፤ በርካታ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ስለሰጡበት እኔ እሱ ላይ አልመለስም።
እኔ ማንሳት የምፈልገው: ከሙያው ቅርበት ካላቸው በስተቀር የኢትዮጵያ ህዝብ አያውቀውም ብዬ የምገምተውን: ማወቅ አለበት፤ አውቆም ለጥፋቱና ለሃገራዊ ሉዓላዊነት መደፈር ከህወሃት እኩል ተጠያቂ መሆኑን ሊያስገነዝብ ይችላል የምለውን አባይ ወንዝ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችን፤ የቀረቡ ሃሳቦችንና እቅዶችን; ህወሃት የሄደበትን የተቃርኖ መንገድ በተመለከተ ይሆናል።
1.1 በአባይ ወንዝ ዙሪያ የተደረጉ አብይ ጥናቶች
በአባይ ዙሪያ የተደረገው የመጀመሪያ ጥናት በአሜሪካ ጂኦሎጂ ቅየሳ (United States Geological Surfay(USGS)) እ አ አ በ1960ዎቹ የነበረ ሲሆን በዚያን ጊዜ የተመረጡት አራት የግድብ ቦታውች ነበሩ፤ እነዚህም ከጎሃጽዮን-ደጀን አባይ ድልድይ ወደ ሱዳን አቅጣጫ ተከትለን ሲንሄድ በቀደም ተከተል (ካራዶቢ፤ ማቢል፤ መንዳያ እና የግርጌ (Karadobi, Mabil, Mandaia and Border) ናቸው።
ከታች ያለውን ንድፍ ይመልከቱ፡
Proposed dams on Blue Nile
ሁለተኛው ጥናት የተደረገው በ1980ቹ ሲሆን ቼዘን (CESEN) የተባለ የጣያን አማካሪ መሃንዲስ ቡድን ሲሆን የሃገሪቱን ጠቅላላ የሃይል ፍላጎትና አቅርቦት አጥንቶ ነበር፤ ይህም ጥናት እነዚህን አራት የአባይ ግድቦች በጥናቱ አካቶ ነበር።
ሶስተኛው ጥናት ደግሞ በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ የተጠናው የአባይ ተፋሰስ የተቀናጀ የማስተር ፕላን ዝግጅት ነው።
(በነገራችን ላይ ይህን የፕሮጀክት ጥናት ለመስራት በመጀመሪያ አሸናፊ የነበረው የሻውል ኮንሰልት ከውጭ ካሉ ድርጅቶች ጋር ነበር፤ ሻውል ኮንሰልት የኢንጅነር ሃይሉ ድርጅት ነው። ጨረታውን አሸንፈው ለፊርማ መለስ ዜናዊ ጋ ሲቀርብ ጠላቶቻችንን ራሳችን ነን ፋይናንስ የምናደርጋቸው ብሎ በመበሳጨቱና ውሉ እንዲሰረዝ ከመደረጉም በላይ በመንግሰት ወጪ በሚሸፈኑ ፕሮጀክቶች ላይ አገር ውስጥ ያሉአማካሪ መሃንዲስ ድርጅቶች (ኢትዮጵያውያንያቋቋሟቸው ድርጅቶች) በሙሉ ጫረታ ላይ እንዳይሳተፉ ታገዱ: ኢንጅነር ሃይሉ በወቅቱ የመ ኢ አ ድ ምክትል ፕሬዚዳንት ስለነበሩ ነው ጠላቶቻችንን ያለው መለስ ዜናዊ:: ኢንጅነር ሃይሉም በዚህ የተነሳ ከመ ኢ አ ድ ምክትል ፕሬዚዳንትነትም አባልነትም ለቀው፤ አገሪቷንም ለቀው ወጥተው።)
ከዚያም ሌላ ጫረታ ተካሂዶ (BCOEM, French Engineering Consultants) የሚባል የፈረንሳይ ኩባንያ ጨረታውን አሸንፎ ጥናቱን አከናውኗል። ይህም ጥናት አነዚህኑ አራት ግድቦች ያካተተ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የልማት አማራጮችንም የካተተ ነበር።
1.2 የአባይ ተፋሰስና የደለል ችግር
