Translate

Wednesday, November 8, 2017

እነ አላሙዲ በሳዑዲ “ቂሊንጦ”


ቅዳሜ ማታ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የሳዑዲ ልዑላንና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም አላሙዲ መሬት ላይ ተኝተው የሚያሳይ ፎቶ ዴይሊ ሜይል በድረገጹ ላይ ለቋል። “ቂሊንጦ” በሚሰኝ ሁኔታ “አገልግሎት” እየተሰጣቸው እንደሆነ ከዴይሊ ሜይል ዘገባ ለመረዳት ይቻላል።

“ከሳዑዲ መንግሥት ምንጮች የተገኘ” በማለት ዴይሊ ሜይል የለቀቀው ይህ ፎቶ እንደሚያሳየው አይነኬዎቹ እነ ልዑል አልዋሊድ (የእኛን ጉድ አላሙዲንን ጨምሮ) በሥሥ ፍራሽ ላይ ሪትዝ ካርልተን ሆቴል መሬት ላይ ተኝተው ይታያል። ጋዜጣው ሲያላግጥም “የሳዑዲ ልዑላን ባለ አምስት ኮከብ እስርቤት ውስጥ” በማለት ለዘገባው ርዕስ ሰጥቶታል። ጋዜጣው ሁኔታውን “የሚያሳፍር” በማለት የጠቀሰው ሲሆን በትንሽ ብርድልብስ ተጠቅልለው ለዚህ ውርደት መብቃታቸው ቢፈቱ እንኳን ውርደቱን ተቀብለው ለመኖር የሚያቅታቸው እንደሆነ አስተያየት ተሰጥቶበታል።
ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ ባይታወቅም ምርመራው እየተካሄደ በዚህ መልኩ ለሳምንታት ሊቆዩ ይችላሉ የሚል ግምት ይሰጣል። (የጋዜጣው ሙሉ መረጃ እዚህ ላይ ይገኛል)
ሰኞ ዕለት የሳዑዲ መንግሥት እንዳስታወቀው የግለሰቦቹ የባንክ ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ ይደረጋል፤ ሃብታቸውም የሳዑዲ መንግሥት ንብረት ይሆናል በማለት መግለጫ ሰጥቷል።
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ

ደላላው “ባለሃብት” አል-አሙዲ በቁጥጥር ሥር ውሏል!

  • “ማንንም አንፈራም!” ንጉሥ ሳልማን
የሳዑዲ የዙፋን ተስፈኛ አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን 11 ልዑላንን እና 38 የመንግሥት ባለሥልጣናትን (የቀድሞውን ጨምሮ) እንዲሁም የንግድ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዋሉ። ደላላ (ተጠሪ ወይም front man) ባለሃብት እንደሆነ የሚነገርለት በግማሽ ኢትዮጵያዊ የሆነው ሞሐመድ አላሙዲ (አል-አሙዲ) በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል መሆኑን ጎልጉል አረጋግጧል። ንጉሥ ሳልማን የሕዝብን ንብረት የመዘበረ ማንም ሰው ተጠያቂ ይሆናል፤ “ማንንም አንፈራም” ብለዋል። ዜናው የተወሳሰበ ትስስር ያላቸውን የአላሙዲ “ወዳጆች” ከፍተኛ ሥጋት ላይ ጥሏል።
ልዑል አልዋሊድ ቢን ጣላልና ባለቤታቸው (የፎቶው ባለቤት Jasper Juinen/Getty Images)
ዜናው በመንግሥታዊው የዜና ወኪል አል-አረቢያ ከተዘገበ በኋላ በተለያዩ ምዕራባዊ የሚዲያ ውጤቶች እንደተነገረው ድርጊቱ “ፈጽሞ ያልተጠበቀ” እና በርካታዎችን “ያስደነገጠ” ሆኗል። በሃብታቸው አይነኬነት የሚታወቁት ልዑል አልዋሊድ ቢን ጣላልን (እንደ ፎርብስ ዘገባ የ17ቢሊዮን ዶላር ባለሃብት ናቸው) ጨምሮ ሌሎች 10 ልዑላን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው አዲሱ አልጋ ወራሽ ወደ ዙፋን የሚደርጉትን ጉዞ የተቃና ለማድረግ የተወሰደ ነው ተብሏል። ከተያዙት መካከል የደኅንነቱ ኃላፊ ሚጤብ ቢን አብደላም እንደሚገኙ ታውቋል።
