ቋጠሮ ድህረ ገጽ
አጼ ምኒልክ የተወለዱት በ1836 ነኅሴ 12 ቅዳሜ ቀን ነበር። በህይወት ቢኖሩ ትናንት ነሃሴ 12 2009 ዓ.ም የ173 ዓመት ልደታቸውን ያከብሩ ነበር ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን አብዛኛው ኢትዮጵያዊው የእኚህን ድንቅና የጥቁር ህዝብ የነጻነት ቀንዲል የሆኑ መሪ ገድል እየዘከረ 173ኛ የልደት ቀናቸውን እያከበረ ይገኛል፡፡ የዚህችም ጽሁፍ ምክንያት ይኽው ነው። የጸሃዩን ንጉስ ዕለተ-ውልደት መዘከር።
አጼ ምኒልክ በዘመነ ንግስናቸው በርካታ የስልጣኔ መሰረት የሆኑ ተግባራትን ፈጽመዋል። ስልጣኔን ወደ ሃገር በማስገባትና በማስፋፋት የአጼ ምኒልክን ያህል ተጠቃሽ መሪ የለም። ይሁን እንጂ አጼ ምኒልክ የውጭውን ስልጣኔ ለማስገባት ሲሞክሩ ህዝቡ አልቀበል እያለ ይቸገሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ ወፍጮን ለማስገባት በሞከሩበት ወቅት ከመኳንቱና ከቀሳውስቱ ጠንከር ያለ ውግዘትና ተቃውሞ ነበር የገጠማቸው። መለኛው ንጉስ ግን የገጠማቸውን ተቃውሞና ውግዘት በጥበብ አክሽፈውታል። ያከሸፉበት ዘዴ ደግሞ ብልህነታቸውን ከማሳየቱም ባሻገር አስቂኝ ነበር።
ጳውሎስ ኞኞ “አጼ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሃፉ ገጽ 337 ላይ የዘመናዊ ወፍጮን አገባብ ታሪክ እንዲህ ሲል አስፍሮታል፦
የወፍጮ መኪና በኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም አስቸጋሪ ነበር። የሸዋው ንጉስ ሳህለ ሥላሴ በ1835 ገደማ አንድ በውሃ የሚሰራ ወፍጮ አስመጥተው ባስተከሉ ግዜ፤ ቀሳውስቱ ወፍጮ የሰይጣን ስራ ነውና በወፍጮው አስፈጭቶ የበላ የሰይጣን አገልጋይ ነውና አውግዘናል በማለታቸው ወፍጭው ፈራርሶ ወደቀ። ከዚያ ዘመን ቀደም ብሎም አቡነ ሰላማ አጼ ቴዎድሮስን ወፍጮ እንዲገባ ባማከሯቸው ግዜ “ የሴቶቹን ክንድ ምን ልናደርግበት ነው?” ወፍጮን ከለከሉ። አጼ ዮሃንስም “በጉዞ ላይ እህል የሚፈጩ ሴቶችን ከማጓጓዝ የሚገላግለን ነው..” ብለው ወፍጮ ቢያስተክሉም በንጉስ ሳህለ ስላሴ እንደደረሰው ሁሉ በእሳቸውም ላይ የሰይጣን ፈጪ ነው ተብሎ ስለተወገዘ ቀረ።