የዘንድሮው ህወሀት በሁለት መልኮች ይገለጻል። አንደኛው በፍርሃት የሚናጥ፡ በማያባራ ህዝባዊ ማዕበል ወንበሩ የተናጋ፡ ወድቀቱን በቅርበት እያየ በስጋት እየተርገፈገፈ የሚገኝ፡ ሳር ቅጠሉ የተጠየፈው፡ ድርጅት ነው። ሌላኛው መልኩ ደግሞ መቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ የሚፎክር፡ በመጨረሻው ሰዓት ንሰሀ መግባት ሲገባው ሃጢያቱን የሚከምር፡ ሞት ደጃፍ ቆሞ የሚሸልል፡ ዕብሪትና ጥጋብ በስተርጅናም ያለቀቀው፡ ለአንድም ቀን ቢሆን በስልጣን ለመቆየት ሀገር ከማፍረስ ወደኋላ የማይል፡ ሃላፊነት የጎደለው፡ ሞራል የደረቀበት፡ ''እኔ ከሞትኩ....'' መስመር ላይ ወጥቶ ወደግዙፍና መጠነ ሰፊ ጥፋት የሚጋልብ ድርጅት ነው።
ለጊዜው ወደተቋረጠው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላምራ። የደህነንቱ ሹሙ ቦግ ብሏል። ተቆጥቷል። ፊቱ ቲማቲም መስሏል። ዓይኑን ያጉረጠርጣል። እንደልማዱ ማስፈራራት ላይ ነው። ባሳደግን ተናቅን፡ ባጎረስን ተነከስን ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆኖ በንዴት ይወራጫል። ወዲያውኑ ደግሞ ይቀዘቅዛል። ስሜቱ ይበርዳል። “ከሀይ ስኩል ጀምሮ ያሳደግናችሁ እኛ ነን። በጣም ጠንካሮችና ጎበዞች በመሆናችሁ እኔ በግሌ እኮራባችኋለሁ። ብዙዎች አገር ትተው ሲሰሹ እናንተ ግን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሕዝብ ጎን በመቆማችሁ ምስጋና ይገባችኋል፤ ሆኖም ግን አገር ሲመራ መቸኮል አያስፈልግም፤ ሰከን ማለት ይገባል” ዓይነት ምክር ለመስጠት ይሞክራል። ጭንቀት። ስጋት። ፍርሃት። ደግሞም ትዕቢት፡ ድንቁርና፡ እየተፈራረቁ ያንገላቱታል።
ቀን በገፋ ቁጥር ልዩነት እየጎላበት የመጣው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በጌታቸው አሰፋ ድንፋታ፡ ማስፈራሪያ የተሞላ ሆኗል። ከመነሻው ወጥረው የህወሀትን ማንቁርት አንቀው ''እኩልነት ወይሞ ሞት'' የሚል መፈክር ያነገቡት እነለማና ገዱ ከዚህ ሰውዬ ጋ የገቡበት ፍጥጫ በስብሰባ አዳራሽ ያለውን የሃይል ሚዛን እየቀየረው ነው። ህወሀት በጌታቸው አንደበት እየተናገረ ነው። እነደብረጺዮን፡ ጌታቸው ረዳና ሌሎች የህወሀት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከደህንነት ሹሙ ጀርባ አድፍጠዋል። አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድ የስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ቆፍጠን፡ ኮስተር ብለው ያስቀመጡት አቋም፡ ያንንም የገዱ ቡድን ድጋፍ መስጠቱ ለህወሀት ያልተጠበቀ መርዶ ነበር የሆነው። ''ህዝብ ቀውስ ውስጥ ገብቶ፡ ሀገሪቱ በትርምስ እየተናጠች እኛ የምንሰብሰበው ለምንድን ነው? ቅድሚያ ለህዝባችን መድረስ አለብን'' የሚለው የእነ ለማ አቋም እንደተሰማ የደህንነት ሹሙ ብድግ አለ። ሁኔታው አላማረውም። ህወሀት አደጋ ላይ ነው። የሆነ ነገር ማድረግ አለበት።