ትውልድ አምካኝ ቤቶችን፣ ትውልድ አምካኝ ደላሎችን፣ በህጻናት የወሲብ ንግድ ገንዘብ የሚሰበስቡትን፣ ማጥፋት ቀላል ነው። ግን ተጠቃሚዎቹ ህግ አስከባሪዎቹ፣ ህግ አወጪዎቹና ዋናዎቹ “የአገሪቱ ህዳሴ ባለቤቶች” የሚባሉት በመሆናቸው አይታሰብም። አንዳንድ ዝግ ቤቶች በሲቪል ጠባቂዎች የሚጠበቁ ናቸው። አንዳንዴ ቤተመንግስቱንና ሟቹን የቤተመንግስት ነዋሪ ይጠብቁ የነበሩት በፈረቃ ይታደሙባቸዋል።
ሃኪሞች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ አገር የሚመሩት፣ ህግ የሚያስከብሩት፣ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ አውራ ባለስልጣናት፣ ህዝብ ፊት ቀርበው በልማት ስም የሚምሉት ሃብታም ተብዬዎች፣ የፖሊስ የበላይ አመራሮች፣ የስለላ አውራ ሰዎች፣ አጫፋሪዎች፣ የአቻ ፓርቲ አመራሮችና መካከል ጥቂት የማይባሉ ከዳር እስከዳር መመሸጊያቸው ዝግ ቤቶች ናቸው። አንዳንዴም ከዝግ ቤቶች ፍራሽ ላይ ሆነው የፖለቲካ መመሪያ የሚሰጥበት አጋጣሚ አለ። ይህን አስደንጋጭ እውነት “መርከስ” ነው። አዲስ አበባ ይፋ አደረገችው እንጂ በየክልሉ ከተሞች የሚደረገው ተመሳሳይ ነው።
የሺሻና የጫት በጀት የሚመድቡ ባለስልጣናት አሉ። አስቤዛ ሲደረግ “ሙአሰል” ከህጻናት ዳይፐርና የዱቄት ወተት እኩል የሚመድቡ አሉ። ህጻናትን በመመልመል ሳውና በማስገባት፣ በማሰልጠን፣ ዘመናዊ ልብስ በማልበስ ለገበያ የሚያቀርቡ ብዙ ናቸው። እገሌ ለሚባል አየር መንገድ አስተናጋጅ እንቀጥራለን በሚል ታዳጊዎችን እያንጋጉ በወሲብ የሚነዱና የሚያነዱ ይህን ተግባራቸውን የሚፈጽሙት ማስታወቂያ እያስነገሩ ነው።
ግብረሰዶም የሚያስፋፉ በየሆቴሉ ድሆችን በማደን ማበላሸት ከጀመሩ ቆይተዋል። አሁን አሁን በየጎዳናው ታዳጊዎችን በማታለል ህሊና የሚያስት ኬሚካልና እጽ በመጠቀም ህሊናቸውንና አካላቸውን መስበር ተለምዷል። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው በዚህ የግብረሰዶም ወረራ ውስጥ ተጠቃሚ በመሆን ወንድሞቻቸውን የሚደልሉ መበራከታቸው ነው።
ህጻናትን ለወሲብ የሚያቀርቡ ነፍሰ በላዎች ኢኮኖሚያቸው አድጎ ባለ ዘመናዊ መኪናና ህንጻ መሆናቸው ነው። አዲስ አበባ ባሉ ዝግ ቤቶች ወሲብንና ግብረ ሰዶምን የሚያሻቅጡ ህሊና ቢሶች ጉዳይ ያሳሰበው ቀጭኑ ዘ-ቄራ የሚባለው የአዲስ አበባው አምደኛችን ከወራት በፊት “የሚዘጋባቸው ህጻናት” በሚል ርዕስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ጠቁሞ ነበር። (ዕድሜ ለኢንሳና አፈናው ብዕሩ ማዕቀብ ተደርጎበት በተከታታይ ጽሁፎችን ሳያስነብብ ቢቆይም እንዲሁ እንደጠፋ ግን አይቀርም፡፡)
የከበረውን ትዳራቸውንና ያብራካቸውን ፍሬዎች ቤት ጥለው፤ ባይወልዷቸውም ልጆቻቸው ከሚሆኑት ጋር የሚዳሩትና፣ የውሽሞች ቀን እያከበሩ አረቄ የሚራጩት ሃብታሞች ጠለቅ ያለ ምርመራ ቢደረግባቸው እስከ ዱባይ የዘለቀው የግፍ ገመናቸው ይገለጥ ነበር። ዳሩ የወንጀሉ ዋና ተባባሪዎች ተቆጣጣሪዎቹና ህግ አስከባሪዎቹ በመሆናቸው አስቀድሞ እንደተባለው አይታሰብም።
አዲስ አበባ መርከሷን ጥር 11 ቀን 2013 በአዲስ አበባ አስተዳደር ይፋ የተደረገው ጥናት፤ የቀንና የማታ ጭፈራ ቤቶችን፣ የእርቃን ዳንስ ቤቶችን፣ የማሳጅ፣ የቪዲዮ፣ የአደንዛዥ ዕጽ መጠቀሚያ፣ የግብረሰዶማውያን ማዘውተሪያ ቤቶችንና የመኪና ላይ ወሲብ መፈፀሚያና ጫት መቃሚያ ቦታዎችን በሚገባ በመቃኘት ተሰብስቦ በተሰራው ጥናት መረጋገጡን መረጃውን ይፋ ባደረገው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በኩል ሰምተናል። ዘገባው ትኩረት የሚያሻውና በሚሊዮን በሚቆጠሩት ታዳጊዎች ህይወት ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ ነው።
No comments:
Post a Comment