አባይ ወንዝ በተለይ ከጎጃም፤ ከወሎና ከሸዋ የሚመጡ ገባሮች (እንደ በሽሎ፤ ጀማ፤ ሙገር ጉደር) የመሳሰሉት ከተራቆተው መሬት አፈሩን ጠርገው ስለሚመጡ ከፍተኛ ደለል ይሸከማሉ። አባይ በአማካኝ በአመት ከ140-150 ሚሊየን ቶን ደለል ተሸክሞ ካገርይወጣል፤ ይህም ደለል ለሱዳንና ግብጽ ከፍተኛ ራስ ምታት እየፈጠረባቸው ነው። ለደለል መጥረጊያ ብቻ በአመት በአማካይ $200,000,000 ሁለት መቶ ሚሊየን ዶላር ያወጣሉ።
1.3 ጥናቶቹ የደረሱበት ግኝትና የልማት እቅድ
አባይ እጅግ ከፍተኛ የሃይል ማመንጨት አቅም ያለው ተፋስስ መሆኑን ሁሉም ጥናቶች ይስማሙበታል፡ የአባይ ተፋሰስ ጥናት ላይ የተመሰረተ፤ ህዝብን ያሳተፈ፤ ባለሙያዎችን ያካተተ እቅድና ልማት ቢካሄድበት ኢትዮጵያን በሙሉ በሃይል አቅርቦትና ከአንዲ ሚሊየን በላይ የመስኖ ልማት በስርኣቱ ቢለማ ለሃገሪቱ የምግብ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል: ግንባታው ግን በሚከተሉት ቀደም ተከተል መሆን እንዳለበት ሙያዊ ምክራቸውን አቅርበዋል::
በቅድሚያ አባይ ከፍተኛ ደለል ተሸካሚ ስለሆነ ይህ ደለል ደግሞ ለግድብ መሙላትና አካባቢ ብክለት ስለሚዳርግ መጀመሪያ በጣም ሊተኮርበት የሚገባው ተግባር ተፋሰሱን ማጎልበትና በጎርፍ የመሬት መሸርሸርን መቆጣጠር ነው። እነዚህም ተግባራት የእርከን ስራዎችን፤ የተራቆቱ መሬቶችን በደን መልሶ መሸፈንን፤ በጣም አስጊ የሆኑትን እንሰሳትና ምንጣሮ እንዳይካሄድባቸው መከለልን ያካትታል።
ግድቦቹ መሰራት ያለባቸው በምዕራፍ (phase) ሲሆን ግንባታውም ከላይ ወደታች መኬድ እንዳለበት (upstream to downstream) ነው፡ ለዚህም በቂ ምክንያት አለ፤ 1ኛ፤ የግድቡ ወጪ ቀለል ያለ ይሆናል፤ ሁለተኛ ከላይ ሲቆፈር የተቆፈረው አፈር ወደ ግድብ የመግባት እድል ስለሌለው ለግድብ መሙላት አሰተዋጽኦ አይኖረውም፤ 3ኛ፤ የኤሌክትሪክ ሃይል ካመረተ በሗላ መስኖ የማልማት እድል ይኖረዋል፡ በዚህ መሰረት ቅድሚያ የሚሰጠው የካራዶቢ (Karadobi) ግድብ ሲሆን በቀጣይ ማብል (Mabil) ማንደያ (Mandaia) በመጨረሻም የግርጌ (Border) ግድብ ናቸው፡ እንዚህ ግንባታዎች አቅም እየተገነባ ቀስ በቀስ የሚገነቡ ሲሆን ተፋሰሱ ላይ ደግሞ ከፍተኛና ተከታታይ ስራ መሰራት እንዳለ ሆኖ ነው። ይህ አሰራር አንድን ውሃ በቅብብሎሽ አራት ቦታ ላይ ሃይል ማመንጨት ሰለሚያስችል ከፍተኛ የሃይል ማመንጨት አቅም ከማስገኘቱም በላይ ግንባታውም አቅምን ያገናዘበና የተጠና ይሆናል። በተጨማሪ አባይ ተፋስሰስ ውስጥ ከአንድ ሚሊየን ሄክታር በላይ የሚሆን ለመስኖ ተስማሚ የሆነ መሬት ስላለ፡ የነዚህ ግድቦች ግንባታ ይህን የመስኖ ልማት እንዲያካትት ሆኖ መሰራት እንዳለበት ጥናቶቹ ይመክራሉ።
1.4 የህወሃት የተቃርኖ ተግባር
ኢትዮጵያ ውስጥ የውሃ ሃብት ጥናትን፤ ዲዛይንን፤ ቁጥጥርን በተመለከተ በባለቤትነት የሚመራው የውሃ ሃብት ሚንሰቴር ነው፡ አባይን እንገድባለን የሚባለውን ቃል የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ መሃንዲሶች የሰሙት ግን እንደማንኛውም ዜጋ አፍሪካ አዳራሽ ለስብሰባ ተጠርተው ከበረከት ስምዖን አፍ ነው። በወቅቱ ከድንጋጤ የተነሳ ምን መናገር፤ ምን ማለት እንዳለባቸው አንኳ ማስብ በማይችሉበት ደረጃ ተገርመው እንደነበር ይታወቃል።
የግድብ ስራው በጥናቱ እንደተመከረው ከላይ ወደታች እየተሰሩ መሄድ ሲገባቸው የመለስ ግድብ ግን የጀመረው ሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ነው። እንደዚህ አይነት ከሜዳ የተነሳ ግንባታን ለስማቸው የሚጨነቁና በሙያቸው የሚኮሩ የግንባታ ተቋማት በምንም መልኩ ተሳታፊ አይሆኑም ለዚህም ለስሙ ብዙም ለማይጨነቀውና ቀድሞም የጎደፈ ስም ላለው ሳሊኒ (SALINI CONSTRUCTION S.P.A.) ያለምንም ጫረታ የተሰጠውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ መጠራጠር አይቻልም።
1.5 ይህ ግድብ ኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው መዘዝ
ግድብ ከታች ተሰርቶ ከላይ ቁፋሮ ማድረግ ስለማይቻል ከላይ ያሉት ሶሰቱ ግድቦች ካሁን በሗላ ለግንባታ የሚታሰቡ አይሆኑም፤ እነሱ እስካልተገደቡ ድረስ ደግሞ አንድ ጥማድ ማሳ እንኳ በመስኖ ለማልማት አይቻልም፡ ስለዚህ ከሶሶቱ የሚገኘውን ሃይልና ከሚሊየን በላይ የሆነ የመስኖ ልማት ያሳጣናል ማለት ነው።
ከላይ እንደተጠቀሰው አባይ ከፍተኛ ደለል ተሸካሚ ስለሆነና በተፋሰሱ ላይ ምንም ተግባር ያልተከናወነ በመሆኑ የተሰራው ግድብ ሃይል ከማመንጨት ይልቅ የደለል ማከማቻ ይሆናል ማለት ነው: ከዚህ የተነሳ ግብጽና ሱዳን ከደለል ነጻ የሆነ ውሃ ስለሚያገኙ በያመቱ ለደለል ጠረጋ ያጠፉ የነበረው $200 ሚሊየን ዶለላር በቀላሉ ያተርፋሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ለመስኖ ውሃ አንድ ባሊ ውሃ እንኳን መጠቀም የማትችልበት ሁኔታ ስለሆነ የአባይን ውሃ ሙሉ ለሙሉ ይቆጣጠሩታል፡ እኛ ኢትዮጵያውን አባይ ወንዝ ላይ ያለን የባለቤትነት መብት እናጣለን የሃገሪቷም ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው: ግድቡ ሲጀመር ግብጽም ሆኑ ሱዳን ለይስሙላና ተቃውመዋል ተብሎ ኢትዮጵያውያንን ለማታለል ብቻ እንጂ ጫን ያለ ተቃውሞ ያላሳዩትም ይህንን ጥቅማቸውን ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበረ ነው።
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የለለበት መለስ ዜናዊ ገና ስልጣን እንደያዘ ወንበሩ ላይ እንኳ ገና ተስተካክሎ ሳይቀመጥ፤ በሽግግር ላይ እያለ ነበር ካይሮ ድረስ ሄዶ ከግብጽ ጋር መፈራረሙን ነው። ያ ውል የተዘጋጀው በሁለት ቋንቋ ሲሆን በአረብኛና በእንግሊዛኛ ነበር፡ አረብኛ የግብጽ ብሄራዊ ቋንቋ ሲሆን እንግሊዘኛ ምን እንደሆነ መለስና ህወሃቶች ናቸው።
