Translate

Thursday, November 30, 2017

መሀል ኢትዮጵያ – አዲስ አበባ፣ ፍርድ ቤት ውስጥ ህዝቡ በእንባ ይራጫል(መሳይ መኮንን)

Political prisoners in Ethiopia
ፍርድ ቤት ውስጥ ህዝቡ በእንባ ይራጫል። አንድ ሰውነቱ በግርፋት የተዘለዘለ እስረኛ ልብሱን አውልቆ ''እዩት ሰውነቴን። አኮላሽተውኛል። ዘር እንዳይኖረኝ አድርገውኛል።'' እያለ ሲቃና ለቅሶ ባሸነፈው ድምጽ ይማጸናል። ''የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ''ም አለ። ፍርድ ቤቱ በሀዘን ክው ብሎ ቀረ። ሁሉም ተላቀሰ። አሁንም እዚያው አዲስ አበባ ወጣቷ ንግስት 10ሩም የእጆቿ ጥፍሮች ተነቅለው በኪሶቿ ይዛለች። የደረሰባት ቶርቸር መልኳን አገርጥቶታል።
በጉጠት የተነቀሉት ጥፍሮቿን እንድትይዛቸውም አልተፈቀደም። በኋላም በህወሀት ገራፊዎች ተነጥቃለች። የሻሸመኔዋ ሸጊቱም ትናገራለች ''ጆሮዬ እስኪደማ ድረስ ተደብድቤ ተጎድቷል።ግራ እጄ ታሟል። በእግራቸው ነበር የሚረግጡኝ። ጸጉሬን እየጎተቱ ነበር የሚደበድቡኝ።''
ሁለቱ የዋልድባ መናኞች በማዕከላዊ የደርሰባቸው ስቃይና ድብደባ ቃላት አይገልጸውም። የህወሀት ደህንነቶች ሌሊትን አልፈዋቸው አያውቁም። እኚህን ዓለምን የተጠየፉትን መናኞች ዘቅዝቀው በመደብደብ፣ በመዝለፍ፣ በማንቋሸሽ ይህ ነው የማይባል ስቃይ እያደረሱባቸው ነው። ልብሰ ተክህኖአቸውን፡ ቆባቸውን እንዲያውልቁና የእስረኛ ዩኒፎርም እንዲለብሱ ነው ግርፊያውና ስቃዩ። ከዚህ ቀደም አበበ ካሴ አስሩንም ጥፍሮቹን በጉጠት ተነቅለዋል። ወ/ሮ እማዋይሽ ጡታቸው በኤሊክትሪክ ሽቦ ተተልትሏል። ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች በማዕከላዊ ተኮላሽተዋል። ተቀጥቅጠዋል። የስቃይ መዓት ቆጥረዋል። ከትላንት እስከ ዛሬ።
ሰሜን ኢትዮጵያ- መቀሌ
ዝሆኖቹ ረጅሙን ስብሰባ ተቀምጠዋል። የሚያስጨንቃቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም። ጓዛቸውን አስጠቅልሎ ለሁለት ወራት መቀሌ የከተታቸው ስለኢትዮጵያውያን ተጨንቀው ተጠበው አልነበረም። የትግራይን የበላይነት ለተጨማሪ ዓመታት አስጠብቀን እንዴት እንቆያለን? የሚለው ላይ በአካሄድ ተለያይተው እንጂ። 77ቢሊየን ብር ዱቄት ያደረገውን አባይ ጸሀዬን መርቀው፡ አባይ ወልዱን ረግመው ዝቅ አድርገዋል። የማዕከላዊ ሰቆቃ እስር ቤት አዛዥ፡ ናዛዥ፡ ገራፊ አስገራፊ፡ የሆነውን ጌታቸው አሰፋን ሸልመው አዜብን ሸኝተዋል። በየነ ምክሩን አዋርደው፡ ጌታቸው ረዳን ከፍ አድርገዋል። ጉልቻ ቀያይረው፡ ከዝንጀሮ መሀል አንዱን ሊቀመንበር መርጠው፡ ወንበር ተለዋውጠው ከጨረሱ በኋላ ለኢትዮጵያ ህዝብ ''የምስራች፡ ምስር ብላ'' ሊሉት ተዘጋጅተዋል።
