ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኦህዴድ መንደር የሚታየው ነገር የተለየ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ለመግለጽ ትንሽ ወደኋላ መንደርደር ግድ ይላል። በ1982ዓም የኦሮሞን ህዝብ ለመቆጣጠር እነ መለስ ዜናዊ ሰሜን ሸዋ ደራ ላይ ጠፍጥፈው የሰሩት፡ ሳምባና ልቡ በህወሀት ቁመና ልክ የሚተነፍስና የሚመታ ድርጅት መሆኑ የአገላለጽ ልዩነት ካልሆነ በቀር በድርጅቱ የታሪክ ድርሳን ላይ የተጻፈ እውነት ነው።
ሻዕቢያ በምርኮ በያዛቸውና በኋላም ለህወሀት በጉዲፈቻነት በተሰጡት የደርግ ወታደሮች የተመሰረተው ኦህዴድ ባለፉት 26 ዓመታት የህወሀት ቅርንጫፍ ሆኖ ትዕዛዝ ከመቀሌ እየተቀበለ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ተፈናጦ መክረሙም የአደባባይ ሀቅ ነው። ለሩብ ክ/ዘመን የኦሮሞ ህዝብ በኦነግ ስም በጅምላ እስር ቤት ሲጋዝ፡ በየመንደርና ጫካው ሲገደል፡ በየማጎሪያ እስር ቤቱ ፍዳ መከራውን ሲበላ ኦህዴድ በስሙ እየማለ ፡ በግብር እየገደለ ከህወሀት ጎን ተሰልፎ ቆይቷል። ስለዚህ ጉዳይ በርካታ ጸሀፊያን ብዙ ነገሮችን ስለጠቀሱ ከዚህ በላይ መግፋት አያስፈልግም። በአጭሩ ግን ኦህዴድ ፈጣሪውና ጌታው ህወሀት መሆኑን፡ ሲያገለግል የከረመውም ህወሀትን እንደሆነ ማስታወስ ይገባል።
አሁን ኦህዴድ ጥርስ አብቅሏል የሚሉ ሰዎች በርክተዋል። ከፈጣሪው መንጋጋ ተላቋል፡ ከጌታው ባርነት አምልጧል፡ በራሱ ቆሞ መገዳደር የሚያስችለው ቁመና ላይ ይገኛል፡ የሚሉ አስተያየቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበላይነትን የያዙ መሆኑን መታዘብ ይቻላል። በተለይ ሶስቱ አመራሮች የኦህዴድንና የኦሮሚያ ክልል መንግስትን በበላይነት ከያዙ በኋላ ኦህዴድ ከተከታይነት ወደ መሪነት አድጓል የሚለውን የሚቀበሉ ጥቂቶች አይደሉም። አቶ ለማ መገርሳ፡ ዶ/ር አብይ አህመድና አቶ አዲሱ አረጋ ስማቸው ገኖ ወጥቷል። በማህበራዊ መድረክ ከኦሮሞ አክቲቪስቶች በተጨማሪ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ስለነዚህ ግለሰቦች አብዝተው መወያየት የጀመሩ ሲሆን ድጋፋቸውንም መስጠታቸው ይታያል።
በእርግጥ ኦህዴድ መንደር የሚታየው ነገር ባለፈው ሩብ ክ/ዘመን ከነበረው የሚለይ መሆኑ እርግጥ ነው። ያልተለመዱ ነገሮች እየሆኑ ነው። በግሌ የታዘብኩትም ኦህዴድ ከህወሀት መዳፍ ፍልቅቆ ለመውጣት ምልክት ማሳየቱን ነው። ጆሮ በሌለው፡ መናገር እንጂ መስማት ባለፈጠረበት የኢህአዴግ ስብስብ ውስጥ የከረመው ኦህዴድ መስማት መጀመሩን፡ ጆሮም እንዳለው ማሳየቱን እየተመለከትን ነው። ለእኔ ከምንም በላይ ከኦህዴድ የወቅቱ መሪዎች አንደበት የሚወጣው ነገር ምቾት