አዝናኝ እና አሳዛኝ የመንግስት ሪፖርቶች - በአዲስ መፅሀፍ
ስኳር፣ ኮንዶሚኒዬም፣ ወርቅ፣ ኤሌክትሪክ፣ አውቶቡስ …
ባለፈው ዓመት፣ የስኳር ምርትን 22 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ አልነበር? ለዚህም፤ ከ200ሺ ሄክታር በላይ አዲስ የእርሻ መሬት ተዘጋጅቶ፣ የስኳር አገዳ ይለማል ተብሎ ነበር - በትራንስፎርሜሽን እቅድ፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ የለማው ተጨማሪ መሬት፣ 35ሺ ሄክታር ነው፡፡
ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር፣ 15 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከእቅዱ ውስጥ፣ ሩብ ያህሉን እንኳ ማሳካት አልቻለም፡፡
ነገር ግን፣ ይህንን ውድቀት እንደ ስኬት አስመስዬ ማቅረብ ብፈልግስ? በአምስት አመታት ውስጥኮ፣ በድሮው 30ሺ ሄክታር ላይ 35ሺ ሄክታር ተጨምሯል፡፡ ስለዚህ፣ የ115% እድገት ተመዝግቧል ማለት ይቻላል፡፡
በእርግጥ፣ በቅርቡ የታተመው አመታዊ የመንግስት ሪፖርት ላይ “215%” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ግን ይሄ አይገርምም፡፡ ለምን ብትሉ፤ “ገና ምኑን አያችሁና!” እላችኋለሁ፡፡ ገና ብዙ ስህተቶችን ታያላችሁ፡፡ ለምን?
አገሩን ካጥለቀለቁት ብዙ አይነት እጥረቶች መካከል፣ “የቁጥር እውቀት እጥረት” (የሂሳብ እጥረት) አንዱ ነዋ፡፡
የመጀመሪያው ስህተት፣ ቁጥሩን ማሳሳት ነው (115% መሆን የነበረበት 215% ብሎ መፃፍ)፡፡ ሁለተኛው ስህተት፣ በ200ሺ ሄክታር (በ700%) ለማሳደግ ታቅዶ እንደነበር ሳይጠቀስ ይታለፋል፡፡
እናም … የ35 ሺ ሄክታር (115%) እድገት ተመዝግቧል ተብሎ እንደ ስኬት ሪፖርት ይቀርባል (በቅርቡ የታተመው የመንግስት አመታዊ መፅሃፍ ገጽ 116፡፡)
ሦስተኛው ስህተት፣ … የተመዘገበው “እድገት”፣ በአብዛኛው በከንቱ እንደባከነ አለመግለፁ ነው፡፡ እንዴት በሉ፡፡ የስኳር አገዳ ቢመረትም፣ አዳዲሶቹ ፋብሪካዎች ስራ አልጀመረም፡፡ የስኳር አገዳው ልማት 65ሺ ሄክታር ደርሷል፡፡ ነገር ግን፣ ከ35ሺ ሄክታር በላይ ማስተናገድ የሚችል የፋብሪካ አቅም እስካሁን የለም፡፡
ለዚህም ነው፤ በየአመቱ በመቶ ሚሊዮን ብር የሚገመት የስኳር አገዳ ምርት በከንቱ እንዲቃጠል የሚደረገው፡፡ ይሄ፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ሪፖርት ውስጥ አይካተትም፡፡
እንዲያውም፤ የስኳር ፋብሪካዎቹ “በተቀመጠላቸው እቅድ መሰረት በመገንባት ላይ ናቸው” ይላል የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ሪፖርት፡፡ (ገፅ 112)
እውነታው ግን፣ እስከ አምና ድረስ ስራ ይጀምራሉ ተብለው ከነበሩ 10 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ፤ አንዳቸውም ምርት አልጀመሩም፡፡ የግማሾቹ ግንባታም፣ ገና በሃሳብ ደረጃ ላይ ነው፡፡ እውነታው ሌላ፣ ሪፖርቱ ሌላ፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር ሪፖርትን ደግሞ ተመልከቱ፡፡ በተለይ በወርቅ ማዕድን ወደ 800 ሜሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሰው የማዕድን ሚኒስቴር፣ በተግባር 320 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘ ገልጿል፡፡
ከእቅዱ በታች ነው፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽንና የብረታብረት ኮርፖሬሽን፣ ውድቀትን ከመሸፋፈን አልፈው፣ እንደ ስኬት አስመስለው አቅርበው የለ? የማዕድን ማኒስቴርስ?
እቅዱ እንዳልተሳካ አልደበቀም፡፡ ይልቅ፣ እቅዱ ለምን እንዳልተሳካ በርካታ ምክንያቶችን ዘርዝሯል፡፡ በአለም ገበያ፣ ለወርቅ መቀነሱ፣ ወርቅ አምራቾችን አዳክሟል፡፡
በግል በየቦታው የወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ከመቶ ሺ በላይ “የቀን ሰራተኞች”፣ ግብር እንዲከፍሉ ሰፊ ዘመቻ መካሄዱም፣ የወርቅ ምርትን ያዳከመ ሌላው ምክንያት ነው ብሏል የሚኒስቴሩ ሪፖርት፡፡
በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ፣ በተለይ ከወርቅ ይገኛል ተብሎ የታሰበው የውጭ ምንዛሬ አልተሳካም - በ500 ሚሊዮን ዶላር ጐድሏል፡፡
ነገር ግን፣ ይህንን “ለማካካስ” በሌሎች ዘርፎች ጥረት እንደተደረገና፣ ከእቅድ በላይ ስኬት እንደተመዘገበ የማዕድን ሚኒስቴር ገልጿል፡፡ ይህም የሆነው፤ “የጌጣጌጥ ንግድን በማስፋፋት፣ ከወርቅ የታጣውን የውጭ ምንዛሪ፣ ለማካካስ ታቅዶ በመሰራቱ ነው” ይላል ሪፖርቱ፡፡ አስገራሚው ነገር፤ በዚህ “ትልቅ ስኬት” አማካኝነት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ፣ 2 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይሄ ነው፣ የ500 ሚ. ዶላር ጉድለትን ያካክሳል ተብሎ በሪፖርቱ የቀረበው፡፡
ግን መፍረድ ያስቸግራል፡፡ የትም አገር ቢሆን፣ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ መስራት ከባድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ በጣም ከባድ ነው፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤት፣ ቀስ በቀስ እይታን እየጋረደ፣ ሙያን እየሸረሸረ ከእውነታ ጋር ያራርቃል፡፡ በቃ፤ ሪፖርት ማሳመር …. የሁሉም ነገር መፍትሄ መስሎ የሚታያቸው ሰዎች ይበራከታሉ፡፡
ቢሆንም ግን፤ የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ከሌሎች ይሻላል፡፡ እቅዱ እንዳልተሳካ በግልፅ ተናግሯል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ከ2006 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር፣ የአምናው ገቢ በሩብ ያህል እንደቀነሰም አልቀበደም፡፡
ይህንን ግልፅነት ብናመሰግን ጥሩ ነው፡፡
የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ሪፖርትን ስታዩ ነው ልዩነቱ የሚገባችሁ፡፡ ነባሩን የ125 ሺ ኪ.ሜ የኃይል ማሰራጫ መስመር፣ በ130ሺ ኪ.ሜ ለማሳደግ ታቅዶ እንደነበር ይጠቅሳል - የኤልፓ ሪፖርት፡፡ እና በአምስት አመታት ምን ያህል ተሳካ?
የማሰራጫ መስመሩን 165 ሺ ኪ. ሜ ማድረስ እንደተቻለ ሪፖርቱ ይገልፃል (ገፅ 224)፡፡ በነባሩ ላይ ምን ያህል ጨመረ? 40ሺ ኪ፣ሜ ገደማ፡፡ ይሄን ከእቅዱ ጋር ስናነፃፅረው ሲሶ እንኳ አይሆንም፡፡ ነገር ግን፣ ኤልፓ “እቅዴ አልተሳካም” ብሎ እውነታውን አልተናገረም፡፡ በተቃራኒው፤ “በበጀት ዓመቱ ከተያዘው እቅድ አንፃር፣ አፈፃፀሙ 105 መቶ” … እንደሆነ ገልጿል፡፡
ወረድ ብሎ ደግሞ፤ “4 ሚሊዮን አምፖሎች ለአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተልከዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 15 ሚሊዮን አምፖሎች ለተጠቃሚ እንዲደርሱ ተደርጓል” ይሏል (ገፅ 226)፡፡ ለአራት ሚሊዮን አምፖሎች ውስጥ?