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥሩ አድርጎ አስተምሮታል። መለስ በፓርላማ የኦሮሞ ተወካዮች በጥያቄ ወጥረው ሲይዙት ''እናውቃለን። ቀን ከእኛ ጋር ማታ ከኦነግ ጋር እንደምታወሩ የማናውቅ እንዳይመስላችሁ'' ብሎ አጀንዳ ማስቀየስ፡ አፍ ማሲያዝ ለምዷል። ጌታቸው አሰፋ ይህን የመለስ ሸልፍ ላይ አዋራ ጠጥቶ የከረመ ስትራቴጂ አራግፎ መጠቀም ፈልጓል። እናም ሁኔታዎች የህወሀትን የበላይነት ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ሆነው ሲመጡ፡ ''ከሀይስኩል ጀምሮ ያሳደግናችሁ......'' አለና ጀመረ። ለአቶ ለማና ለዶ/ር አብይ መሆኑ ነው። ረጅም በማስፈራሪያ የታጀበ ዲስኩር ከለቀቀ በኋላ ''ከኦነግ አመራር ጋር የተጻጻፋችሁት፡ በስልክ ያወራችሁት በእጃችን አለ። አይተን እንዳላየን በዝምታ አለፈን እንጂ የማናውቅ እንዳይመስላችሁ''
ጌታቸው አሰፋ ገዱ ላይ ዞረ። “ገዱ የአማራ ክልልን ማረጋጋት አልቻልክም፤ ክልሉ በቁጥጥር ስር ነው ማለት ያዳግታል'' አለው። ቀጠለ- ሰውዬው። '' “ለሀገር አይጠቅምም ብለን ነው እንጂ ብዙ ማስረጃ በእጃችን አለ” በማለት ጌታቸው የተቀረፀ ድምጽ አሰማና ተዝናንቶ ተቀመጠ። ገዱ የዋዛ አልነበረም። ''ክልሉን ማረጋጋት እንዳንችል የእናንተ ጣልቃ ገብነት አስቸገረን። አሁን የሰማነው ድምጽ ደግሞ የእኔ አይደለም። ከሆነም በፍርድ ቤት ክሰሰኝ እንጂ እዚህ ማሰማት ምን ይጠቅማል?'' በማለት በድፍረት ተናገረ።
ከዚህ ቀደም ለመጥቀስ እንደተሞከረው እነለማ ከዚህ ስብሰባ ከሚያገኙት ይልቅ የሚያጡት ይበልጣል። ስብሰባውን ረግጠው መውጣት፡ ከሆነላቸውም ኢህአዴግ የተባለውን የኩሸት ቤት ማፍረስ፡ ከዚያም አልፈው በህወሀት አምሳያ፡ አሻራና የበላይነት የቆመውን መንግስት ገንድሰው በመጣል አዲስ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ማድረግ ካልቻሉ ይህ ስብሰባ በረዘመና ጊዜ በወሰደ ቁጥር ለህወሀት አፈር ልሶ መነሳት እድሉን ይሰጣል የሚል ሀሳብ ተሰንዝሮ ነበር። አሁን እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ህወሀት አንገቱን ከደፋበት ቀና እያደረገ ነው። ከተከላካይነት ወደ አጥቂ መስመር ላይ ወጥቷል። እነለማ እንደአጀማመራቸው ሊቀጥሉ አልቻሉም። እንደምንሰማው ከሆነ አቶ ጌታቸው አሰፋ በእነለማና ገዱ ላይ የጀመረው ማስፈራራት መስመር ይዞለታል። በተወሰነ ደረጃም ተሳክቶለታል። በተለይ ከኦህዴድና ከብአዴን ተንሸራተው ህወሀት ጎጆ ውስጥ የገቡ ሰዎች እነለማንና ገዱን አጋፈጠው ሰጥተዋል።
''“ችግሩ አማራ ላይ ብቻ ሳይሆን ኦሮሚያም ላይ ነው“ ብሎ መጀመሪያ የተነሳው ወርቅነህ ገበየሁ ነበር። የተጠና አካሄድ ይመስላል። ህወሀቶች የቤት ስራቸውን ሲሰሩ ቆይተዋል ማለት ነው። አንገታቸውን ሰብረው፡ የተሸነፉ፡ እጅ የሰጡ መስለው ከቆዩ በኋላ አሁን ቀና ብለው የበቀል ጅራፋቸውን እያስጮሁ ነው። ወርቅነህ ገበየሁ፡ የእነለማን ቡድን በማጥቃት፡ ለጌቶቹ ህውሀቶች ጥብቅና በመቆም ተናገረ። አቶ ዲሪባ ኩማም የጌታቸው አሰፋን ልብ በደስታ ያዘለለ፡ ህወሀቶችን ያስቦረቀ፡ እነለማን እንደይሁዳ አሳልፎ የሰጠ ንግግር አደረገ። ሌላኛው የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማም ጨመረበት። እነለማ ላይ ሁለት ግንባሮች በይፋ ተከፈቱ። ከበብአዴን በኩልም በተመሳሳይ አለምነው መኮንንና ከበደ ጫኔ ከህውሀት በላይ ህወሀት ሆነው በመቅረብ እነገዱ ላይ የውግዘት መዓት አወረዱ። ከኦህዴድና ከብአዴን ስራ አስፈጻሚ አባላት የመጣው ተቃውሞና መንሸራተት ለጊዜው የእነለማንና ገዱን የለውጥ ግስጋሴ አስቁሞታል።