የሚሰጡኝ ናቸው። ከአንጀትም ይሁን ከአንገት ብቻ የምንሰማው ንግግር ልብን የሚከፍት ነው። አይጎረብጥም። አይቆረቁርም። ኢትዮጵያዊነትን ከሲኒና ጀበና ጋር እያነጻጸረ በሚያላግጠው የጽንፈኛው የኦሮሞ ብሄርተኛ ጩሀት በተጨናነቀው መንደር የእነ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያዊ መልዕክቶች እፎይታን የሚሰጡ፡ ተስፋንም የሚያጭሩ መሆናቸውን መካድ አይገባም።
በአንጻሩ የኦህዴድን አዲሱን አካሄድ በጥርጣሬ የሚመለከቱት ጥቂቶች አይደሉም። ህወሀት የኦሮሞ ህዝብን የማያቋርጥ፡ እየጠነከረ የመጣን ተቃውሞ ለመደፍጠጥ የቆመራት ስሌት እንዳትሆን የሚል ውሃ የሚያነሳ ሀሳብ የሚሰነዝሩም በርካቶች ናቸው። በገመድ ተለክቶ፡ አንገት ላይ በሸምቀቆ ታስሮ የተሰጠ ነጻነት ነው የሚሉት ወገኖች በተለይም ኦህዴድ የትኛውን ሃይል ተማምኖ ነው ህወሀትን የሚገዳደረው ሲሉ ይጠይቃሉ። መከላከያው፡ ደህንነቱ፡ ቢሮክራሲው በህወሀት የአንድ መንደር ልጆች የበላይነት በተያዘበት ሁኔታ የኦህዴድ ጉልበት ከየት የመጣ ነው የሚለውን መከራከሪያ ይጠቅሳሉ። ህዝብ ሃይል ነው፡ የህዝብ ጉልበት ከየትኛውም የጦር ሃይል በላይ ነው የሚለው እውነት ቢሆንም እንደ ህወሀት ዓይነት ፍጹም ጸረ ህዝብ በሆነ አገዛዝ ስር ባለች ሀገር ውስጥ የህዝብ ጉልበት ብቻውን ለውጥ አያመጣም ሲሉም ይሞግታሉ። በተለይም የአሁኖቹ የኦህዴድ መሪዎች የጀርባ ታሪካቸውን የሚያስታውሱ ወገኖች ዛሬ በምን ተአምር የነጻነት አርበኛ፡ የለውጥ ሃዋሪያ ይሆናሉ ሲሉም ጥርጣሪያቸውን ያጠናክራሉ። ህወሀት እንደቀደመው የኦሮሞን ህዝብ ተቃውሞ በሃይል ጨፍልቆ ማለፍ እንደማይችል ሲረዳ በሌላ አማላይ፡ አታላይ በሆነ ጊዜያዊ ድል ለማዘናጋት የጎነጎናት ሴራ መሆኗን በመጥቀስ ልባቸውን ለኦህዴድ አዲሱ መስመር ጥርቅም አድርገው የዘጉ ወገኖች ድምጻቸው ጎልቶ እየተሰማ ነው።
የኦህዴድን ጥርስ ማብቀል የማይቀበሉ ወገኖች ጥርጣሪያቸው ተዘርግቶ ከባህር ማዶ ይሻገራል። በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚዘባበቱ፡ በልባቸው መንግስት መስርተው ዘውትር የጥላቻ መዝሙር የሚያቀነቅኑ ከአትላንቲክ ማዶ ያሉ ጽንፈኞችና በኢትዮጵያዊነት መልዕክቶቻቸው መድረኩ ላይ ብቅ ያሉት የኦህዴድ መሪዎች አንድ መስመር ላይ ያገናኛቸው ጉዳይ ምንድን ነው ሲሉ ይጠይቃሉ። እነዚህ ወገኖች በተለይ ትላንትናና ዛሬ የሆኑ ሁለት ጉዳዮችን በመጥቀስ የኦህዴድ አዲሱ መስመር ዕድሜ የሌለው፡ ተቃውሞ ለማስተንፈስ እንጂ ከዚያ ያለፈ ተጽእኖ የለውም ይላሉ። የትግራይ መስተዳድር እጅ ጠምዝዞ የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክን ይቅርታ ማስባሉን፡ የአቶ በቀለ ገርባን በዋስ የመፈታቱ ውሳኔ መታገዱን የሚጠቅሱት እነዚህ ወገኖች