ነብር ዥንጉርጉርነቱን “ግራ ዘመም” ኢትዮጲያዊ ክሽፈቱን
በክፍሉ ሁሴን
ታምራት ነገራ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ”መጽሃፍ ላይ የሰጠውን አስተያዬት ካነበብኩት በኋላ የመጣብኝ ሃሳብ ሰውዬው የሚለውን ያውቀዋልን? የሚል ነው። እንደምፀት ሆኖ አሁን በማላስታውሰው ምክንያት ግን በወቅቱ በወደድኩለት አንድ የፌስቡክ አስተያዬቱ ብዙም በአንባቢነትና አለማቀፍ ነገሮችን በመተንተን ችሎታው የማላማው ይልቁንም የእሱን አይነት ሃይማኖት ያላቸውን ሰዎች “የአዲስ ኪዳን በግ ቅዱስ ካህን፤ የፅድቅ ንጉስ የአለም መድህን” እያልኩ የምመሰጥበት ሌላ ጓደኛዬ በዚያው እኔ የታምራትን አስተያዬት “ላይክ” ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የፌስቡክ ባልንጀሮቼ ባቃመስኩበት ወቅት “ይህ ታምራት የሚለውን ያውቀዋልን?”ሲል የጠየቀውን አስታወሰኝ። ምናልባት ጌታን በተቀበለና ባልተቀበለ መካከል ያለ ልዩነት ይሆን?
ጌታን እስከዛሬ ባልቀበልም (ጌታ ነው ከሚሉትም ጋር ጌታ አይደለም ብዬ ጠብ እንደማላበቅልም ልብ ይባልልኝ) ባንዳች ምክንያት ወልይ ሆኜ ነው መሰለኝ ታምራት “ነብር ዥንጉርጉርነቱን፤ ኢትዮጲያዊ ክሽፈቱን” በሚል ርዕስ በሰጠው አስተያዬት ልክ እንደ ዳግም ልደቱ ክርስቲያን ወዳጄ እኔም በተራዬ “የሚለውን ያውቀዋልን?” እንድል አስገድዶኛል። ታምራት የፕሮፌሰር መስፍን “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” ከመውጣቱ በፊት “The Ethiopian mind” በሚል ሊፅፍ እንዳሰበ ከነገረን በኋላ የፕሮፌሰርን መፅሃፍ ሲያነብ አንድ ላይ አጠቃሎ አስተያዬቱን እንደሚያቀርብ አሳወቀን፤ በዚያው በፌስቡክ ላይ። አከታትሎም “አርታኢዎቹ” ማስረሻ ማሞ እና ዳኝነት… እንዳሹበት አሳወቀን። ከጥቂት ቀናት በኋላም አስተያዬቱን በአዲስ ነገር የፌስቡክ ገጽ ላይ ለበደው። የእኔም በታምራት አስተያዬት እና አጻጻፍ ላይ መደናገር ከዚህ ይጀምራል።
ፕሮፌሰርን ፅሁፋቸውን ወደአንባቢ ከማድረሳቸው በፊት “ለአንድ ሁለት ዙር” ትችት ለአርታኢ የመስጠት ትህትና የላቸውም የሚለው ታምራት የእሱን ፅሁፍ ሳነብ ከአርታኢ ምንም የተጠቀመ አልመሰለኝም። ብዙ ነው ባይባልም እንኳ እሱ ፕሮፌሰር መስፍን ለአርታኢ አይሰጡም ብሎ ከተቸበት አኳያ ሲታይ ቀላል የማይባሉ የፊደል ግድፈቶች በጽሁፉ ላይ እዚህም እዚያም ይታያሉ። ለምሳሌ በአንቀጽ 3 ላይ “መናጡ እንደቀረልኝ” ሊል ፈልጎ “እየደቀረልኝ”ይላል። እንዲሁም ፕሮፌሰርን “ኢትዮጵያን ከመውደዳቸው የተነሳ ለማቀፍ ሲንደረደሩ ሊያንቋት ከሚዳዳቸው የቀኞች ወገን “ፓትያርክም” እያለ ይገድፋል። እንዴት በአርታኢ የሚያምን እና አርታኢን የተጠቀመ ጸሃፊ ፅሁፍ ውስጥ እንዲህ ያለ ግድፈት ሊኖር እንደቻለ አልገባኝም። ከሁሉም በላይ ታምራት በፕሮፌሰር መስፍን መፅሃፍ በተነሱት ቁምነገሮች መመሰጡን እየነገረን 238 ገጽ ከያዘው