ሙስናን ህወሀቶች አላነሷትም። ከመሃላቸው በዚህ ጉዳይ የሚተርፍ አልነበረምና። አቅምና ብቃት ማነስም ለግምገማ አልቀረበም። ሁሉም አቅመ ቢስ፡ የደናቁርት ስብስብ ናቸውና። አባይ ወልዱ የተገመገመው የትግራይ ተወላጆች በአማራ ክልል ጉዳት ሲደርስባቸው የወሰድከው እርምጃ ዝግ ያለ ነው፡ የወሰኑ ጉዳይ መቋጪያ ሳያገኝ ተራዘመ የሚል ነበር። ወልቃይትን በጠራራ ጸሀይ የወሰደው፡ ራያን ከአማራ ነጥቆ ወደ ትግራይ የከለለው፡ ግጨውን እጅ ጠምዝዞ የነጠቀው፡ ከምንም በላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ወጣቶችን በጥይት ደብድቦ የገደለው ህወሀት፡ ለፖኣለቲካ ትርፍ ተብሎ ጭረት ሳይነካቸው በአውሮፕላን ተሳፍረው ወደትግራይ የተወሰዱትን የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ አንገብጋቢ አጀንዳ አድርጎ ነበር ሊቀመንበሩን የገመገመውና ከቦታቸው ያነሳው።
በተንኮልና ሴራ ያላረጀው ስብሃት
የ86ዓመቱ ሽማግሌ በስጋ አርጅቶ፡ በተንኮል ጎልምሶ ዘንድሮም ብቅ ብሏል። በህወሀት የፓርቲም ሆነ በፌደራል መንግስት ውስጥ የያዘው ስልጣን የለም። ሆኖም ከጀርባ መዘወሩን ማሽከርከሩን ከዘመናትም በኋላ አላቆመም። በተንኮል ተፈጥሮ፡ በሴራ አድጎ፡ በሸፍጥ ሸብቷል። የአረቄ ብዛት የተንኮል አቅሙን አላደከመውም። ሰውነቱ ውስጥ በቀን የሚገባው የአልኮል መጠን፡ የአእምሮውን ሴራ የመጎንጎን ክፍል አልጎዳውም። ከ6 በላይ ህንፍሽፍሾችን በአሸናፊነት የተሻገረ፡ ስንቱን የህወሀት አመራር መንግሎ ያስወገደ፡ በስተርጅናም በጥሎ ማለፍ ታክቲክ ሻምፒዮን ሆኖ እየታየ ያለ ሰው ነው። የአጼ ዮሀንስን ዘውድ ያስመለሰ ተብሎ በታሪክ እንዲጻፍለት እየታተረ ያለ፡ ይህቺን ታሪኩን በህወሀት መዘገብ ውስጥ መስፈሩን ሳያረጋግጥ ሞቱን ላይጨልጥ ለራሱ ቃልኪዳን የገባ ለመሆኑም ይነገርለታል። የህወሀት መሀንዲስ ነው። King maker ነው ይሉታል። በእሱ ያልተቀባ ለስልጣን የማይበቃ፡ በሱ የተረገመ ደግሞ ስልጣን የማይበረክትለት ይባልለታልም።
ስብሃት ነጋ ለጊዜው የአሸናፊነት አክሊሉን ደፍቷል። በአልኮል ብዛት ጎሮሮው ሲርርር የምትልበት ስብሃት ከቀን እንቅልፍ ጋር እየታገለ፡ የመቀሌውን ስብሰባ በድል አጠናቋል። በእርግጥ ውስኪ የጠበሰው ፊቱ ደስታውን ደብቆበታል። እንደልማዱ ቀጣዩን የህውሀት አለቃ እንዲሰየም አድርጓል። የሚጠራረጉትን ጠራርጓል። የሚፈልጋቸውን አስገብቷል። በጊዜ እጅ የሰጠው በረከት ስምዖንም ለስብሃት ውዳሴ ማቅረቡ ተሰምቷል።
በእርግጥ ድሉ ጊዚያዊ ነው። ተጀመረ እንጂ አላበቃም። ህወሀት በማይድን በሽታ የተለከፈ፡ ቀኑን እየቆጠረ ያለ ድርጅት ነው። አቶ ገብረመድህን አርዓያ እንዳሉት ህወሀት ሟሙቷል። መሪዎቹም አርጅተዋል። ከተፈጥሮአዊ ሞት በፊት መቃብር የሚወስዳቸው ማዕበል ከደጃፋቸው ደርሷል። ለእነሱ ግን አይታያቸውም።