ኤሌክትሪክ ተዘረጋላቸው የደንበኞች ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግና 4 ሚሊዮን ለማድረስ ነበር የታቀደው፡፡ በሌላ አነጋገር ለሁለት ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች ኤሌክትሪክ ማቅረብ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ምን ያህሉ በአምስት አመታት ተሳካ? ለ200 ሺ አዳዲስ ደንበኞች ኤሌክትሪክ ተዘርግቷል፡፡ ማለትም፣ ከእቅዱ 10% ብቻ ነው የተሰራው፡፡ የኤልፓ ሪፖርት ግን፤ ከእቅዱ ከግማሽ በላይ መከናወኑን ያሳያል በማለት የስኬት ጥሩምባ ያስተጋባል፡፡፡፡ ለነገሩ የእቅዱን ግማሽ ያህል ቢሰራ እንኳ፤ እንደ ስኬት መቆጠር አልነበረበትም፡፡ (ገፅ 224)
በእርግጥ፣ በየጊዜው ሪፖርት ማቅረብ፣ መልካም ነው፡፡ የየመስሪያ ቤቱ ሪፖርቶች ተሰባስበው፣ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት አማካኝነት መታተማቸውና ተጠርዘው መሰራጨታቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ሪፖርቶቹ እውነተኛ መረጃን የሚያቀርቡ መሆን አለባቸው፡፡
የኮንዶሚኒየም ግንባታን ተመልከቱ፡፡ ከ2003 ዓ.ም በፊት ሲጓተቱ የቆዩ ቤቶች ካልሆነ በቀር፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተጀመሩ ግንባታዎች አልተጠናቀቁም፡፡
እንደ እቅዱ ቢሆን ኖሮ ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ 300 ሺ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች በሽያጭ መተላለፍ ነበረባቸው እስከ 2007 ዓ.ም በነበሩት አምስት ዓመታት፡፡ ግን ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡
የከተማ ልማትና የቤቶች ሚኒስቴር ሪፖርት ግን ይህንን እውነታ አይጠቅስም፡፡ ያልቅስ፣ የቤት ግብይትን ለማስፈፀም የሚያስችል የደንብ ዝግጅት 87% ላይ ደርሷል ይላል ሪፖርቱ፡፡ ስንት አንቀፆች ወይም ስንት አረፍተ ነገነሮ ተፅፈው ይሆን፤ የደንቡ ዝግጅት እንዲህ ወደ 90% የተጠጋው?
የከተማ ልማት ሚኒስቴር፣ ሌሎች ስኬቶችም ዘርዝሯል፡፡ 300 ሄክታር መናፈሻ ለማዘጋጀት ታቅዶ፤ በእጥፍ ከእቅዱ የሚበልጥ 730 ሄክታር እንደተሳካ የሚኒስቴሩ ሪፖርት ያበስራል፡፡ ፓርክ እና አረንጓዴ ስፍራ … ጥሩ ነው፡፡ ግን፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ ስራ አጥነት፣ የውሃና የትራንስፖርት የመሳሰሉ ችግሮች መቅደም የለባቸውም?
አሁን ደግሞ፤ ከፒያሳ እስከ ብሄራዊ ትያትር ድረስ የተዘረጋው የቸርችል ጎዳና ላይ፣ የመኪና እንቅስቀቃሴ ይታገዳል ተብሏል፡፡ የመናፈሻ ፓርክ ይስፋፋበታል ሲባልም ሰምተናል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
የቸርችል ጎዳናን መዝጋትኮ …
ከወዲህ ፒያሳ ነው - ብዙ ህዝብ የሚኖርበት የንግድ ማዕከል፡፡ ከወዲያ ለገሃር አለ - የትራንስፖርና የመኖሪያ ማዕከል፡፡ ከቀኝ በኩልም፣ እስከ መርካቶ፣ ጥቅጥቅ ያለ መኖሪያና የተጧጧፈ የንግድ መናሃሪያ አለ፡፡
ከግራ በኩል ደግሞ፣ ስታዲየምንና መስቀል አደባባይን ጨምሮ ወደ ቦሌ፣ ወደ መገናኛና ወደ ሳሪስ በሚወስዱ ዋና ዋና የትራንስፖርት መስመሮች ተወጥሯል፡፡
በአራቱም አቅጣጫ የተከበበው የቸርችል ጎዳና ላይ፣ “ፓርክ” ለማስፋፋትና የመኪና ትራንስፖርት ለመዝጋት ማቀድ ምን ይሉታል?
ይህንን እቅድ ያዘጋጁ ሰዎች እንዴት እንዴት እንደሚያስቡ ለማወቅ አትጓጉም? ወይም ደግሞ እንዴት እንዴት እንደማያስቡ!
No comments:
Post a Comment