Translate

Wednesday, May 27, 2015

ውዝግብን ያስተናገደው የዛሬው የጦማሪያኑ እና የጋዜጠኞቹ የፍርድ ቤት ዝርዝር ዘገባ

ውዝግብን ያስተናገደው የዛሬው የጦማሪያኑ እና የጋዜጠኞቹ የፍርድ ቤት ዝርዝር ዘገባ
በትናንቱ የቪኦኤ ዘገባ ላይ አቃቤ ሕግ ቅሬታ አቀረበ
ጦማሪ አቤል ዋበላ ችሎት በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ
‹‹ሥነ-ሥርዓት ያዝ!›› ዳኞች
‹‹እናንተ ራሳችሁ ሥነ-ሥርዓት ያዙ! ይህ ችሎት ነው፡፡ ግልጽ ነው›› አቤል ዋበላ
‹‹ውሳኔው ለሁሉም ከሆነ፣ ለአቃቤ ህጉም ሆነ ለአለቃው ጠ/ሚኒስቴርም መሆን አለበት፡፡››
‹‹ጓደኛዬ (አቤል) የሚቀጣ ከሆነ ውሳኔው እኔም ላይ ይታዘዝ››
ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ

ትናንት ምሽት ከ3፡00 ሰዓት ጀምሮ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ (VoA)ን ሳዳምጥ ነበር፡፡ ከዘገባዎቹ መካከል ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ ስለሚገኙት ስድስቱ የዞን 9 ጦማሪያንና ሶስት ጋዜጠኞች በትናንትናው ዕለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የነበራቸውን የፍርድ ቤት ውሎ ይገኝበታል፡፡ ዘጋቢው ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ ጠበቃ አምሃ መኮንን በስልክ በማነጋገር የፍርድ ቤት ውሎውን አስደምጦን ለዛሬ በአዳሪ የተቀጠረ ጉዳይ መኖሩን ስሳማ ጠዋት ወደችሎት ላመራ ወሰንኩ፡፡ በችሎቱ ዛሬ በጥዋት ልደታ ፍርድ ቤት ደረስኩ፡፡ በችሎቱ በር አቅራቢያ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ፣ የአማሪካ ኤምባሲው ባልደረባ በላይ ለገሠና ሌሎች ጥቂት የውጭ ሀገር ዘጋቢዎች እና ዲፕሎማቶች ነበሩ፡፡ ከርቀት አብዲ ለሜሳንና ጓደኞቹን ሰላም አልኳቸው፡፡ ከነበላይ ጋር ስለሰሞኑ ምርጫ አወጋን፡፡ ትንሽ ቆይቶ የቪኦኤው ዘጋቢ መለስካሰካቸው አምሃም መጣ፡፡ ስለትናንቱ የዜና ዘገባው፣ ስለምርጫው ሁኔታ … ጥቂት አወጋን፡፡
ከ3፡50 ገደማ ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ ወደ ችሎቱ በፖሊሶች ታጅበው መጡ፡፡ [ጋዜጠኛ ተስፋለም ወደፍርድ ቤት ይዟቸው በመጣው የእስረኛ መኪና ውስጥ ሆኖ እጁን ለሰላምታ ሲያውለበልብ እኔና እና በላይ አይተነው ነበር፤ ላለፉት ዓመታት ከተስፍሽ ጋር ለፍርድ ቤት ዘገባ ነበር ልደታ የምንገኛኘው፡፡ አንዳንዴም አብረን ከቤት የምንወጣበት ጊዜም ነበር፡፡ ዛሬ እሱ ታሳሪ እኔ ደግሞ ዘጋቢ ሆኜ የሚመጣውን እያየን እንገናናለን፤ ይሄ ሀሳብ አዕምሮዬ ተመላለሰ - ውስጤ እንዳዘነ!] ሰላምታ ሰጥተናቸው ገቡ፡፡ እኛም እየተፈተሽን ወደችሎቱ ዘለቅን፡፡ ሁሉም ቦታ ቦታውን ያዘ፡፡ አቀማመጣቸውም ከፊት አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬ፣ ናትናኤል ፈለቀና ማህሌት ፋንታሁን ሲሆኑ፣ በመጨረሻው የእስረኞች ወንበር ላይ ደግሞ አቤል ዋበላ፣ ዘላለም ክብረት፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔና ተስፋለም ወልደየስ ተቀምጠው ነበር፡፡ ከረፋዱ 4፡10 ሰዓት ላይ የችሎቱ ዳኞች ተሰየሙና ‹‹እነሶሊያና ሽመልስ …›› በሚል የዕለቱ ችሎት ስራውን ጀመረ፡፡