ከወዲሁ ድለቃው ተጀምሯል። ኢቲቪ የህውሀትን ማላገጫ በሰበር አቅርቦታል። ሪፖርተር በጉጉት የሚጠበቅ ብሎታል። የፓርቲና የመንግስት ሚዲያዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ የብስራት ያህል የመቀሌውን ስብሰባ ውጤት ሊያበስሩ አፋችውን እያሟሹ ነው። የክልል መንግስታት የደስታ መግለጫ እንዲያወጡ ይደረጋል። አጋር፡ አባል፡ አሯሯጭና ደሞዝ ተከፋይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለህወሀት ስብሰባ ስኬት ''የእንኳን ደስ አላችሁ'' መልዕክት ከሰሞኑ ይዥጎደጎዳል። በየከተማው ያለው በሊግ፡ በፎረም፡ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጀ፡ በሴልና በመሰረታዊ ድርጅት መዋቅር የተሰገሰገ ካድሬ በያለበት ሰልፍ ወጥቶ በእልልታና ጭፈራ ለመቀሌው ስብሰባ ውጤት ደስታውን እንዲገልጽ ይደረጋል። በቃ! የኢትዮጵያ ችግር ተፈቷል። ሰንኮፉ ተነቅሏል። ይለናል ሃይለማርያምም በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ።
ከወዲሁ የህወሀት የፌስቡክ ሰራዊት አባላት ቄጤማ እየጎዘጎዙ፡ ዘንባባ እያነጠፉ፡ ፈንዲሻ እየነሰነሱ ናቸው። የህወሀት ስብሰባ ኢትዮጵያውያንን ያስጨነቃቸው ጉዳይ እንዲመስል የሚችሉትን እየተፈራገጡ ነው። አንዳንድ የህወሀት ደጋፊዎችም በዱቄትና አመድ መሃል የሚደረገውን ፉክክር የሂላሪና ትራምፕ ዓይነት አስመስለው ማን ይመረጣል፡ ማን ይወገዳል በሚል ትኩረት እንድንሰጠው እየተሯሯጡ ነው። ያስጨነቀን የሞንጆሪኖ መምጣት፡ እንቅልፍ የነሳን የአዜብ መወገድ፡ ትካዜ ውስጥ የከተተን የጌታቸው ረዳ ስራ አስፈጻሚ ውስጥ መግባት ይመስል አጓጊና ልብ ሰቃይ የሆሊውድ ፊልም አድርገን እንድንከታተለው ተፈልጓል።
የቁጭት ዘመን አልፏል
የኢትዮጵያ ህዝብ ጆሮው ከመቀሌ አይደለም። ይልቅስ ከነጻነት ሃይሎች የድል ዜና ተቀስሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ ቀልቡ የህውሀት ስብሰባ ላይ አልነበረም። ይልቅስ የኦሮሚያ ቄሮዎችን ገድል ፡ የአማራ ፋኖዎችን ተጋድሎ፡ የጋሞጎፋ ጀግኖችን ውሎ፡ በመከታተል ተጠምዷል። የመቀሌው ቲያትር የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ አይደለም። አሁን ዘመን ተቀይሯል። የቁጭት ጊዜ አብቅቷል። የእርምጃ ምዕራፍ አንድ ብሏል። እየተደበደቡ ከቤት መግባት ቀርቷል። እየተገደሉ ማልቀስ አሮጌ ሆኗል። ግራን ሲመቱ ቀኝን መስጠት በትላንት ታሪክ ውስጥ ገብቷል። ሲደበደብ፡ የሚደበድብ፡ ሲገደል፡ የሚገድል፡ ግራውን ሲመቱት፡ መልሶ በጥፊ የሚያጮል ኢትዮጵያዊ ሆ ብሎ ተነስቷል።
ትላንት ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ በአርባምንጭ ከተማ አየር መንገድን ሲጠብቁ የነበሩ 13 ወታደሮች ሙሉ ትጥቃቸውን እንደያዙ ጠፍተዋል። ባለፈው ሳምንት በሞያሌ 38 ወታደሮች ከነትጥቃቸው ለቅኝት እንደወጡ በዚያው ተሰውረዋል። እነሱን ለማሰስ የወጣው ሌላ ሃይልም በተናጠልና በቡድን በርካታ ወታደሮች የገቡበት አይታውቅም። በየግንባሩ ወታደሩ እየከዳ ነው። ወገናችን ላይ አንተኩስም የሚሉ የጸጥታ ሃይሎች ድምጻቸው ከፍ ብሎ መሰማት ጀምሯል። አዲስ የሚመዘገብ ወታደር ሊገኝ አልቻለም። ህወሀት ሰራዊቱ ተስፋ ቆርጦብኛል ሲል ተናዟል።