በሳውዲ አረቢያ ለውጥ መካሄድ እንደሚያስፈልግ እና ለዚህም ገጣሚ ናቸው በሚል የሳዑዲው ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ አል ሳውድ ቁጥራቸው ከማይታወቀው ሚስቶቻቸው ከተወለዷቸው ልጆች መካከል የ32ዓመቱን ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማንን አልጋወራሽ አድርገው ከሾሙ በኋላ በሳውዲ ለውጦች እየተካሄዱ ነው። የሳዑዲ ሃብት ከነዳጅ ወደሌሎች የኢኮኖሚ ውጤቶች ማደግ አለበት በሚል ራዕይ 2030ን አንግበው የተነሱት አልጋ ወራሹ ወደ ዙፋን በሚደርጉት ጉዞ መንገዳቸው ላይ “ዕንቅፋት” የሚሆኑትን ማስወገድ ይዘዋል።
ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን
የለውጡና የተሃድሶው ዋነኛ ደጋፊ የሆኑት ንጉሥ ሳልማን በቅርቡ ባቋቋሙት የጸረሙስና ኮሚቴ አልጋወራሽ ሳልማንን ኃላፊ አድርገው ከሾሙ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ነበር በቁጥጥር የማዋል ዘመቻው ተግባራዊ የተደረገው። እንደ አል-አረቢያ ዘገባ ከሆነ፤ ይህ በንጉሡ የተቋቋመው “የጸረሙስና ኮሚቴ ሞሳኝ ነው ብሎ ያመነበትን የማንንም ንብረት የመመርመር፣ የመያዝ (በቁጥጥር ሥር የማዋል)፣ የጉዞ ዕገዳ የማድረግ፣ ወይም ንብረቱ እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ” ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ይህ “ኃያላንን” በቁጥጥር ሥር የማዋል ዘመቻ በተወሰነ መልኩ ከአሜሪካ የውስጥ ፖለቲካ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ጎልጉል ያገኘው መረጃ ያስረዳል። ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሆኖ የተዘገበው መረጃ እንደሚያመለክተው በቅርቡ የዶናልድ ትራምፕ ሴት ልጅ ባለቤት ያሬድ ኩሽነር ከዕድሜ አቻው አልጋወራሽ ልዑል ሳልማን ጋር በሳዑዲ ያካሄደው ውይይት እንደ አስረጅነት ይጠቀሳል። ኩሽነር የፕሬዚዳንቱ አማካሪ እንደመሆኑ ጉብኝቱ በምሥጢር መያዙና ከስድስት ቀናት በፊት ይፋ መሆኑ በርካታ መላምት እንዲሰጥበት አድርጓል።
ከዚህ ሌላ ዶናልድ ትራምፕ ለምርጫ በሚወዳደሩበት ወቅት ከይነኬው ባለሃብት ልዑል አልዋሊድ ቢን ጣላል (በሲቲግሩፕ፣ ኧፕል፣ ትዊተር፣ ሊፍት ወዘተ ውስጥ ከፍተኛ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው) ጋር የነበራቸውን ቁርሾ የሚያነሱ አሉ። በምርጫው ውድድር ወቅት ልዑሉ ዶናልድ ትራምፕን “ለሪፓብሊካን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ለመላው አሜሪካ ኃፍረት (ውርደት) ነህና በጭራሽ ስለማታሸንፍ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ራስህን አግልል” በማለት የትዊተር መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
ትራምፕ ሲመልሱም፤ “ደንቆሮው (በዕጽ የደነዘዘው) ልዑል አልዋሊድ ጣላል በአባቱ ገንዘብ የአሜሪካንን ፖለቲከኞች ለመቆጣጠር ይፈልጋል። እኔ ስመረጥ ይህንን ማድረግ አይችልም” ብለው ነበር። በበቀለኝነታቸውና ጠላቶቻቸውን ጊዜ ጠብቀው በማዋረድ፣ ድባቅ በመምታት የሚታወቁት ትራምፕ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ያለፈውን ቁርሾ አሁን በተግባር ፈጽመውታል የሚሉ አሉ።
ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን አስቀድመው የተመለከቱት ልዑል አልዋሊድ የትራምፕ መመረጥ ይፋ እንደሆነ ወዲያውኑ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት እንዲህ የሚል የአጸፋ ምላሽ ሰጥተው ነበር፤ “ያለፈው ልዩነታችን ምንም ይሁን የአሜሪካ ሕዝብ ተናግሯል፤ እንኳን ደስ አለዎት፤ በፕሬዚዳንታዊ ዘመንዎ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ።”
“በሳዑዲ አረቢያ ታሪክ ተፈጽሞ አያውቅም” በማለት የሚናገሩ፤ ይህ የማጽዳት ዘመቻ ንጉሡ ቅዳሜ ዕለት የጸረሙስና ኮሚቴ መቋቋሙን በተናገሩበት ወቅት ጉዳዩ “የራሳቸውን የግል ጥቅም ከሕዝቡ ጥቅም በማስበለጥ በሚበዘብዙ አንዳንድ ደካማ ሰዎች” ዋንኛው ትኩረቱ እንደሚሆን መናገራቸውን ይጠቅሳሉ። ኮሚቴው እኤአ በ2009ዓም ለመቶ ያህል ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን የመካከለኛው ምስራቅ የመተንፈሻ በሽታ (MERS) አስመልክቶ የመንግሥት ኃላፊነትና በቫይረሱ መከሰት የተፈጸመውን ደካማ እርምጃ ይመረምራል። በኃላፊነት የሚጠየቁትንም በቁጥጥር ሥር ያውላል። ከዚህ ሌላ ከመቶ በላይ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን በ2009 በሳዑዲ (ጂዳ) የደረሰውን የጎርፍ አደጋ በተመለከተ ከመንግሥት የተሰጠውን የአጸፋ እርምጃ ደካማነት በመመርመር ተጠያቂዎችን ለፍርድ ያቀርባል።
ማንኛውንም የማሰር፣ የመያዝ፣ ወዘተ ሥልጣን የተሰጠውን ኮሚቴ አስመልክተው ንጉሥ ሳልማን በሳዑዲ ቲቪ ላይ እንደተናገሩት፤ “የሕዝብን ገንዘብ በነካ፣ በመዘበረ፣ ወይም እንዳይሰረቅ ባልተከላከለ ወይም ሥልጣኑን ተጠቅሞ (ይህንን ዓይነት ተግባር በፈጸመ) በማንኛውም ግለሰብ ላይ ሕጉ በጽናት ተግባራዊ ይደረጋል። ይህ የሚፈጸመው በትልልቆቹም ሆነ በትንንሾቹም ላይ ይሆናል፤ ማንንም አንፈራም” ብለዋል።
የንጉሡን ንግግር ተከትለው አልጋወራሹ ልዑል “ማንም በሙስና ውስጥ የሚገኝ ሚኒስትርም ይሁን ልዑል ማንም ከሕግ በላይ እንደማይሆን ላረጋግጥ እወዳለሁ” በማለት መናገራቸውን አልአረቢያ ዘግቧል
ተጠርጣሪዎቹ ባለ አምስት ኮከቡ ሪትዝ ካርልተን (Ritz Carlton) ሆቴል በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙና ሆቴሉ እስከ ዲሴምበር 1፤ 2017 ድረስ ምንም ዓይነት ክፍት ቦታ እንደሌለው፤ ክፍሎቹ በሙሉ የተያዙ መሆናቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። እንደ ዜና ዘገባው ከሆነ ይህ የሚያሳየው ይህንን ባከለ ከፍተኛ ደረጃ የሚካሄድ ምርመራ ለሳምንታት ያህል እንደሚወስድ አመላካች ነው ብሏል። ግለሰቦቹ ከሳምንታት ወይም ከቀናት በኋላ የመፈታት ዕድል ቢገጥማቸው እንኳን ባሁኑ የገጠማቸው ኃፍረት ሊሸከሙት የማይችሉት እንደሆነ ይነገራል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የልዑል አልዋሊድ በቁጥጥር ከመዋል ተያይዞ ከሃብታቸው 750 ሚሊዮን ዶላር መጠረጉን ሲኤንኤን ዘግቧል
እነ ልዑል አልዋሊድ ካላቸው ዓለምአቀፋዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ሃብት ጋር ሲነጻጸር የሽልንግ ያህል እንደሆነ የሚቆጠረው የአላሙዲ ስም በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል “ሞሐመድ አል-አሙዲ፣ ነጋዴ” በሚል የመጨረሻው መስመር ላይ በሮይተርስ ተጠቅሷል። ዜናው ይፋ እንደሆነ በርካታዎችን ያስደነገጠ ከመሆኑ አኳያ ወዳጅና ደጋፊዎቹ እንዲሁም “ከእጃቸው የበላን” ያሉትን ጨምሮ ማስተባበያ ለመስጠት የተሞከረበት ቢሆንም ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣየዲፕሎማቲክ ምንጭ በተለምዶ ሼክ መሐመድ አላሙዲን እየተባለ የሚጠራው በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስረድተዋል።
