ተኳሹም ተንኳሹም በዝቷል…
በኢትዮጰያ አየር መንገድ “ካርጎ” ውስጥ የቀን ሰራተኛ ሆኖ የሚሰራ አንድ “ፋራ” ሰውዬ በአራዶቹ የታክሲ ሹፌር እና ወያላ ላይ ሽጉጥ መዝዞ አጓጉል ሊያደርጋቸው ሲቃጣ ወያላ ነፍሴ ተወርውሮ ሽጉጡን ነጥቆታል። ቢሆንም ግን የተቀባበለቺቱ ጥይት አንበሳው ወያላ ጎን ውስጥ ተሰንቅራለች።
ጠቡ የተጀመረው ቦሌ አካባቢ ተኳሹ የተሳፈረበትን ታክሲ ሰራተኞች… ከተመደበላቸው ቀጠና ውጪ ካላጓጓዛችሁኝ ቢል “የሚሰማህ የለም” በመባሉ ነው።
ልብ አድርጉ ባለ ሽጉጡ ሰውዬ የቀን ሰራተኛ ነው። ሽጉጧም ህጋዊ ዕውቅና ያላት ሽጉጥ መሆኗን ፖሊስ ተናግሯል። ይሄ የቀን ሰራተኛ ህጋዊ ዕውቅና ያለው መሳሪያ ምን ሲባል ታጠቀው… እኛም የቀን ሰራተኛ ሆነን ሰርተን እናውቃለን። ታድያ ያኔ እንኳንስ መሳሪያ እና ቀበቶ እንኳ የምንታጠቀው ዕቁብ ጥለን ነበር።
ነገሩ ግልፅ ነው ተኳሹ “ኢህአዴግ ጌታ ነው!” ብሎ ያመነ የተጠመቀ ግለሰብ ነው። አረ ደግሞ እንዳይጣላን ድርጅት ነው እንበለው። የምር ግን፤ እኛ ልብሳችንን እንኳ ለመተኮስ አቅም ባጣንበት በዚህ ሰዓት በየጎዳናው ሽጉጥ የሚተኩስብን ይህ ግለሰብ ስንት እንጀራ ቢበላ ነው…?
እውነቱን ለመናገር ግን ይሄ ተኳሽ እልም ያለ ፋራ ነው። ኢህአዴግዬን ከተፎገረችውም በላይ ያስፎገራት እልል ያለ ፋራ…! (በነገራችን ላይ ፋራ ማለት በዚህ ጽሁፍ አግባብ ሊገባው ሲገባ ያልገባው… የሚል ትርጓሜ ይይዛል)
መንግስታችንስ ምን ነካው…? በየገዳ ጎድጓዳው አስታጥቆ አስታጥቆ ምን ሊያደርገን ፈልጎ ነው? ታስታውሱ እንደሁ ደርግ ኢሰፓም ሊወድቅ አካባቢ እንዲሁ ታጣቂውም ተኳሹም በዝቶ ነበር። አሁንም ደርግ ኢህአዴግ እየተንገዳገደች ነው መሰል ተኳሹም ተንኳሹም በዝቷል…
No comments:
Post a Comment