የፕሮፌሰር መስፍን መፅሃፍ ውስጥ ቁምነገር ያገኘው እና እንዲጽፍበት የጎነተለው በ 46 ገጾች ውስጥ ብቻ ያሉት “ቁምነገሮች” እንደሆኑ ይነግረናል። እንደታምራትም ባይሆን በትንሿ የአንባቢነት ዘመኔ ከያዘው ዳጎስ ያለ ገጽ ውስጥ ከ 80 ከመቶው በላይ ጅል ከሆነ ሃያ ፐርሰንቱ “ቁምነገር” ጋር ለመድረስ ተካልቦ በሚያካልበው የዛሬ ጊዜ ላይ ትዕግስት እንደማይኖር ጠንቅቄ ተረድቻለሁ። እና ታምራት ከሰማንያ ፐርሰንት በላይ በ “አላስፈላጊ ሐሳቦች” እና “አርቲ ቡርቲ” ተጥለቅልቋል የሚለው መጽሃፍ ላይ እንዴት ጊዜውን ወስዶ “ትችት” እስከመጻፍ እንደተጎነተለ አልገባኝም። አርታኢዎቹ በዚህ በኩል እንዲህ ያለ ሞጋች ጥያቄ ቢመጣብህ እንዴት ትከላከለዋለህ ሳይሉት ቀሩ ወይስ ያሉትን ሳይሰማቸው ቀረ? ወይስ ደግሞ “ዴሞክራት” አርታኢ የቋንቋ ግድፈት ከማሳደድ በቀር እንዲህ ያለ ጉዳይ ውስጥ አይገባም? ቋንቋን በማረምም ሆነ ሃሳብን በማጥራት በኩል ለታምራት ያልጠቀሙ አርታኢዎች ለፕሮፌሰር መስፍን ምን ይፈይዳሉ?
የ “ቀኝ ዘመም” ፖለቲካ እንዲህ ከሆነ
በደርግ ዘመን ነፍስ እንደማወቄ ኢሕአፓ የሚባለው ቡድን የእሱን አላማ የሚጠይቁትንና የሚቃወሙትን በተለይም መኢሶን የተባለውን የባላንጣውን ቡድን “ቀኝ መንገደኛ” እያለ ስም በማጥፋት ብቻ ሳይመለስ በጥይትም እንካ ቅመስ ይል እንደነበር አስታውሳለሁ። በንባብ ላይ ንባብ እየጨመርኩ እንዳቅሚቲ ለመንቃት በማደርገውም ጥረት በውጪው አለም ፖለቲካም የ”ቀኝ” የ”ግራ” የሚባል ፍረጃ እንዳለ ተረዳሁ። ያም ሆኖ በግሌ ገና ሳየው ጠረኑ ልክ (Just) የሆነ እና ልክ ያልሆነን (Unjust) ፖለቲካን የማፈነፍንበት ግን ስም ያልሰጠሁት የራሴን መስፈርት ስለቀየስኩ የቱ የ”ቀኝ” የቱ የ”ግራ” በሚለው እሰጥ አገባ ውስጥ ጊዜዬን አባክኜ አላውቅም። ሆኖም ታምራት የፕሮፌሰር መስፍንን መጽሃፍ “ባዘለው መልካም መልዕክት ከመሳብ ይልቅ” ከ”ቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጋር ተደባልቆ “ስለቀረበ “በጠረኑ ብቻ ብዙ ሰው ሊገፈተር ይችላል” የሚል የተምታታ ነገር ስላቀረበ የ”ቀኝ” የ”ግራ” የሚሉት ፖለቲካ ፈሊጥ ከየት እንደመጣ እና ማን በቀኝ ማን በግራ እንሚፈረጅ ማወቂያው ጊዜ አሁን ነው ብዬ ተነሳሁ። እናም ኮሌጅ መበጠስ ሳያስፈለግኝ እድሜ ለዊኪፔዲያ ፈሊጡ ከፈረንሳይ አብዮት የመጣ መሆኑን አጫወተኝ። እጅግ የሚገርመው እንደዊኪፔዲያ ትንተና ከሆነ የፕሮፌሰር አመለካከትም ሆነ የፖለቲካ አቋም የግራ የሚባል እንጂ ከቀኝ ዘመም የሚሰለፍ አይደለም። ፕሮፌሰሩ ያልተገራ ስልጣንን አደብ እንዲገዛ እና እንዲገራ እውነትን ለስልጣን እየነገሩ (speak truth to power) እንዲል ፈረንጅ በሶስት አገዛዝ እድሜ ልካቸውን እንዳልባጁ በጥራዝ ነጠቅነትና በጀሌነት ራሱን “ግራ ዘመም” አድርጎ ሲግበሰበስ የነበረው እና የኢትዮጵያን ሕዝብ በ”መሬት ለአራሹ” እና “የብሄር ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል መብት” ባዶ መፈክር ከግለሰብ ጉልተኞች በሰፊው ሕዝብ ስም ለአገዛዝ ጢስኝነት አሳልፎ የሰጠውና ለአደገኛ የመከፋፈል የጎሳ ፖለቲካ የዳረገው ክፍል እስከዛሬ ፕሮፌሰር መስፍንን የ”ቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጠማቂ” እና አከፋፋይ ያደርጋቸዋል። የእዚህ አንድምታ ፕሮፌሰሩን ወግ አጥባቂ እንዲያም ሲል አድሃሪ አድርጎ በመሳል ራስን ተራማጅ እና “የላብ አደር/ወዛደር፤ አርሶ አደር፤ ጭቁን ብሄር ብሄረሰብ እና የሰፊው ሕዝብ/ሕዝቦች” ተቋርቋሪ አድርጎ ለማቅረብ ነው። ይህንን ክፍል ነው ታምራት “ብዙው ሰው” ሲል ከሳለው በኋላ በፕሮፌሰር መስፍን “የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጠረን” ይገፈተራል የሚለን። በገዛ ራሳቸው አእምሯቸውን ከ1969 ዓ.ም በኋላ እንዳያድግ አድርገው የዘጉትን ግለሰቦች ፕሮፌሰር ምን ማድረግ ይችላሉ? የቀኝ ዘመም ፖለቲካ እንደ ፕሮፌሰር ከሆነ እጅግ አድርጎ የሚስብ እንጂ የሚገፋተር አይደለም። ታምራት በሚኖርበት አሜሪካ ሁለት የታወቁ አንዱ አሁንም በሕይወት ያለ አንዱ ከሶስት አመት በፊት የሞተ ስመጥሩ የማህበረሰብ፣ የፖለቲካና የታሪክ ተንታኞች ይገኛሉ። በሕይወት ያለው ኖም ቾምስኪ ሲሆን ሟቹ ደግሞ ሆዋርድ ዚን ይባላል። ሁለቱም በቀይ ህንዶች እና በጥቁር አሜሪካኖች ላይ የተፈጸመውን ግፍ እያነሱ እንዲሁም የአሜሪካንን የሌሎችን አገሮች የመቆጣጠር (Hegemonic) አባዜ ያለውን የውጭ ፖሊሲውን የሞገቱ ሲሆን አንድም ጊዜ ግን በአሜሪካ ግፍ የተፈጸመባቸውን የተለያየ ዝርያ ያላቸውን አሜሪካኖች በዘር አንጻር የዘር “ነጻ አውጪ ፖለቲካ” እንዲያቀነቅኑ እንደእኛ “ግራ ዘመም” የብሄር ብሄረሰብ ተቋርቋሪዎች አልመከሩም። እንደእሱ ያለው አመለካከት ከኢትዮጲያ በኋላ በተፈጠረችው እና በራሱ የታምራት ቋንቋ “ተቀራራቢ ምናባዊ” አሜሪካንን ለመፍጠር በተሳካላት አገር አገርን እንደመክዳት ይቆጠራል ሃሳቡን ማንሳት እንኳ ባይከለከልም። በአጠቃላይ የፖለቲካ አመለካከታቸውም ሆነ እድሜያቸው ከፕሮፌሰር መስፍን ብዙም የማይራራቁት እነዚህ አሜሪካኖች የሚፈረጁት በግራ ፖለቲከኛነት እንጂ በ”ቀኝ ዘመም” ፖለቲካ ጠላ ጠማቂነት አይደለም። የቀኝ እና የግራው ፍረጃ እንዲህ ግልጽ ከሆነ ለምን ታምራት ሊያጨናብረን ፈለገ? ሳያውቀው የእኛዎቹ “የግራ ዘመም” የብሄር ብሄረሰብ ተቋርቋሪ “ፖለቲከኞች” ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ይሆን? ጥያቄውን የመመለስ ያለመመለስ መብቱ የታምራት ሆኖ ሳለ ይህን ጽሁፉን ከአድናቂዎችም በላይ አምላኪዎችንም ያፈራችው የአዲስ ነገር ፌስቡክ ገጽ ላይ ስለለበደው አስተያዬቱ እንደወንጌል እንዳይወሰድ ሌላውን ገጽታ ማሳያት ግዴታዬ ሆኖ ተስምቶኛል። እናም ፕሮፌስር መስፍንን ፈረንጅ (whispering campaign )በሚለው የረቀቀ ስልት እንዴት እና ለምን ለሶስቱም አገዛዝ ቅርብ የነበሩ የተለያዩ ግለሰቦች ስማቸውን ለማጥፈት እና ሥራቸውን ለማቃለል እንደተነሳሱ ላሳይ። ታምራት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ነው ለማለት ሳይሆን በእነሱ ተጨናብሮ ሊያጨናብር ተነስቷል ግን እላለሁ። ፕሮፌሰር መስፍንን መጀመሪያ በበጎ ከማያነሷቸው ሰዎች ውስጥ የእድሜ እኩያቸው ከሆኑትና የሙያ “አቻቸው” ከሆኑት ውስጥ እንደሚገኙበት በተለያየ አጋጣሚ ለመታዘብ ችያለሁ። እነዚህ ሰዎች እንደእሳቸው ባለዲግሪ ቢሆኑም ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) “አይተኙበት ጀንዲ ዲግሪማ ነበረን በአይነት በብዛት” የሚላቸው አይነት ሰነፎች ሲሆኑ በምሁርነታቸው እያነበቡ እና እየተመራመሩ ከማደግ ይልቅ ለዘውዱ ሥርዓት እጅ እየነሱና እየተሞዳሞዱ ማደግን የኑሮ ዘዴ አድርገው የያዙና ለልጆቻቸውም ሲመክሩ የነበሩ ናቸው። የመስፍን ፍጹም በራስ መተመማን ሁልጊዜ የእነዚህን ሰዎች ድኩማንነት የሚያስታውስ ስለሆነ በቅናት መንፈስ መስፍንን ማብጠልጠል አንዱ መላ ነበር። መስፍንን እና እንደእሳቸው የዘውዱን ሥርዓት የአካዳሚክ ነፃነታቸውን ተጠቅመው የሚተቹትን ለማግለል ሲባል በአክሊሉ ካቢኔ ለመስፍን የግምቢ አውርጃ ገዢነት ሹመት ሲሰጥ ለሌሎች ደግሞ የክፍ ለሃገር ከተማ ከንቲባነት እና በሞስኮ ከተማ አታሼነት ተሰጠ። ሌሎቹ ያለምንም ማንገራገር ሹመቱን ሲቀበሉ መስፍን ግን ስለሹመቱ ከንጉሱ ማብራሪያ ካላገኙ እንደማይሄዱ ተናገሩ። የአክሊሉ ካቢኔም “ሹመቱ የተሰጠህ ከመተቸት ውጭ የተሻለ አስተዳደር ታመጣ እንደሆነ እንድታሳየን ነው” አላቸው። ሲመልሱም “በአውሮፕላን ስሄድ አየር ላይ መናጥ ሲበዛብኝ አስተናጋጁን ምነው መናጥ በዛ ስለው መልሱ ከቻልክ የማብረሪያው ክፍል (cockpit) ግባና አውሮፕላኑን አብረው ሊሆን አይገባም። “ሲሉ የአካዳሚክ ነጻነቱን ተጠቅሞ በሚያስተምር ምሁር ላይ አጸፋዊ እርምጃ መወሰድ እንደሌለበት አስረዱ። ለዚህ ጠንካራ አቋማቸውም ጥቂት ቀናት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዲከርሙ ሆነ። ይህንን የፕሮፌስር መስፍንን የአካዳሚክ ነፃነትን የማስከበር ፅኑ አቋም “የማስተዳደር ሥራ ስለማይችል ነው ሹመቱን ያልተቀበለው” በሚል ስማቸውን የሚያጠፉ የእድሜ እኩዮቻቸው አጋጥመውኛል። በደርግ ጊዜ በመርማሪ ኮሚሲዮኑ ተመርጠው ለጥቂት ጊዜ በመስራታቸው የተነሳ ስድሳዎቹን እንዳስረሸኑ አድርገው የሚያስወሩ ስራፈቶችና ይህንኑ የሚያምኑ ጅሎች እስከዛሬ መኖራቸውንም ታዝቤያለሁ። የደርግ ዋና ሰዎች መንግስቱ ኃ/ማሪያምንም ጨምሮ እስከዛሬ ድረስ ሳይገድሏቸው በመውደቃቸው እንዲሁ ስማቸውን ለማጥፋት እንደባጁ አሉ። ግን በወያኔ የውሸት ፍርድ ቤት ለማስመሰል እንኳ የሚበቃ ቅንጣት ማስረጃ ስለሌለ መንግስቱም ሟቹ መለስም አንዳቸው የወያኔ ሰው ነው ሌላኛቸው ደግሞ የደርግ ሰው ነው ብለው ስማቸውን ከሚያጠፉ በቀር የፕሮፌሰር መስፍን የረጅም ዘመን ታሪክ ላይ ጉድፍ ማግኘት አልተቻለም። የዘውዱን ሥርዓት እቃወማለሁ ይል የነበረውና ራሱን በግራ የፈረጀው የተማሪው እንቅስቃሴም ወደብረት የአመፅ ትግል ሲያዘነብል ሃሳብ ለሃሳብ ብቻ የሚፋጭበት የአካዳሚክ ሕይወትና ጡንቻ አብረው አይሄዱም በማለት ፕሮፌሰሩ ስለተቃወሙ ከዚህ ጮርቃነት እስከዛሬ ያልወጡት ስማቸውን እንዳብጠለጠሉት አሉ። እናም ይቺ በታምራትም ፕሮፌሰሩን “የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጠማቂ” የማድረግ ነገር ምንጯ ከዚህ የተለየ አይደለም። ባጭሩ ፕሮፌሰሩ በፅኑ አቋማቸው የተነሳ ቀኝ ተብለው የተፈረጁበት ሁኔታ “ግራ ዘመም” ነኝ የሚለውን ኢትዮጲያዊ የዘወትር ክሽፈት የሚያሳይ ዝብዛንኬ ነው። ታምራት “ባንድም ሆነ በሌላም መልኩ ስለመክሸፍ የኢትዮጵያ ምሁራን አውርተዋል” ሲል በተማሪዎች ረብሸኝነት በጎሳ ነጻ አውጪነት እና የጎሳ ማህበራት ተሰባስበው ራሳቸውን የሽግግር መንግስት ስላሉበት ሁኔታ አለመሳካት የጻፉትን ከመስፍን የመክሸፍ ትንተና ጋር ማያያዙ አንዱ ከመጽሃፉ በኋላም እንኳ እንዴት መክሸፍ እንዳላባራ ማሳያ ነው። ታምራት የጠቀሳቸው ምሁራን በአብዛኛው ከሽፎ ስላከሸፈ ትውልድ መክሸፍን እንደሚፈልገው አድርጎ እንዲቀጥል ባለማድረጉ ስላለው ክሽፈት ካልሆነ በቀር ስለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ጻፉ፤ ተመራመሩ ለማለት አይቻልም። እነዚህ በአብዛኛው ራሱ ታምራት ለሚለው “የምናባዊት ኢትዮጲያ ማህበረሰብ” አለመፈጠር ምክንያት ሆነው ከሽፈው ያከሸፉ ናቸው። እንዴት ሆኖ በእኔ ሞት የኢሕአዴግ የሽግግር መንግስት ክሽፈት ከኢትዮጵያ መክሸፍ ትንተና ጋር የሚያያዘው? ኢሕአዴግ የሚባለው መጥቶ ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ የኢትዮጵያ መክሸፍ የለየለት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ኦነግ እና ወያኔ ሽግግር በሚባለው ዘመን ተጣልተው በየፊናቸው ባይሄዱ ኖሮ ክሽፈት አልነበረም ለማለት ከሆነ ከባድ ቧልት ነው።
ታምራት “ስለኢትዮጲያ ሲባል ለምን ሐበሻ ልቡ ይፈሳል?” ሲል የጠየቀውን ጥያቄ ኢትዮጲዊነት ገብቶት ነው ብዬ ባስብ ኖሮ እወድለት ነበር። አንዱ የሐበሻን ልብ የሚያፈሰው እንደዚህ እሱ እንደጻፈው ያለ የተሳከረ ፅሁፍ መሆኑን ልነግረው እወዳለሁ። አገር ወዳድነት ሌላ ቦቃ የለውም ከመንደርተኝነት መውጣት ነው። ከመንደርተኝነት የወጣ ሰው ስለአገር ወዳድነት ማብራራት የግድ ካለበት እንደሩሲያዊው ሌሮሞንቶቭ “I love my country, but with a strange love. My reason cannot fathom it.” ማለት ብቻ ይበቃዋል። ሌላው ሃተታ በማያንሰራራ ሁኔታ ይበልጥ እንድንከሽፍ ማጨናበር ነው።
No comments:
Post a Comment