የኦሮሞ ቄሮዎውች የህውሀትን ዝርፊያ በየከተሞቹ መግታት ጀምረዋል። ስኳር፡ ቡና የጫኑ የህወሀት ተሽከርካሪዎች እርምጃ ይወሰድባቸዋል። ከሰል ጭኖ ሊወጣ የነበረ የሜቴክ ተሽከርካሪ በደሌ ላይ ታግቷል። በባህርዳር ህዝብ ሲገድል ሲያስገድል የነበረው ኮማንደር ደሳለኝ ልጃለም በነጻነት ሃይሎች ተገድሏል። በጋሞጎፋ ሳውላ ግብር አንከፍልም ያሉ ነዋሪዎች የወረዳውን ገቢዎች ጽ/ቤት ዶግ አመድ አድርገዋል። በጋምቤላም የከተማው አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት እንዲቃጠል ተደርጓል። እዚህም እዚያም ህዝቡ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግሯል።
በአጭሩ የቁጭት ዘመን ወጥቷል። የእርምጃ ዘመን ገብቷል። ህወሀቶች ጉልቻ ብትቀያየሩ፡ ከመሃላችሁ አንድ መርጣችሁ አለቃ ብትሰይሙ፡ ብታስወግዱ፡ ብትሾሙ የራሳችሁ ጉዳይ ነው---ብሏል የኢትዮጵያ ህዝብ።
የትግራይ ህዝብ ሚና
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚዘዋወር በኢትዮቲዩብ የቀረበ የአንዲት የትግራይ ወ/ሮ ቃለመጠይቅ እያቃረኝም ቢሆን ሰማሁት። የትግራይን ህዝብ በዚህች ሴትዮ ሚዛን ላስቀምጥ አልችልም። በሷም መነጽር የትግራይን ህዝብ መመልከቱ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ሆኖም እንደዚህች ዓይነቶቹ ሰዎች የጎረበጠውን ይበልጥ የሚያሻክሩ፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በጥርጣሬ ውስጥ የሚደፍቁ በመሆናቸው ጉዳታቸው የትየሌለ ነው። ስለትግራይ ህዝብ ዝምታ አጥብቆ እየተጨነቀ ያለውና ይሄ ህዝብ ራሱን ህወሀት ከተሰኘ የዘራፊዎችና ነፍሰገዳዮች ቡድን ነጥሎ እንዲቀርብ እየጠየቀ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ የእነዚህ ዓይነት ሰዎችን በድንቁርና የተለወሰ ንግግር ሲሰማ ስለትግራይ ህዝብ ተስፋ እንዳይቆርጥ እሰጋለሁ።
በእንግሊዝ የህውሀት ደጋፊዎች የመቀሌው ስብሰባ መቋጨቱን ተከትሎ መግለጫ አውጥተዋል። ዘራፍ ብለዋል። አጆሃ፡ ጀግናው ወያናይ፡ እንደብረት የጠነከረ የማይገረስስ ሲነኩት የሚያርድ ተራራን ያንቀጠቀጠ ዓይነት ፉከራና ቀረርቶ አሰምተዋል። እነዚህ ዘረኝነት ከደማቸው ሰርጾ ከአጥንታቸው የገባባቸው የህውሀት ደጋፊዎች በመግለጫቸው እንዲህ የሚል አስፍረዋል ‘’ሁሉም ነገር ወደትግራይ እየሄደ ነው; የትግራይ ተወላጆች ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝበ የበለጠ ጥቅም ያገኛሉ እየተባለ የሚወራውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ ትክክል እንዳልሆነ የሚያስረዱ መረጃዎች ወደ ህዝብ እንዲቀርቡ::’’