ስምምነቱም ለግብጽ ታዛዥነትን ያመለከተ ከመሆኑ ባሻገር ለ ኢትዮጵያ ታላቅ ኪሳራ ያስከተለ ነበር፤ ያንን ፊርማ ተከትሎ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የነበራትን ፍጹም የግዛት ሉዓላዊነት አቋም ለውጦ ምንነቱ እንኳ በውል መተርጎም ያልተቻለበትን (equitable utilization and non appreciable harm) ነው የምንከተለው ተባለ። ግብጽ ግንጥንት ጀምሮ ስትከተል የነበረውን ኣቋም ቅንጣት አልቀየረችም: አሁንም አልቀየረችም።
የህወሃት ባለስልጣናት ግድቡ የታቀደው የሰሜን አፍሪቃን ህዝባዊ አመጽ ትኩረት እንዳይስብ የኢትዮጵያን ህዝብ ትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር እንጂ ታስቦበትና ታቅዶ የተጀመረ አለመሆኑን ቢያውቁም ከህዝብ የሚሰበሰበው ገንዘብ ደግሞ የኤፈርትንና የህወሃት ባለስልጣናትን ኪስ እያደለበ በመሆኑ ሊያስቆሙት አልፈለጉም: የሚያመጣውም ጣጣ አልታያቸውም እንዳውም ይባስ ብለው ሌላ ውል እየተዋዋልን ነው አሉን።
1.6 ግድቡ ለግብጽና ለሱዳን ጠቃሚ ከሆነ ያሁኑ ስምምነት ፊርማ ለምን መጣ?
ከላይ ከላይ የሚታየው ስምምነቱን በፓርላሜንት አስጸድቀው ህጋዊ እውቅና ያገኘ ሰነድ በእጃቸው ለመጨበጥና ወደፊት ለሚነስ የይገባኛል ጥያቄዎች ማስረጃ ለመያዝ መስሎ ሊታይ ይችላል፡ ህጋዊ ሆነም አልሆነ አሁን ያለው ግድብ በዚሁ ካለቀ ሁሌም አገልግሎቱ ለግርጌ ተፋስስ ሃገሮች ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ባዶ እጇን አጨብጭባ ዜጎችም በጉልበት ገንዘባቸው ከመበዝበዝ ያለፈ ጠብ የሚል ነገር አለመኖሩን በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።
ይህ ከላይ የተጠቀሰው ውጫዊና ማስመሰያ ሲሆን ዋናው አላማ ግን፡ ግድቡ እንደተባለው ለተቃውሞ ማስተንፈሻ፤ አቅጣጫ ማስቀየሪያ እንጂ ለእውነተኛ ልማት የታቀደ ባለመሆኑ መካተት ያለባቸው ጥናቶች አልተካተቱም፤ የአባይ የውሃ መቋጠሪያ ውሃው የሚጠራቀምበት፤ ሃይቅ የሚፈጥርበት ሸለቆ (Reservoir area) እሳተገሞራ ወለድ አለት በመሆኑ (volcanic rock) ስለሆነ ስንጥቅጥቅና ስብርባሪ (fractures and fissures) ይበዛበታል፡ ውሃ በነዚህ ስንጥቆች ውስጥ በቀላሉ ሊሰርግ ይችላል፡ ውሃ ሰርጎ ከገባ ደግሞ አለቱን የመፈንቀል፤ አፈሩን የመሸርሸር ከፍተኛ አቅም (uplift/pore pressure and piping) ስላለው ግድቡን እስከማፍረስ ሊደርስ ይችላል፤ ግብጽና ሱዳን ይህንን ጠንቅቀው ያውቁታል፡ ግድቡ ሲፈርስ ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ ያሰሉታል: ስለሆነም ዋሰትና ይፈልጋሉ፤ እነሱ ከአባይ ጥቅሙን እንጂ ጉዳቱን መጋራት አይፈልጉም። አጋጣሚ ሆኖ ግድቡ ቢፈርስና ጉዳት ቢደርስባቸው ካሳ ይፈልጋሉ ለዚህም ነው የካሳን ነገር ስምምነቱ ውስጥ የሸነቀሩት። ህወሃት ደግሞ ዛሬን ስልጣን ላይ አድሮ መገኘቱን እንጀ ነገ የሚመጣውን ማሰብም ሆነ ማቀድ አይፈልግም፤ አቅሙም ፍላጎቱም የለውም። የተፈራው ደርሶ ግድቡ ቢናድና ሱዳንና ግበጽ ላይ አደጋ ቢደርስ ኢትዮጵያ የምትከፍለው ካሳ ምን ያህል ነው? ካሳውስ ከየት ነው የሚሰበሰበው? ያው ከህዝብ አደል?