ከህወሀት ፍቃድ ውጪ ለኦህዴድ ከዚህ በላይ እንዲጋልብ አልተፈቀድለትም በማለት አቋማቸውን ያስቀምጣሉ። ግፋ ቢል ህውሀት አቶ ለማን ጠ/ሚር እሰከማድረግ ድረስ ሊዘልቅበት እንደሚችል በመገመት በየትኛውም መለኪያ ህወሀት አሸናፊ ለመሆን እንደሚችልም ይገልጻሉ። በቅርቡም እነለማ የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንዳጠናቀቁ ወደቀድሞው ታዛዥነታቸው ይመለሳሉ፡ ወደሰገባቸው ገብተው የህወሀት አስፈጻሚነታቸውን ይቀጥላሉ ብለውም መስመራቸውን ያጠናክራሉ። ለኢትዮጵያ እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው ጌታውና ባርያዎቹ ሳይነጣጠሉ ተያይዘው፡ ተጠራርገው ሲወገዱ ብቻ ነው የሚል የመፍትሄ ሀሳብ ያስቀምጣሉ።
ሌሎች ወገኖችም አሉ። የእነ ለማን ጥርስ ማብቀል ከወደፊቷ ኢትዮጵያ ጋር በማማያዝ ስጋትና ተስፋቸውን የሚገለጹትም ድምጻቸው ይሰማል። እነዚህ ወገኖች የህወሀትን መዳከምና አቅመ ቢስነት ይቀበላሉ። የእነለማን ጡንቻ መፈርጠምም የእውነት አድርገው ያምናሉ። በህወሀት መዳከም ተስፋን፡ በእነለማ ብቻቸውን እየጎሉ መምጣትን ስጋት የሚፈጥርባቸው ናቸው። የእነዚህ ወገኖች ስጋት የእነለማ ጉዞ መጨረሻው ዘረኝኛ ስርዓትን በሌላ ዘረኛ ስርዓት የሚተካ እንዳይሆን የሚል ነው። ላለፈው ሩብ ክ/ዘመን የህውሀት ስርዓት የበተነው የዘረኝነት መርዝ ባልመከነበት ሁኔታ ከክልል የተሻገረ ዕይታ የሌለው ኦህዴድ ብቻውን ጥርስ ማብቀሉ ለሀገሪቱ በጎ አይሆንም ነው ስጋታቸው።
በእርግጥ የእኔ ዕይታ የሁሉንም ወገኖች የሚጋራ ነው። እነለማን ሁሌም አሽከር፡ ሁሌም ታዛዥ የሚለው አካሄድ የምቀበልው አይደለም። እነለማን የለውጥ ሀዋሪያ አድርጎ ከሚያመልከው ጎራም አልስማማም። በተለይ ከህወሀት መዳከም አንጻር እነለማ የጀመሩት መንገድ በህወሀት አሸናፊነት ይጠናቀቃል የሚል እምነት የለኝም። ሁሌም ህወሀትን የምይገረሰስ፡ ጠንካራ፡ ውስብስብ ፓርቲ አድርጎ መቀበል በራሱ ተሸናፊነት ነው። ዘላለሙን በባርነት የኖረ ሰው በባርነት ከመሞት ውጪ ምርጫ የለውም የሚለውን ድፍን ያለ ሀሳብ አልቀበለውም። ጌታው ላይ የሚያምጽ ባርያ ይኖራል። በባርነት ኖሮ በነጻነት የሚሞት ስንት ጀግና አይተናል። እነለማ ይሄን የህዝብ ድጋፍ ይዘው ከእንግዲህ የህወሀት ባሪያ ለመሆን ይፈቅዳሉ ብዬ ለማሰብ ይከብደኛል። ስጋው አልቆ፡ በአጥንቱ ብቻ የቀረውን የህወሀትን ስርዓት ከዚህ በኋላ ለማገልገል የሚፈቅድ ካለ እሱ ባርነትን ጸጋና በረከት አድርጎ የተቀበለ ብቻ ነው።