በፓርላማ አባላቱ አስቸኳይ ጥሪ ምክንያት ስብሰባው ተቋርጧል። የሃይል ሚዛኑ ወደ ህወሀት ያጋደለ መስሏል። ገዱ ወደአሜሪካ መምጣቱ ታውቋል። ለህክምና ነው። ጨርሶ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ይመለሳል ተብሏል። አስደናቂ ለውጥ አሳይተው በብዙዎች ዘንድ ተስፋን የጫሩት የፓርላማ አባላት ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ምን እንደተነጋገሩ የሚነግረን እስከአሁን አልተገኘም። በእርግጥ ከአቶ ሃይለማርያም የሚሰማው ቁምነገር ያለው ባይሆንም የፓርላማው አባላት ወክለነዋል ለሚሉት ህዝብ መረጃ መንፈጋቸው ወይም እንዳይናገሩ አፋቸው መቆለፉ የህወሀትን ማንሰራራት ያመላክታል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። በእርግጥ በዝጉ የፓርላማ ስብሰባ አዲስ ነገር እንደሌለ ጭምጭምታው ተሰምቷል። ''በኢህአዴግ የውስጥ ዲሞክራሲ መሰረት የተፈጠሩትን ችግሮች እንፈታለን'' በምትል አንዲት አረፍተ ነገር የፓርላማው ግርግር ተቋጭቷል።
እነለማና ገዱ ሁለት ግንባሮች ጋር መላተማቸው በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ያለውን የበላይነታቸውን እንዳሳጣቸው ማረጋገጥ ተችሏል።ከጌታቸው አሰፋ ድንፋታ፡ ማስፈራሪያ ይልቅ ከጎናቸው የሚገኙ ጓዶቻቸው መንሸራተት ለእነለማ በጀመሩት ፍጥነት እንዳይራመዱ አድርጓቸዋል። እነወቅነህ ገበየሁ በዚህን ቀውጢ ወቅት ከዳር እስከዳር ለሚሰማው የህዝብ የለውጥ ድምጽ ጆሮአቸውን ዘግተው ለጌታቸው አሰፋ ቡራ ከረዩ ማስፈራሪያ እጅ ሰጥተዋል። ለጊዜው የእነለማ ቡድን መለሳለስ ማሳየቱም እየተነገረ ነው። ገፍተው እንዳይሄዱ ከጓዶቻቸው የተከፈተባቸው አዲስ ግንባር በዚያ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ጉልበታቸውን አዝሎታል። ሁለቱንም ግንባሮች ለመመከት የሚያስችል አቅም እዚያ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የላቸውም። እንደሚባለውም፡ ለመገመትም የሚቻለው እነለማ ለጊዜው ተለሳልሰው ተስማምተው ከመውጣት ውጪ ያለው አማራጭ ፊት ለፊት መላተም ነው።
እንግዲህ የቁርጡ ጊዜ ደርሷል። ከአፍንጫችን ስር ነው። በእኔ እምነት እነለማ/ገዱ አማራጭ አላቸው። እዚህ ነገር ውስጥ ሲገቡ ከህውሀት ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል ቀድመው እንደሚያውቁ እርግጠኛ ነኝ። ከህወሀት መሪዎች ጋር በተለይም ከደህንነቱ ሹም ጋር ለዓመታት የሚተዋወቁ በመሆናቸው የህወሀትን ቁማር አስቀድመው ያውቃሉ ብሎ መናገር ይቻላል። እንኳን እነሱ የውጭ ታዛቢም የህወሀትን እያንዳንዷን እርምጃ በሚገባ ያውቃል። ህወሀት በሀሳብ ድርቀት የሚሰቃይ፡ በድንቁርና በተሽቆጠቆጡ መሪዎች የሚመራ ኋላ ቀር ድርጅት በመሆኑ ስለሚያደርጋቸው ነገሮች መገመት በጣም ቀላል ነው። እናም እነለማ አሁን እየሆነ ያለው ያልጠበቁት ዱብ እዳ ነው ለማለት ይከብዳል። ጌታቸው አሰፋ ቢላዋ ስሎ፡ በሀሰት ማስረጃ፡ ለማስፈራራት እንደሚመጣ ቀድመው ልቅም አድርገው ያውቁታል። በዚያ የስብሰባ አዳራሽ እናሸንፋለን የሚል ተስፋ ከውስጣቸው ከነበር የተሳሳተ ስሌት ነበራቸው ማለት ነው። የእነሱ ጉልበት ከውጭ ነው። አሸናፊነታቸው ከአዳራሹ ባሻገር ነው።
አዎን። ህወህት ካደፈጠበት ቀና እያለ ነው። ለጥቂት ቀናት አንገቱን ከቀበረበት አውጥቶ የበቀል በትሩን ሊሰነዝር ተዘጋጅቷል። የመጀመሪያ ሰለባዎቹ እነለማ መሆናቸው ጥርጥር የለውም። የኦሮሞ ህዝብ ያነሳውን ተቃውሞ የጥቅላይ ሚኒስትርነቱን ወንበር በመስጠት እናስቆመዋለን በሚል ከኦህዴድ ሰው እያፈላለጉም እንደሆነ ይነገራል። ይህ ህወሀት ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን ንቀት ከማሳየት ባለፈ ለውጥ የለውም። ነጻነት፡ ፍትህና እኩልነት ለተራበ ህዝብ የሞግዚት ወንበር በመስጠት አጠግባለሁ ብሎ መነሳት አሳፋሪ ነው። የኦሮሞ ህዝብ እኩልነትን ጠይቋል። በገዛ ሀገሩ የባይተዋር ኑሮ በቃኝ ብሏል። ለዚህም መስዋዕትነት እየከፈለ ነው። ይህን የህዝብ ጥያቄ በህወሀት የሞግዚት ወንበር ላይ አንድ የኦሮሞ ልጅ በማስቀመጥ ይመለሳል የሚል ድፍረት ከህወሀት መንደር እየተሰማ ነው። መከላከያውንና ደህንነቱን የማይቆጣጠር የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ለኦሮሞ ህዝብ የዘመናት ጥያቄ መልስ አይሆንም።
እነለማ/ገዱ ከፍርሃት ቆፈን የተላቀቁ እንደሆነ ይሰማኛል። ከጌታቸው አሰፋ ድንፋታ በላይ የህዝባቸው የለውጥ ረሃብ እንደሚያንበረክካቸው እረዳለሁ። በመጨረሻው ሰዓት በጓዶቻቸው ቢካዱ እንኳን የጀመሩትን መስመር መልቀቅ አደጋው ከማንም በላይ ለእነለማ/ገዱ ነው። በአዳራሹ የታመቀውን ሚስጢር ለህዝባቸው በይፋ ገልጸው የሚመጣውን ሁሉ መቀበል እንጂ ከዚህ በኋላ ማፈግፈግ አደገኛ ነው። ህወሀት ከእንግዲህ ለእነለማ ጉድጓድ ከመማስ ውጪ በስልጣን እንዲቆዩ የሚፈቅድ አይሆንም። ደጋፊዎቻቸው ሰልቅጧቸው፡ ብሏቸው እያለ ነው። ቅስቀሳው ከወዲሁ በህወሀት መንደር ጦፏል። ጌታቸው አሰፋ የህወሀት የጋዜጠኞች ስኳድ ወደ ሶማሌ ክልል በመላክ የዘር ፍጅት ፕሮግራሞችን እንዲያዘጋጁ ያዘዘው ያለምክንያት አይደለም። ለእነ ለማ ወጥመድ እያዘጋጀ መሆኑ አይጠፋንም።
እነለማ/ገዱ ላይጨርሱት አልጀመሩም። የትኛውንም ዋጋ በመክፈል የህወሀትን መርዝ ማርከስ አለባቸው። በዝግ የሚደረገውን ስብሰባ ለአደባባይ ያበቁት ዘንድ ይጠበቃሉ። ከህወሀት ጋር ሚስጢር ከህዝብ ያጋጫል። ከህዝብ ልብ ያጠፋል። ብሎም ለአሳፋሪ አወዳደቅ ይዳርጋል። በቃ! እየሆነ ያለውን ያፍርጡት። ለህዝብ ይንገሩ። የተሸፈነውን ይግለጡት። የተደበቀውን ያጋልጡት። ህወሀት ቢተፋቸው ህዝብ ይቀበላቸዋል። ሳምባው አልቆ በአርቴፊሻል ኦክሲጅን እየተነፈሰ ካለ አገዛዝ ጋር ከዚህ በላይ አብሮ መጓዝ በሰማይም በምድርም ያስጠይቃል። ለማና ገዱ ኢ- ህ -አ -ዴ- ግ ን አፍርሱና ከህዝብ ተቀላቀሉ። ዛሬ አይደለም። አሁኑኑ።
No comments:
Post a Comment