1.7 አሁን ከህዝብ ምን ይጠበቃል?
ይህ ቀላል ጉዳይ አደለም፤ ለእለት ስልጣን ተብሎ የትውልድ ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብትና የሃገር ሉዓላዊነትን አሳልፎ መስጠት ቀልድ አይደለም፤ እንኳን ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ የህወሃት አባላትና ባለስልጣናት በእጅጉ ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሃገሪቷን ምን አይነት ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊከቷት እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል።
ከዚሁ ጋር ለግድቡ ግንባታ እርዳታ አደረግን፤ ቦንድ ገዛን የምትሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልማትን እየደገፋችሁ ሳይሆን የሃገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እየጣላችሁ፤ ለትውልድ መተላለፍ ያለበትን የተፈጥሮ ሃብት ለባዕድ ሃገር አሳልፋችሁ እየሰጣችሁ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል፤ ሃገሪቷ ለሚደርስባት ማንኛውም ውድቀት ተሳታፊ መሆናችሁን መገንዘብ አለባችሁ።
ለዘለቄታው የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ላለመስጠትና ሉዓላዊነቷን አደጋ ላይ ላለመጣል ግድቡ ለወፊት ሊቀጥል በሚቻልበት ደረጃ ተዘጋጅቶ መቆም አለበት (The construction of the dam should be halted right away with a condition to resume when the time is right.) ግንባታው አሁን ባለበት ቆሞ፤ ህዝብንና ባለሙያዎችን ያሳተፈ ጥናትና እቅድ ተይዞለት ለሃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን የውሃ ሃብቱንም ለመስኖ መጠቀም በሚቻልበት መንገድ መሰራተ አለበት። ግንባታው ከጠረፍ ሳይሆን ከካራዶቢ (KIaradobi) መጀመር አለበት። ይህን ስል ለግድቡ እስካሁን የወጣውን ወጭ ግምት ውስጥ ማስገባት ተስኖኝ አደለም ግን ሃገርንና የተፈጥሮ ሃብትን ጨርሶ ከማጣትና ተተኪ ትውልድን ድህነትና ውርደትን ከማስረከብ እዚሁ ላይ ቢቆም ይበጃል ከሚል ግንዛቤ ነው።
እኔ የታየኝን፤ ያማውቀውን፤ የማምንበትን፤ የሚያስጨንቀኝን እንደ አንድ ዜጋ መልዕክቴን አስተላልፌያለሁ። እያንዳንዱ የዜግነት ድርሻውን ይወጣ፤ በተለይ ለዚህ ግድብ ግንባታ ቦንድ የምትገዙ፤ እርዳታ የምትሰጡ፤ አባይ አባይ እያላችሁ የምትጮሁ አርቲስቶች ሃቁን ተረድታችሁ የህሊናችሁን እንድታደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ
እስከ ነጻነት

No comments:

Post a Comment