የህወሀት ደጋፊዎች ዘረኝነት ልቦናቸውን ስለጋረደ ለማስተዋል የሚያስችል ጠብታ አቅምም የላቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖርበትን እውነት በፕሮፖጋንዳ ጭነት ለመለወጥ መፍጨርጨራቸው አስገራሚ ነው። አሁንም እነዚህን በሌላው ኪሳራ ምቾትና ድሎታቸውን አስጠብቀው እሰከመጨረሻው ለመዝለቅ ቅንጣት ታክል የማይሰቀጥጣቸውን ሰዎች ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ አድርጎ መውሰድ ስህተት ላይ ይጥላል። ነገር ግን በቋፍ ላይ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ዓይነቱ ጭፍንነት ስለትግራይ ህዝብ ጥያቄ እንዲያነሳ ይገፋፋዋል። በውጭ ሀገራት በየፓል ቶኩ፡ የየአከባቢ ሬዲዮ ጣቢያዎች፡ በድረገጾች በትግራይ ህዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያበሻቅጡ ጥቂት የትግራይ ጽንፈኞች ድምጻቸው ጎልቶ የሚሰማ በመሆኑ በወደፊቱ የትግራይ ህዝብ አብሮነት ላይ ግርዶሽ እንዳይጥሉ በእርግጥም እሰጋለሁ።
እናም የትግራይ ህዝብ ዝምታውን መስበር አለበት። መቀሌ ላይ ለሁለት ወራት የተጎለተው የዘረኞች ስብስብ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን ግፍና መከራ በአስቸኳይ እንዲያቆም መጠየቅ መጀመር ይጠበቅበታል። በማዕከላዊ፡ ቂሊንጦ፡ ቃሊቲ፡ ዝዋይና በተለያዩ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ስቃይ እያየ ያለው ወገናቸው፡ መቀሌ በተሰብሰቡትና በስሙ በሚነግዱት ጥቂቶች ትዕዛዝ የሚፈጸም በመሆኑ ይህ እንዲቆም ያደርግ ዘንድ የትግራይ ህዝብ ውሳኔው ይጠበቃል። ጊዜው እየረፈደ ነው።
በመጨረሻም
የሀራሬ ሰማይ ፈክቷል። ምድሩ በተስፋ ለምልሟል። ሀራሬ በጭፈራ ላይ ናት። በደስታ ሰክራለች። የአንድ ሰው ፊት እያየ ያደገው 2 ትውልድ ዛሬ ጮቤ እየረገጠ ነው። የዚምቧቡዌ አየር በነጻነት ጠረን ታውዷል። ዛሬ ልዩ ቀን ናት። የ37 ዓመቱ የሙጋቤ ዘመን አክትሟል። የ93ዓመቱ አዛውንት በመጨረሻው ሰዓት ከውርደት ስንብት ተርፈዋል። የሙጋቤ ነገር በታሪክ ማህደር ሰፍሮ ፋይሉ ተዘግቶ መደርደሪያ ላይ ተሰቅሏል። አዲስ ቀን፡ አዲስ ዚምቧቡዌ።
የኢትዮጵያም ሰማይ በጉም ጠቁሮ አይቀርም። ከዚህ በላይ ምድሯ በተስፋ ጥም እንደገረጣ አይዘልቅም። በየከተሞቿ ልጆቿ በአጋዚ ጥይት መውደቃቸው ይቆም ዘንድ ጊዜው ደርሷል። ኢትዮጵያ የለበሰችውን የሀዘን ከል ታወልቃለች። ዘረኛው፡ ቅጥረኛው፡ ወንጀለኛው፡ መንግስታዊ አሸባሪው ስርዓትን እያየ ያደገው ትውልድ መድረሻ አጥቶ መንከራተቱም ያበቃል። ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ እንደ አልቅት ተጣብቆ ላለመውረድ የሚንገታገተው የህወሀት ቡድንም በህዝብ ማዕበል ተጠራርጎ የሚወግድበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። አዲስ ቀን፡ አዲስ ኢትዮጵያ በቅርብ ቀን።
ባዶ ምኞት አይደለም። ሰማይ ላይ የተሰቅለ የማይደረስ ተስፋም አይደለም። አፍንጫዬ ስር የሚሸተኝ የነጻነት መዓዛ እንጂ።
ፈጣሪ እግዚያብሔር ውድ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ይባርካት

No comments:

Post a Comment