እነለማ የሚናገሩትን ብቻ ከወሰድን ምቾት ይሰጣል። በቅርቡ ወደጣና ሀይቅ የሄዱትና የእምቧጭን አረም ነቅለው አንድነትንና ፍቅርን የተከሉት የኦሮሞ ልጆች ጉዞ በእነለማ ቢሮ የተዘጋጀ መሆኑ ይነገራል። ይህ ቀላል የማይባል ውጤት ያመጣ ጉዞ ነው። የህወሀትን የ25 ዓመታት ተንኮል በአንዲት ጀንበር ያከሸፈ ጉዞ። እነለማ ባገኙት መድረክ የሚናገሩት ኢትዮጵያዊነት ከአንጀት ይሆን ዘንድ ምኞቴ ነው። መሪዎች የሚናገሩት ከአንገት እንኳን ቢሆን የሚፈጥረው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
እነለማ የለውጥ ሀዋርያ መደረጋቸው ተገቢ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ እያደረገ ያለው ትግል ከኦህዴድ እጅ መውደቅ የለበትም የሚል እምነት አለኝ። እነለማ ህወሀትን የማዳከም ተልዕኮአቸው በቂ ነው። ለዓመታት ከህወሀት ጋር ተሰልፈው የረጩትን መረዝ ካመከኑ እንደውለታ ይቆጠርላቸዋል። የተዳከመውን ህወሀት ወደ መቃብሩ በመውሰዱ ትግል ላይ አስተዋጽኦ ካደረጉ እሰየው ነው። ከዚያን በኋላ ሃጢያታቸውን በሰማይ ቤት እንዲሰረዝ እንጸልይላቸዋለን። በምድርም ይቅርታችንን አንነፍጋቸውም። ከዚያ ያለፈ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የለውጥ ሃይሎች ተደርገው መወሰዳቸው አደጋ እንዳለው መዘንጋት የለብንም።
የማጠቃለያ ሀሳብ
የኦህዴድ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው። እነለማ በዚህ ኮንፍረንስ አንድ ነገር ቢያሳዩ ከምር ልንወስዳቸው እንገደዳለን። በተለይ ከህወሀት ባርነት ለመላልቀቅ ያሳዩትን ፍንጭ መሬት በረገጠ እርምጃ ያረጋግጡ ዘንድ ይህን ኮንፍረንስ እንደመልካም እድል መጠቀም አለባቸው።በህወሀት ሳምባ የማይተነፍሱ መሆናቸውን የማረጋገጥ የቤት ስራ ተሰጥቷቸዋል። የተለመደ የጉባዔ ጋጋታና ዲስኩር አድርገው ካጠናቀቁት የሚጠራጠሯቸውን ወገኖች ልብ ይበልጥ እያጡ መሄዳቸው አይቀርም። ህወሀት ሊቧጨር ይችላል። ሊናከስ ጥርሱን ስሎ መምጣቱ አይቀርም። ያን ጊዜ የእነለማ አቋም ይፈተናል። አለበለዚያ ጭራቸውን ቆልፈው የህወሀት እግር ስር የሚወተፉ ከሆነ አዲዮስ!!!
ሌላው የኢትዮጵያ ሃይል የእነለማን ጉዞ ከማደናቀፍ ይልቅ የጋር ጠላት በሆነው የህወሀት ስርዓት ላይ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ላይ ተጋባዥ ሆኖ እንዲጠራ መጠበቅ ትልቅ አደጋ ነው። በእኩል መሪ ተዋናይ በመሆን ለመጪዋ ኢትዮጵያ ከድሉም ከመስዋዕትነቱም መካፈል ሃገራዊ ሃላፊነት ነው። እነለማ ብቻቸውን እንዲሮጡ መፍቀድና ዳር ይዞ መመልከት መዘዝ አለው ። በእርግጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ከህወሀት የበለጠ ጭራቅ ይመጣል የሚል ስጋት የለኝም። ህወሀትን መገላገሉ የቅድሚያ ትኩረት ቢሆንም ከወዲሁ የለውጡ አካል ለመሆን መነሳት ከሌላው የኢትዮጵያ ሃይል ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment