በመንደርና በዘር የተሰባሰቡ የትግራይ ልጆች ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ወይም የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በሚል ሥም ተደራጅተው በነፍጥ የአገራችንን በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ላለፉት 27 አመታት ከኛ ወዲያ ላሳር በሚል እብሪትና ትዕቢት እያንዳንዱን ማህበረሰብ አዋርደው ገዝተዋል ፤ አሁንም እየገዙ ነው።
ህወሃት ህዝባችንን እያፈነ ፤ እየገደለና እያሰደደ ለዚህ ሁሉ ያህል ዘመን ሊገዛ የቻለው እያንዳንዳችንን በባህል ፤ በቋንቋና በሃይማኖት እየከፋፈለ እንደሆነ ግልጽ ነው። በዚህ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው “እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ፤ እርስ በርስ መተላለቅ አይቀሬ ነው” እያለም ትንቢት አይሉት ሟርት በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች እና በጥቅም ባሰባሰባቸው ጋሻ ጃግሬዎቹ አማካይነት ሲሰብከን ኖሮአል።
ሆኖም ግን ኦሮሚያ ውስጥ የዛሬ ሶስት አመት የተቀሰቀሰው እና ወደ አማራና ሌሎች ያገሪቱ ክፍሎች የተዛመተው የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ ህውዓት ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ገንብቼዋለሁ ብሎ የተማመነበትን ይህንን የጥላቻና የልዩነት ግንብ ሙሉ በሙሉ የናደና የህዝብን አንድነት ያረጋገጠ እንቅስቃሴ እንደሆነ ተረጋግጦአል። ዛሬ በሁሉም የሐገራችን ክፍል የሚገኘው ህዝብ የወያኔን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት ለማስቀጠል የሚፈጸምበትን አፈናና ግዲያ ተቋቁሞ ከያለበት Down Down ወያኔ! ወያኔ ይውደም ! ወያኔ አይገዛንም ! የሚል መፈክሮችን በጋራ እያሰተጋባ ያለው የክፍፍልና የልዩነት ግንብ መፍረሱን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑ አያጠራጥርም ።
በተለይ ለህውሀት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ቅኝት እንዲመች ተደርጎ በተቀነባባረው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለአመታት በቅኝ ገዥነት እና በትምክህተኝነት የማሸማቀቅ ዘመቻ ሲካሄድበት የኖረው የአማራ ህዝብ ጎንደር ላይ የነ በቀለ ገርባን ፎቶግራፍ ይዞ በመውጣት “በኦሮሚያ የሚፈሰው ደም የኛም ደም ነው!” የሚል መፈክር ካሰማበት ዕለት ጀምሮ በመላው ኦሮሚያ እየተስተጋባ ያለው “አንከፋፈልም እኛ አንድ ነን” ድምጽ ህውሀት የቆመበትን የድጋፍ መሠረት እንዲደረመስ ከማድረግ አልፎ ፍርሃትና ድንጋጤን በድርጅቱ ውስጥ እንዲነግስ ዓይነተኛ ምክንያት ሆኖአል ። በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ የተዘፈቀው ህውዓት የመንግሥት ሥልጣን ከእጁ እንዳያመልጥና የአገዛዝ ዕድሜው እንዲራዘም የመጨረሻው የሚመስለውን ሙከራ ለማካሄድ በግለሰቦች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ጭምር ወደ ብሄር ግጭት ለማዞር እየተቅበዘበዘ እና አቅም የፈቀደለትን ሁሉ ሴራ እየሸረበ ይገኛል።
ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ሱማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ቦታዎች የሚኖሩትን ዜጎች ለማጋጨት የአገዛዙ ደህንነትና ከርሱ ጋር በቅርበት የሚሠሩ የክልሎቹ ሹሞች የተጫወቱትን ሚና ፤ በዝዋይ አንድ የወላይታ ተወላጅ ከአንድ ኦሮሞ ተወላጅ ጋር መጋጨቱን ተከትሎ ግጭቱ የብሄር መልክ እንዲይዝ ለማድረግ የተሞከረው ሴራ እና ባለፈው ሳምንት አጋማሽ አርሲ ነገሌ ላይ በግለሰቦች መካከል በተነሳው ጠብ አንድ ግልፍተኛ ግለሰብ ሌላኛውን ተኩሶ በመግደሉ ግጭቱን የአማራና የኦሮሞ ለማስመሰል የተሄደበት ርቀት ተጠቃሽ ናቸው። በእንዲህ አይነት የህወሃት መሰሪ ተንኮል ከዚህ ቀደም በአኝዋክና በኑዬር ፤ በአፋርና በትግራይ ፤ በወላይታና በሲዳማ ፤ በጉጂና በኮንሶ ፤ ቤንሻንጉል እና ኦሮሚያ ውስጥ “በአካባቢው ተወላጆችና መጤ” በተባሉት መካከል ሆን ተብሎ በተቀሰቀሱ ግጭቶች ምን ያህል የሰው ህይወት እንደጠፋ እና ምን ያህል ንብረት እንደወደመ ይታወቃል።
በእስከዛሬው የህወሃት የመከፋፈል ሴራ አልበገር ብሎ በጋራ በቆመው ህዝብ መካከል እንደገና የጥርጣሬና የስጋት መንፈስ ለመዝራት በደህንነት መስሪያቤቱ በኩል እየተካሄደ ካለው ሴራ በተጨማሪ ኦሮሚያ ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ህዝባዊ እምቢተኝነት አቅጣጫ ለማስለወጥ ሠልፈኛው ከቤቱ ይዞት ያልወጣቸውን መፈክሮችና አገዛዙ “በሽብርተኝነት” ከፈረጃቸው ድርጅቶች የአንዱ የሆነውን ድርጅት የትግል አርማ አሰርጎ በማስገባት የዘመናት ብሶትና በደል አንገብግቦት አደባባይ የወጣውን ህዝብ በምን ለመወንጀል እንደተሞከረም ተመልክተናል። የዚያ ውንጀላ ዋና ዓላማ ህወሃት እስከ ዛሬ በሚተማመንባቸው የመሳሪያ እና የጉልበት የበላይነት ሊጨፈልቅ ያልቻለውን የቄሮ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሌሎች ዘንድ በጥርጣሬ ዓይን እንዲታይ እና ድጋፍ እንዳይቸረው ለማድረግ በመሞከር የተቃውሞ ትግሉን ለመግደል ወይም ለመቆጣጠር እንደሆነ መገመት አያስቸግርም ።
በአርበኞች ግንቦት 7 የፖለቲካ ግምገማ ህወሃት ህዝባችን ለፍትህና ለእኩልነት ብቻ ሳይሆን ለራሱ ክብር እና ልዕልና የጀመረውን ትግል ለማስቆምም ሆነ ለመቆጣጠር የሚያስችለው አቅም ላይ እነዳልሆነ ተረጋግጦአል። ከአሁን ቦኋላ ያንን ያጣውን የበላይነት መልሶ ማግኘት የሚችልበት መንገድም አብቅቶአል ብሎ ንቅናቄው ያምናል። ይህንን ጸሃይ የሞቀውንና አገር ያወቀውን እውነታ ባለመቀበል ህወሃት ሊሄድበት ያሰበው መንገድም ሆነ ሐገራችን እንዲገጥማት የሚፈልገው አደጋ ህወሃትን እንደ ድርጅት ፤ ጉምቱ ባለሥልጣናቱንም እንደ ብቸኛ ተጠያቂ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አደጋ ያዘለ መሆኑን ህወሃት የተረዳው አይመስልም።
አርበኞች ግንቦት 7 የህወሓት የግፍ አገዛዝ እንዲያበቃ የኢትዮጵያ ህዝብ እያካሄደ ያለዉን ትግል ለማጠናከር እና እየተከፈለ ያለዉን መስዋዕትነት ከዉጤት ለማድረስ በሙሉ ሃይሉ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በእብሪተኞችና በመንደርተኞች የተቀማውን ነጻነት ለማስመለስ ብሎም በነጻ እና ገለልተኛ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሚቋቋም መንግሥት ለመተዳደር ህዝባችን እያካሄደ ያለው ትግል ከአሁን ቦኋላ በምንም አይነት የህወሃት ሰራሽ ሴራ እንዳይጨናገፍ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ለነጻነቱ ቀናዒ ከሆነው ህዝባችን ጎን በመቆም ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያስታውቃል።
የህዝብ ወገን የሆናችሁ የሐገሪቱ መከላኪያ ሠራዊት ፤ የፖሊስና የደህንነት አባላት የመንግሥት ሥልጣን የጨበጠው ህወሃት የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘም ሲል በሚሸርበው ሴራ የገዛ ወገኖቻችሁን ለመግደል ፤ ለማሰርና ለማሰደድ የሚሠጣችሁን ትእዛዝ እንቀበልም በማለት ከህዝባችሁ ጎን እንድትቆሙና የህዝብ አለኝታነታችሁን በተግባር እንድታረጋግጡ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
No comments:
Post a Comment