የችሎቱ የቀኝ ዳኛ ጉዳዩ ለዛሬ ያደረበትን ጉዳይ ከገለጹ በኋላ ውሳኔ ማንበብ ጀመሩ፡፡ አቃቤ ሕግ ተጨማሪ ምስክሮች እንዲሰሙለት የጠየቀው ነገር ‹‹የደረጃ ምስክሮቹ በሥራ ምክንያት ስላላገኘናቸው›› ሲል ያቀረበው ሀሳብ ‹‹ሥለስራቸው በግልጽ አልተገነገረም››ና ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግን ጥያቄ ሳይቀበል ቀርቶ ውድቅ ማድረጉን ገለጸ፡፡
‹‹የሚቀሩ ሲዲዎች አሉኝ›› በማለት አቃቤ ህግ በድጋሚ ያቀረበውን ጥያቄም ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ አቃቤ ሕግ አቀርበዋለሁ የሚለው ሲዲ እንዲቀርብ ሲል ውሳኔ ሰጠ፡፡ ፍርድ ቤቱ ሲዲውን ከሰዓት በኋላ ማቅረብ ይችል እንደሆነም አቃቤ ህጉን ብርሃኑ ወንድማገኝን ጠይቆት ነበር፡፡ [ከቦታው ርቀት ከድምጹ ማነስ አኳያ የአቃቤ ህጉን መልስ ማድመጥ አልቻልኩም] ፍርድ ቤቱም ‹‹ሲዲው በጽ/ቤት በኩል ይግባና ዳኞች ካየነው በኋላ ‹ሲዲው በግልጽ ቢታይ ችግር አለው ወይስ የለውም? ቀሪ ተከሳሾችን ይጎዳል አይስ አይጎዳም?› የሚለውን አይቶ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 09 ቀን ቀጠሮ እንያዝ›› ብሎ ነበር፡፡
አቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝም ቅሬታ አለኝ በማለት ለችሎት ተናግረዋል፡፡ ሀሳብን በሚዲያ በመግለጽ በኩል ችግር መኖሩን ጠቁመው፤ ‹‹በትናንትናው ዕለት በቪኦኤ በቀረበው የፍርድ ቤት ዘገባ ላይ በጠበቃ አምሃ በኩል የቀረበው አስተያየት ሚዛናዊ ያልሆነና አንድ አካል ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው፡፡ የዘገባው አቀራረብ ትክክል አይደለም፡፡ በአንድ ወገን የቀረበ ነው፡፡ እንዲህ መዘገብ የለበትም፡፡ በአግባቡ ይዘገብ፡፡ በፍርድ ቤት ዘገባ ላይ ላይም ሥርዓት ይደረግ›› የሚል ይዘት ያለው አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ጠበቃ አምሃም ‹‹አቃቤ ሕጉ በዚህ መድረክ ላይ አንድ ተከራካሪ ናቸው፡፡ ሥርዓት የማስያዝ መብት የላቸውም፡፡ ዘገባው ችግር አለበት ካሉ ‹‹በምን ቀን የትኛው ጉዳይ ስህተት እንደሆነ በግልጽ ለፍርድ ቤቱ አቅርበው ይታረምልኝ ማለት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የችሎቱን ሥራ እንደሚመራ መሆን አይገባም፡፡ ትክክል አይደለም፡፡ እዚህ ችሎት ውስጥ ብዙ ጋዜጠኞች እና ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ጉዳዩ በተለያየ መንገድ ይዘገባል፡፡ የችሎት ጉዳይ እንዴት እንደሚዘገብ እናውቃለን፡፡›› በማለት መልስ ሰጡ፡፡ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ እጁን አውጥቶ ‹‹መናገር የምፈልገው ነገር አለ›› በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹ስለጉዳዩ ጠበቃው ተናግረዋል፡፡›› ሲሉ የመሃል ዳኛው ተናገሩት - እንዲተው፡፡
የመሃል ዳኛው ‹‹ዘገባው በፍርድ ቤት ውሎ ላይ የመደምደሚያ ነገር ቀርቧል›› ሲል አቃቤ ሕግ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ጠበቃውም ምላሽ ሠጥተዋል፡፡ ተወያይተን ብይን እንሰጥበታለን›› አሉ በድጋሚ፡፡
