(ዘ-ሐበሻ) በሕወሓት ደህንነቶች ተንኳሽነት; በጎንደር ሕዝብ ቁጣ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል:: የጎንደር ከተማ በአሁኑ ወቅት ከሕወሓት መንግስት ቁጥጥር ውጭ መሆኗን የሚገልጹ ምንጮች ወታደሮች አሁንም ወደ ሕዝቡ እየተኮሱ ቢሆንም ሕዝቡም የአጸፋ ምላሹን በተለያዩ መንገዶች እየገለጸ ነው::
ከጎንደር የሚመጡ መረጃዎች እንደሚያመለከቱት የሕወሃት መንግስት በጎንደር ህዝብ ላይ ጥይት ቢያዘንብበትም ሕዝቡ ግን ከገጠር ጭምር እየተጠራራ ወደ ከተማ እየገባ ነው:: በተለይ የአርማጭሆ ሕዝብ ወደ ጎንደር በመትመም ከወገኖቹ ጋር በመቀላቀል ለሕወሃት መንግስት ራስ ምታት ሆኖበታል::
የከተማው ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ተቃውሞውን እና መንግስት እየፈጸመ ያለውን ግድያ እያወገዘ የሚገኘው የሕወሓት ባለስልጣናት ንብረት የሆኑ መኪኖችን እና ሱቆችን በማንደድ መሆኑም ተሰምቷል::
በተለይም በዛሬው እለትም 1ኛ ሁመራ ፔኒስዬን; 2ኛ ጣና ሆቴል; 3ኛ ሮማን ሆቴል; እና 4ኛ ቋራ ሆቴል መውደማቸውም ተሰምቷል::
በሌላ ዜና ሁለት የወያኔ ደህነቶች ዛሬ በጎንደር መገደላቸውን ቤተ አማራ አስታውቋል: እንደ ቤተ አማራ ዘገባ “የጎንደር አማሮች በሚያስደንቅ ጀግንነት ከህወሓት ሰዎች ጋር ተፋልመዋል። ፍጥጫው አሁንም እንደቀጠለ ነው። ትናንት ማታ ኮሮኔል ደመቀን ከከበባው በፍፅም ጀግንነት ያስወጡት የአርማጭሆ ፣ የጠገዴ እና የወልቃይት ገበሬ አማሮች ነበሩ። ከህዋህት ሰዎች በአይን ወድቀው የታዩ 9 አስከሬኖች ተቆጥረዋል ። ሰው እንደሚለው ከሕወሓት ልዩ ሃይል ከዚህ በላይ ተገሏል። እስከ አሁን ድረስ አስከሬናቸው ዝናብ እዬሰበደበው ያልተነሱ እንዳሉ ዘጋቢያችን አረጋግጧል።”
ቤተ አማራ ዘገባውን ቀጥሎ አሁን ቀበሌ አስራ ስምንት ከፍተኛ የአማራ ገበሬ ጦር ቦታ ይዞ እዬተጠባበቀ ነው። አራቱ ታፍነው የተወሰዱ ኮሚቴዎቻችን በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል። ያ ካልሆነ ከፍተኛ አደጋ እንደሚጥሉ ተናግረዋል። በአራቱም አቅጣጫ ወደ ከተማዋ የአማራ ገበሬ ጦር እዬተመመ ነው። ምንም እንኳ በየኬላው የመከላከያ ጦር ዘግቶ ቢጠብቅም አማሮች መግቢያ አላጡም ። በዛሬው እለት ብቻ ሁለት ከፍተኛ የህወሓት ደህንነቶች ተገለዋል ሲል ዘግቧል::
No comments:
Post a Comment