ልዑል አልዋሊድ
እንደ መረጃ አቀባያችን (ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ ስማቸው እንዳይገለጽ አሳስበዋል) ከሆነ በቁጥጥር የማዋል ዘመቻው በዕቅድ የተከናወነ ነው የሚሉት። ንጉሡ ኮሚቴውን ማቋቋማቸው ከተሰማ በኋላ ነበር ብዙም ሳይቆይ ሁሉም ሰዎች የተያዙት። ይህም የሆነው የሚፈለጉት ግለሰቦች አገር ውስጥ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ እነ ልዑል አልዋሊድን ብቻ ሳይሆን አላሙዲንን የሚጨምር እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህ በሳዑዲ የተወሰደው ተግባር በሙስና ሽፋን ስም የተደረገ ቢሆንም ዋናው አጀንዳ ግን የፖለቲካ እንደሆነ የመረጃው ሰው ይናገራሉ። ምክንያቱም የሙስና ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሰዎች ካላቸው ሃብት አኳያ የሚጠየቀውን ገንዘብ ከፍለው በዋስ ይለቀቁ ነበር። ቢለቀቁ እንኳን አገር ውስጥ እስኪገቡ መጠበቁ ኮሚቴው ካለው የጉዞ ዕገዳ የማድረግ ሥልጣን አኳያ ከአገር እንዳወጡ አፍኖ ለመያዝ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው ይላሉ።
በኢትዮጵያና በዳያስፖራ በተቃዋሚውም ሆነ በወያኔ ደጋፊው ዘንድ ከተራ ግለሰብ ጀምሮ እስከ ራሳቸውን “ጋዜጠኛ፣ ተንታኝ …” ብለው በሚጠሩ ሁሉ አንዳች ልዩነት ሳያደርጉ “የደሃ አባት፣ ሥራ ፈጣሪ፣ የሕዝብ ደራሽ፣ ከእጃቸው በልቻለሁ፣ ወዘተ” እየተባለ በተለያዩ ቁልምጫዎች የሚጠራው የአላሙዲ መያዝ ከተራዎቹ “ፍርፋሪ ለቃሚዎች” በተለየ ህወሓትን በእጅጉ እንደሚጎዳው ጎልጉል ያገኘው መረጃ ይጠቁማል። በተለይ ለዘመናት ግብር ሳይከፍል የኢትዮጵያን ሃብት በመመዝበር ድርጅቶቹን ሲያንቀሳቅስ መኖሩ አሁን እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች በማን ቁጥጥር ሥር እንደሚሆኑና የዕዝ ሠንሠለቱስ እንዴት ተያይዞ እንደሚቀጥል አወዛጋቢ ይሆናል ተብሏል።
ለአስር ሰዎች ሥራ “ለመፍጠር” የሺዎችን የመኖር ኅልውና በመንፈግ ከዓለም የሃብታሞች ተርታ ለመሰለፍ የበቃው አላሙዲን ሥራ ፈጣሪ ተብሎ በተቃዋሚውም ሆነ በህወሓት ደጋፊ መሞካሸቱ የፖለቲካችንን መክሸፍ የሚያመለክት መሆኑን ሲናገሩ የቆዩ ይህ ሥራ መፍጠር ሳይሆን የኔ ከተሳካልኝ ስለሌላው አያገባኝም ዓይነት ሆዳምነት ነው ይላሉ። በድለላ በሚባል ዓይነት የፊትለፊት ሰው በመሆን ሃብት ካካበተው አላሙዲን፤ “ከእጃቸው በልተናል” የሚሉት ህወሓትንና ኤፈርትን ያለመታከት በሚወቅሱበት “ብዕራቸው” አላሙዲንን ዝም ማለታቸው የሚዲያውን መደዴነት፣ አድርባይነትና ጥቅመኝነት የሚያሳይ ነው ይላሉ።
ራሱን “ጋዜጠኛ” ብሎ በመጥራት ከሚዘግብለት ሠንደቅ ጋዜጣ ጎን ለጎን (Honorable Dr Sheik Mohammed Hussien Ali Al-Amoudi) የሚል የፌስቡክ ገጽ የሚያስተዳድረው ፍሬው አበበ በአላሙዲ ስም በከፈተው ገጽ ላይ “የሼህ ሙሐመድ እስር አልተረጋገጠም” በማለት ሲጽፍ በራሱ የፌስቡክ ገጽ ደግሞ “ሼህ አልአሙዲ አልታሠሩም!” በማለት ገልብጦ መጻፉ “ለሆዱ ያደረ ኅሊናቢስነቱን ብቻ ሳይሆን የአላሙዲ በቁጥጥር ሥር መዋል ምን ያህል መደናገጥ መፍጠሩን የሚሳብቅ ነው” በማለት መረጃውን የላኩልን የጎልጉል የፌስቡክ ወዳጅ ተናግረዋል።
ሌላው የአላሙዲ ተጧሪ የEthiopiaFirst.com ቢኒያም ከበደ ዜናውን ለማመን ከከበዳቸው በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሆኗል። ቢኒያም በፌስቡክ ገጹ “… አዲሱ መጤው ልዑል ተፎካካሪ ልዑላልን ሪያድ ወደሚገኘው Ritz Carlton Hotel አሰልፎ በመውሰድ ቃላቸውን እንዲሰጡ ማድረጉ ነው። በዚህ መሀከልም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆኑት ሼህ ሙሓመድ አል-አሙዲም ቃላቸውን እንዲሰጡ ወደ ግዙፉ ሆቴል መወሰዳቸውን ሰምተናል፤” “… እግዚአብሔር ይጠብቃቸው” በማለት ታማኝነቱን አስመስክሯል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ለቢኒያም መልዕክት በሌሎች የፌስቡክ ገጾች ላይ “የጣናን እምቦጭ እነቅላለሁ ያለው ትልቁ እምቦጭ አላሙዲ እምቦጭ አለ” በማለት አላግጠዋል።
በአላሙዲን ቀኝ የሚታየው አብነት ነው
በርካታዎች እየሞቱና መብታቸው ተገፍፎ በእስር እየማቀቁ በነበሩበት ወቅት የንብ ካኔተራ በመልበስ የህወሓት ደጋፊነቱን በገሃድ ያስመሰከረው አላሙዲንን ከህወሓት ለይቶ “የሕዝብ ሰው” አድርጎ ማቅረብ ለህወሓት ያለን “ጥላቻ” ከአላሙዲ “ትግሬ” አለመሆን ጋር የተገናኘ ይመስላል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ከዚህም አልፎ የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት አካባቢ በኢህአዴግ ሰዎች ሎንዶን ላይ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መጠመቁን የሚናገረውን አላሙዲንን እና ድርጅቶቹን ከኤፈርት ለይቶ ኢትዮጵያዊ አድርጎ ማቅረብ ጭፍንነት ብቻ ሳይሆን ህወሓትን የመቃወሚያው መሠረት አልባነትን የሚያሳይ እንደሆነ ድምጻቸው የታፈነ ጥቂቶች ሲናገሩት የቆዩት ጉዳይ ነው። አላሙዲንና ሚድሮክን የምናሞግስ ከሆነ ስብሃት ነጋንና ኤፈርትን ልንቃወም የምንችልበት መሥፈርት የለንም በማለት እነዚሁ ወገኖች መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ።
ሳውዲ በወሰደችው በዚህ ያልተጠበቀ እርምጃ አፈ-አላሙዲን በመሆን ሥራውን የሚያስፈጽመው አብነት ገብረመስቀልና ከእርሱ ጋር ያስተሳሰራቸው የህወሓትና ሌሎች የጥቅም ተካፋዮች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መውደቁ የማይቀር እንደሚሆን ይታመናል። “አላሙዲን ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰር አይችልም ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ አገሪቷን አስሯታል፤ አትበቃውም። እርሱን በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚችለው ሌላ ኃይል ነበር፤ አሁን አይተነዋል፤ ከዚህ በኋላ ድርጅቶቹን እንደ እርሱ ሆኖ መምራት የሚችል ግለሰብ መኖሩ በጣም አጠራጣሪ ነው፤ ይህ ደግሞ ለድርጅቶቹ ብቻ ሳይሆን ለህወሓትም ትልቅ ዱብዕዳ ነው፤ አገር ውስጥ ካለው እንቅስቃሴ አኳያ ሁኔታዎች በዚሁ አይቀጥሉም፤ በቅርብ በርካታ ያልተጠበቁ የሚመስሉ ለውጦችን ማየት እንጀምራለን” በማለት የጎልጉል መረጃ አቀባይ አስረድተዋል።
ማስታወሻ፤ አላሙዲንን “አንተ” ብለን መጥራታችን ለሚያሳስባችሁ ይህንን እንድታነቡ ይሁን

No comments:

Post a Comment