Translate

Thursday, March 21, 2013

የወያኔ/ኢህአዴግ ጉባኤ ውሃ ቢወቅጡት እሞቦጭ



ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይና በተለምዶ ተለጣፊ እየተባሉ የሚጠሩት ሎሌ ድርጅቶቹ ሰሞኑን በጉባኤ ሽርጉድ ላይ ተጠምደዋል። የድግሱ፣ የፌስታውና የካርኔባሉ አይነትና ብዛት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች በቀን አንድ ጊዜ ለመብላት በሚቸገሩበት ሀገር ውስጥ የሚደረግ አይመስልም። ይሔው የፈረደበት የኢትዮጵያ ድሃ ግብር ከፋይ ይህን በብዙ መቶ ሚሊየኖች ብር የሚቆጠር ወጭ ይሸፍናል። ማን ከልካይና ጠያቂ አለ? ሌሎች በህግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ለአንድ ደቂቃ እንኮን በአጠገቡ ዝር እንዳይሉ የሚከለክለው የመንግስት ሚዲያ ይህንን የግፈኞች የውሸት ዲስኩርና ፌሽታ በቀን 24 ሰአት ያጋፍራል። እንጨት እንጨት የሚል ፕሮፖጋንዳ ሊግተን፣ ሊያደነቁረን ይታገላል፡፡ ልብ ብሎ ለተመለከተው ጠቅላላው የወያኔ የጉባኤ ሽርጉድ ከጆርጅ ኦርዌል “የእንስሳት እርሻ” (Animal Farm) የስላቅ ድርሰት ተወስዶ የሚሰራ ትያትር ይመስላል።
የወያኔ መሪዎችና ሎሌዎቻቸው ለሆድ አደሮች እግዚያብሄር እንደ ፀጋ ሰጥቷቸዋል። እፍረትና ይሉኝታ የሚባል ነገር ከልክሎ ፈጥሯቸዋል። ትዝብት አይፈሩም። ህዝቡ አንጀቱ እያረረ እብሪታቸውን ሲመለከት በደስታ ፈንድቆ የሚጨፍር ይመስላቸዋል። ኢትዮጵያን ወደ ፖሊሲያዊ መንግስትነት ቀይሮ የሞተውን አለቃቸውን ለአፍሪካና ለአለም የሚያጎድል መሪ ነው ይሉናል። መለስ በምን ህመም እንደሞተ እንኩዋን አጣርተው የማያውቁ ጀሌዎች ትግል ላይ የተሰዋ ኣርበኛ ኣስመስለው ሲያወሩ አያፍሩም።

ይህንኑ እንዲመሰክርላቸው ከዚህ ቀደም በሙሁር ሸቃጭነት (intellectual prostitution) የገዛ ጎደኞቻቸው ሙሁር ከከሰሳቸው የኮሎምቢያ ሙሁራንም  አንዱን አስመጥተዋል። በነዚህ ሰዎች ግምት መለስ ዜናዊ በግፍ የጨፈጨፋቸው ወገኖቻችን፣ የዝምብ ያህል ክብር የላቸውም።   በእስር የታሰሩት ንጹሃንና ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ወገኖቻችን በነሱ ቤት ሰዎች አይደሉም። እናም ጉባኤው አይናችሁን ጨፍኑልንና እናሞኛችሁ ከሚል  ቡዋልት የተለየ አይደለም።
እንዳለፉት ጉባኤዎች ሁሉ የዚህንም ጉባኤ ተብዬ  ውጤት አስቀድሞ መናገር ይቻላል።አሁንም አይናቸውን አጥበው ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እየሰራን ነው የሚል መግለጫ ያወጡልናል። መለስ ዜናዊ ቀድሞውኑ ራሱን አዋቂ አድርጎ በመሳል ከሱ የተቀራረበ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ጠራርጎ በደካሞች ራሱን ከቦ ከበሮ እያስደለቀ መቆየቱ ለከንቱ የሙት ውዳሴ ጠቅሞታል። እነዚህ ደካማ ጀሌዎች አሁንም ምንም የራሳቸን እውቀት ስለሌለን በሞተው መለስ ራእይ በሚሉት ነገር እንደሚመሩ በጉባኤው መጨረሻ የአዞ እንባ ያለበት መግለጫ ያወጣሉ።
እድገትና ትራንስፎርሜሽን የሚባለው ነገር ከሁለት አመት በኋላ ህብስተመና ከሰማይ ይወርዳል የሚል የጉባኤ ውሳኔም እንሰማለን። መብታቸውን የሚጠይቁ ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራራትና አስጎንብሶ ለመግዛት ይጠቅማሉ የተባሉ መግለጫዎችም በጉባኤው መጨረሻ ይጠበቃሉ። አሸባሪ፣ ጸረ-ልማት፣ አክራሪ፣ ወዘተ ወዮላችሁ ይሉናል። ስልጣንና ስልጣንን መከታ በማድረግ የዘረፉት ሀብት ይቀርብናል የሚል የሚያባንን ፍርሃት ስላደረባቸው ባስፈራሩን ቁጥር ሰላም ያገኙ ይመስላቸዋል። በህዝብ መሃል ልዩነት መፍጠርና አንዱን በአንዱ ላይ ማነሳሳት ሰላም ይሰጠናል ብለው ስለወሰኑ እርስበርሳችን እንድንጋጭ ጥሪ ያቀርቡልናል።
ዛሬም እንዳምና ካቻምናው የነሱ ምቾት ስለጨመረና ስለተመቻቸው ኢኮኖሚው እየተመነደገ ነው እንደሚሉን ይጠበቃል። የህዝባችን ኑሮ የከዘራ ያህል እንኳን ቀና እንዳላለ ህዝቡ ራሱ ያውቀዋል።
ወገን ይሄ ግፍ ለከቱን አልፏል። ከወያኔ አገዛዝ በጎ ነገር መጠበቅ ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ  መሆኑን ካወቅን ውለን አድረናል።
ግንቦት 7 የፍትህ የነትጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ  በሀገራችን ዴሞክራሲ ሰፍኖ በገዛ ሀገር ተዋርዶ መኖር ቆሞ፣ በኩራትና በሰባአዊ ክብር ሁላችንም የምንኖርበት ሀገር ወያኔና ሎሌዎቹ ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው ብሎ ያምናል ። በመሆኑም የወደፊቱ እጣችንና ተስፋችን ያለው በራሳችን መዳፍ  ውስጥ ብቻ  እንደመሆኑ   ለነጻነቱና ለክብሩ ቀናዕ የሆነ ሁሉ በራሱ   አነሳሽነት ትግሉን ለማቀጣጠል መነሳት ያለበት ጊዜው አሁን ነው ።
ከወያኔ በጅጉ የተሻለ ስርዓት የሚገባን ህዝብና ሀገር እንደመሆናችን ህዝባችን  በወያኔ አገዛዝ ላይ በቃኝ በማለት ዛሬውኑ እንዲነሳና ! በየአቅጣጫው ለነጻነት የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን እንዲቀላቀል ግንቦት 7 የፍትህ የነትጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ  የትግል ጥሪውን ያቀርባል!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

    No comments:

    Post a Comment