እኒሁ ዳኛ ወደናትናኤል እያዩ ‹‹3ኛ ተከሳሽ ያለኸው ችሎት ውስጥ ነው፡፡ ወደኋላ ዞረህ አታውራ፡፡ ቁጭ በል፡፡ ችሎቱን የሚመራው ፍርድ ቤት ነው፡፡ ተው ተው ስትባል ተው!›› አሉትና ‹‹በአጠቃላይ ዘገባን በተመለከተ ከዚህ በፊት አስጠንቅቀናል፡፡ ፍርድ ቤት በማስረጃ ተረጋግጧል /አልተረጋገጠም፤ ተመስክሯል/አልተመሰከረም/ ነጻ ነው /አይደለም ይላል፡፡ ይሄን የሚለው ሌላ አካል አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ነው መዘገብ ያለበት፡፡ ተመስክሯል አልተመሰከረም የሚለው አይሰራም፡፡ አቃቤ ህግ በዝርዝር ያቀረበው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን፣ በዚህ መንገድ ካልተዘገበ ለወደፊቱ ይስተካከል›› የሚል ብይን ሰጡ፡፡
ጦማሪ ናትናኤል እና ጋዜጠኛ አስማማው ወ/ጊዮርጊስ ‹‹የምንናገረው ነገር አለ›› ብለው እጃቸውን አወጡ፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ብይን ሰጥተናል ሌላ ነገር ከሆነ ነው …›› ሲሉ የመሃል ዳኛው በድጋሚ ተናገሩ፡፡ የማህሌት ጠበቃም እጃቸውን አውጥተው ‹‹ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ ጠበቃው ተናገሩ የተባለው ተነሳ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በሚኒስትር ደረጃ ያሉ ሰዎች …›› ብለው እየተናገሩ እያለ ሰብሳቢው ዳኛ አቋረጧቸውና ‹‹ጠ/ሚኒስትርን …በተመለከተ ችሎቱ አይመለከተውም፡፡ (በዚህ የፍርድ ቤት ጉዳይ ላይ ያልቀረበ ነገር ለማለት ይመስለኛል) እኛ እዚህ ያለውን ጉዳይ ነው የምናየው፡፡ ችሎትን በማወክ …›› ሲሉ መልስ ሰጡ፡፡
ናትናኤል መናገሩን ቀጥሎ ‹‹በዚህ ጉዳይ ሀሳባችንን በነጻነት የመግለጽ መብታችን ተከልክሏል›› አለ፡፡ ‹‹እኛ እኮ ውሳኔ ለሁሉም ሰጠን፡፡›› ሲሉ ዳኛው በድጋሚ ተናገሩ፡፡ ናትናኤልም ‹‹ውሳኔው ለሁሉም ከሆነ፣ ለአቃቤ ህጉም ሆነ ለአለቃው ጠ/ሚኒስትር መሆን አለበት፡፡›› ሲል ገለጸ፡፡
መጨረሻ ረድፍ ላይ የቆመው ጦማሪ አቤል ዋበላም እጁን አውጥቶ መናገር ፈለገ፡፡ ዳኞቹ ‹‹ሥነ-ሥርዓት ያዝ›› አሉት ፡፡ እሱም ቆጣ ብሎ ‹‹እኛም የምንናገረው ነገር አለ፡፡ እናንተ ራሳችሁ ሥነ-ሥርዓት ያዙ! ይህ ችሎት ነው፡፡ ግልጽ ነው›› አለ፡፡
ዳኞች እርስ በእርስ መነጋገር ጀመሩ፡፡ የማህሌት ፋንታሁን ጠበቃ (እኔ ሳየው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው) ወደአቤል ጋር መጥተው ትንሽ ተነጋገሩ፡፡ የቀኝ ዳኛው አዲስ ወረቅት አውጥተው መጻፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ጠበቃው ‹‹ተከሶሾቹ ሊጠይቁ የፈለጉት ሲቀርብ ስለታሰበው ሲዲ ነው፡፡ ከሶሊያና ጋር የሚገናኝ ሰለሆነ›› ሲሉ ለዳኞች ተናገሩ፡፡
ሰብሳቢ ዳኛው ‹‹አሁን ስለተፈጠረው ነገርስ (ስለአቤል ንግግር)?›› ሲሉ ጠበቃውን ጠየቋቸው፡፡ ‹‹በይቅርታ ይታለፍ›› የሚለው የጠበቃው መልስ ነበር፡፡ የቀኝ ዳኛው ‹‹ስለሚሉን ነገር (በይቅርታ ይታለፍ) ራሱ አቤል መልስ ይስጥ›› ካሉ በኋላ ‹‹ስሜታዊ መሆን ከእናንተ አይጠበቅም፡፡ የተማራችሁ ናችሁ፡፡ ፍርድ ቤትን ማክበር አለባችሁ›› ሲሉ ተናገሩ፡፡ አቤል ‹‹መናገር የፈለኩት …›› ‹‹አይ እሱን አይደለም፤ አሁን በስሜት ስለተናገርከው ነገር (መልስ ስጥ ነው)›› አሉት ዳኞቹ፡፡
አቤል ወደፊት ቀረብ አለና ‹‹እኔ ምንም አላጠፋሁም፡፡ የጠየኩት ሕገ-መንግሥታዊ መብታችንን ነው፡፡ መናገር እየቻልን ጥያቄያችንን በጽሑፍ አመልክቱ ለምን እንባላለን?›› ሲል መለሰ፡፡ ሰብሳቢው ዳኛ ‹‹አሁን የምትመልሰው በችሎት ይቀዳ›› አሉት፡፡ አቤልም ‹‹በድምጽ አልቀዳም፣ ጥያቄያችን አልተሰማም፡፡ ፍርድ ቤቱ በግልጽ ይስማን›› በማለት ወደቦታው ተመለሰ፡፡ ችሎቱም ወዲያው አቤልን በችሎት መድፈር ወንጀል ጥፋተኛ እንዳለውና ተገቢውን ቅጣት ለመወሰን ቀጠሮ እንደሚሰጥ ተናገረ፡፡
ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉም ተነስቶ ቆመ፡፡ ዳኛው ‹‹ተቀመጥ›› አሉት፡፡ ‹‹አልቀመጥም፣ ጉዳዩ የእኔም ነው›› ሲል መለሰ፡፡ ከፊት ያለው ናትናኤልም ቆመ፡፡ ‹‹ተቀመጥ›› አሉት፡፡ ‹‹የጓደኛዬ ጥያቄ የእኔም ነው›› ሲል ተናገረ፡፡
ጠበቃውም ‹‹ደንበኛዬ ችሎት ለመድፈር ሆን ብሎ ሳይሆን ቀደም ሲል ከተሰጠው ትዕዛዝ ጋር በተያያዘ ሊጠይቅ ሲል ዕድል የተነፈገ መስሎት ነው፡፡ ይሄንን በስሜት የተሞላ የተናገረውን ንግግር ችሎት በመድፈር ሳይሆን በተግሳጽ እንዲያልፈው ሲል እናመለክታለን›› አሉ፡፡ ዳኛው ይሄንን መልስ መዘገቡ፡፡
ችሎቱም በሰባተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም፣ እንዲሁም በ1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስን የሚመለከተውን የአቃቤ ሕግ የሲዲ ማስረጃ ቀደም ብሎ በመመልከት ‹‹ሲዲው በግልጽ ቢታይ ችግር አለው ወይስ የለውም? ቀሪ ተከሳሾችን ይጎዳል አይስ አይጎዳም? በሚለው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 08 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ናትናኤልም ‹‹ጓደኛዬ (አቤል) የሚቀጣ ከሆነ ውሳኔው እኔም ላይ ይታዘዝ›› ሲል ለችሎቱ ተናገረ፡፡ ዳኛውም ‹‹ሌሎቻችሁን አይመለከትም፡፡›› ካሉ በኋላ ለፖሊሶች ተከሳሾቹን ከችሎት እንዲያወጧቸው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ናትናኤልም ‹‹የሚደረገው ነገር ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፤ ለሌሎችም ትምህርት አይሆንም›› በማለት ለዳኞች ድምጹን ከፍ አድርጎ ነገራቸው፡፡ ሰብሳቢው ዳኛው ‹‹በስሜት እየተነጋገርን የችሎት ሥራ እንስራ ታዲያ? …›› ሲሉ መለሱ፡፡ ፖሊሶችም ወደጦማሪያኑንና ጋዜጠኞቹ ተጠግተው ‹‹ከችሎት ውጡ›› በማለት በር ላይ በካቴና እጆቻቸውን እያሰሯቸው ወደእስረኞች መኪና ይዘዋቸው ሄዱ፡፡
እኛም ከችሎት ወጣን፡፡ እኔም የዛሬ ፍርድ ቤት ውሎን በቀድሞ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙኑኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ‹‹የመለስ ትሩፋቶች›› በተሰኛው መጽሃፋቸው ላይ ባስተዋወቁን ‹‹የካሳንቺሱ መንግሥት›› መቀመጫ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ላፕቶቴን አውጥቼ ያየሁትን፣ የሰማሁትንና የተከታተልኩትን እንዲህ ከትቤ አስነበብኳችሁ፡፡
መልካም ቀን!
Elias Gebru Godana

No comments:

Post a Comment