Translate

Monday, June 3, 2013

ምርመራው ወደ አቃብያነህጉ ተዛወረ!

የሙስናው “ሻርኮች” በዒላማ ውስጥ?

berhane


* “አዲስ ነገር የለም” ጸረ ሙስና ኮሚሽን
በተለያዩ ከፍተኛ ወንጀሎች በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ የተከፈቱ ክሶችን በማፈንና በመመሪያ ፍትህ በማዛባትና በማቋረጥ ወንጀል የተጠረጠሩ አቃቤያነህግ ላይ ምርመራ መጀመሩ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩ ተሰማ። በተለይም ከወንጀል ጋር ቁርኝት እንዳላቸው በህዝብ የሚታወቁ ክፍሎች ክፉኛ መደናገጣቸው ተሰምቷል።

በሙስና የተጠረጠሩት የጉምሩክ ባለስልጣናት፣ ተባባሪ ነጋዴዎችና ደላሎች መታሰራቸውን ተከትሎ ከተፈጠረው ስሜት በላይ ከፍተኛ መደናገጥ የፈጠረው ዜና አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅዳሜ እለት ለንባብ ያበቃው ዜና ነው።
በቅርቡ ከሃላፊነታቸው የተነሱት የፍትህ ሚኒስትር አቶ ብርሀነ ሃይሉና ከአስር በላይ አቃብያነህግ በተለያዩ ጉዳዮች የተመሰረቱ ክሶች እንዲቋረጡ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው መመርመራቸው በትክክል ከተሰራበት ዋንኛ የሚባሉትን የሙስና ወንጀል “ሻርኮች” በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚያስችል ከፖሊስ ያገኘነው ጥቆማ ያመለክታል።
“የበርካታ ጉዳዮች ክስ እንዲቋረጥ መደረጉን እናውቃለን” በማለት ለጎልጉል ጥቆማ የሰጡት የፖሊስ አባላት “ይህ ጉዳይ ከተነሳና በትክክል ከተሰራበት የማይጎተት የለም” በማለት በትዕዛዝና በመመሪያ የተቋረጡ የምርመራና የክስ ፋይሎች በርካታ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ተቋማትንና ጉዳዮችን ስም በመጥራት መናገር እንደሚቻል የጠቆሙት ክፍሎች እንዲቋረጡ  የተደረጉ የክስ ሂደቶችን አስመልክቶ ህዝብ ነጻ መድረክ ቢሰጠው የተሻለ እንደሆነ አመልክተዋል። የፌደራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የቅርብ ሰው የሆኑ የጎልጉል ምንጭ በበኩላቸው “ኮሚሽኑ የመረጃና የማስረጃ ችግር የለበትም። በርካታ አቤቱታዎች ቀርበውለታል። ግን ሳይፈቀድለት መራመድ አይችልም” በማለት ማነቆው ከላይ እንደሆነ አስረድተዋል።
አሁን ስለተፈጠረው አዲስ ሂደት ሲያስረዱ “አዲስ ነገር የለም” በማለት ፍትህ ሚኒስትሩንና የፍርድ አስፈጻሚ አካላትን በስልክና በቃል መመሪያ በመስጠት ሲያዙ የነበሩት ክፍሎች አስቀድመው የሚታወቁና ኮሚሽኑ ከቁጥር በላይ መረጃ የሰበሰበበት እንደሆነ አመልክተዋል። ከደህንነቱ ጋር በቁርኝት የሚሰራው ኮሚሽኑ ራሱ ውስጥም ተመሳሳይ መነካካት እንዳለበት ጠቁመዋል። ዝርዝር ጉዳዩን ለመናገር አይቻልም ብለዋል።
አዲስ አድማስ አስር አቃቤ ህጉጋን እንደሚታሰሩ ጠቅሶ የዘገበው ዜና እነሆ
በቅርቡ ከስልጣን የተነሱት የፍትህ ሚኒስትር አቶ ብርሃነ ኃይሉና ከአስር በላይ አቃቤ ህጐች በሙስና፣ በሽብርተኝነትና በግድያ ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የተመሰረተን ክስ ያለአግባብ አቋርጠዋል በሚል በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ምንጮች ገለፁ፡፡ ፖሊስ በሚኒስትሩና በአቃቤ ህጐቹ ቢሮ ባካሄደው ከፍተኛ ብርበራ በርካታ መዝገቦችን ማግኘቱንና ለምርመራ መውሰዱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በፖሊስ ብርበራ የተገኙት መዝገቦች ያለአግባብ ተቋርጠው እንዲዘጉ የተደረጉ ክሶች ናቸው ተብሏል፡፡
ተከሳሾች ላይ በቂ ማስረጃ ማቅረብ ካልተቻለ ክሶቹን አቋርጦ መዝገቡን መዝጋት የፍትህ ሚኒስትርና የአቃቤ ህጐች ስልጣን መሆኑ ቢታወቅም ከሙስና፣ ከሽብርተኝነትና ከግድያ ጋር የተያያዙት እነዚህ በፖሊስ ብርበራ የተገኙ ከደርዘን በላይ የሆኑ መዝገቦች ግን፣ በቂ ማስረጃ እያለ፣ ያለ አግባብ የተቋረጡ ናቸው ተብሏል፡፡ ምርመራው ተጠናቆ እንዳበቃ በሚኒስትሩና በአቃቤ ህጐቹ ላይ ክስ እንደሚመሰረትም ምንጮች ጠቁመዋል። ለሰራተኞች አቤቱታ ምላሽ ባለመስጠትና በሥራ ድልድል በደል ፈጽመዋል በሚል ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩት የፍትህ ሚኒስትሩ፤ በተለይ የጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ይታያሉ የተባሉ ችግሮችን እንዲፈቱ አራት የማሳሰቢያ ደብዳቤዎች ተጽፎላቸው እንደነበር ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በሚኒስትሩ ላይ ከባለጉዳዮችም የተለያዩ ቅሬታዎች ይሰነዘሩ ነበር ያሉት ምንጮች፤ የታራሚዎች የይቅርታ ጥያቄን ማዘግየትና ተገቢ ምላሸ አለመስጠት በዋናነት እንደሚጠቀስ ገልፀዋል፡፡
በቅርቡ በተካሄደው የኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ ላይ ከፓርቲው መሪዎችና አባላት ለሚኒስትሩ የቃል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው እንደነበር ምንጮች ገልፀው፣ ፓርላማም የመ/ቤቱ በርካታ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ በኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ ላይ የአገሪቱ ዋና ችግር በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሚታይ እንደሆነ መገለፁ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ሶስት ሚኒስትሮች በወንጀል ተጠርጥረው ከስልጣን የወረዱ ሲሆን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ከአገር መኮብለላቸው ይታወሳል፡፡ (ፎቶ አዲስ አድማስ)

http://www.goolgule.com/changing-gear-to-prosecutors/

No comments:

Post a Comment