ኩላሊት ለመስረቅ ሙሉ መሳሪያና የኩላሊት ባለሙያ ያስፈልጋል – የሆስፒታሉ ባለሙያ በምንሊክ ሆስፒታል ኩላሊት ተሰርቋል በሚል በቀረበ አቤቱታ የተነሳ በሆስፒታሉ የአስክሬን ምርመራ ክፍል ላይ ምርመራ እንደተካሄደ ምንጮች የገለፁ ሲሆን፣ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች የኩላሊት ስርቆት ሊካሄድ አይችልም ሲሉ አስተባበሉ፡፡ የመኪና አደጋ ደርሶበት በምንሊክ ሆስፒታል ሲታከም የነበረ ሰው ህይወቱ በማለፉ የሟች ቤተሰቦች ለፖሊስ የሚቀርብ ማስረጃ ከሆስፒታሉ ጠይቀው ነበር በማለት የገለፁ ምንጮች እንደሚሉት፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተካሄደው የአስከሬን ምርመራ በቤተሰቦች ላይ ቅሬታና ጥርጣሬ እንደፈጠረ ይጠቁማሉ።
ጉዳዩም ወደ ፖሊስና ወደ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዳመራ ምንጮቹ ጠቁመው፣ መርማሪዎች በሆስፒታሉ ተገኝተው ቅኝት እንዳካሄዱና ባለሙያዎችን እንዳነጋገሩ ገልፀዋል። ከፖሊስና ከፀረ ሙስና ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ፣ በሃላፊዎች አለመገኘት ምክንያት ባይሳካም፤ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በበኩላቸው መርማሪዎች ወደ ሆስፒታሉ መጥተው እንዳነጋገሯቸው ጠቅሰዋል። አስከሬን ላይ ተገቢውን ምርመራ እንደሚያከናውኑ የሚገልፁት የሆስፒታሉ ባለሙያዎች፤ “በህክምና ወቅት ያልተከፈተውን የሟች አካል፣ በአስከሬን ምርመራ ወቅት እንዴት ይከፈታል?” የሚል ቅሬታ ከሟች ቤተሰቦች በተደጋጋሚ ይቀርባል ሲሉ ተናግረዋል።
ቅሬታውን ተቀብለው ምርመራ ለመካሄድ የፀረሙስና ኮሚሽን መርማሪዎች መጥተው እንዳነጋገሯቸው የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ጠቅሰው፤ ጉዳዩ ሊያስከስስ እንደሚችልና እንደማይችል የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡ እዚህ ሆስፒታል ውስጥ የኩላሊት ስርቆት ሊካሄድ አይችልም ሲሉ የተናገሩ ባለሙያዎች፣ በሆስፒታሉ ውስጥ የኩላሊት ተከላ የሚካሄድ ቢሆን ኖሮ አልያም የኩላሊት ማስቀመጫ መሳሪያ ቢኖር ኖሮ ለጥርጣሬ ምክንያት ሊሆን ይችላል ነበር ብለዋል። ከሟች አካል ኩላሊት ሊሰረቅ የሚችለው፤ በአፋጣኝ ኩላሊቱን መውሰድ የሚችል ባለሙያና የተሟላ መሳሪያ ሲኖር ብቻ ነው ያሉት ባለሙያዎች፤ የሟች አካል ለምርመራ ስለተከፈተ ብቻ የስርቆት ተጠርጣሪ መሆን የለብንም ብለዋል። እንኳን እዚህ አገር ከውጪ የሚመጡ አስክሬኖች ላይም ምንም አይነት አካል ሲጎድል አላጋጠመንም ብለዋል – ባለሙያዎቹ።
addisadmas.com
No comments:
Post a Comment