አዜብ ጌታቸው
ከሁሉ አስቀድሜ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በሃገራችን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በወረደው የመከራ ናዳ ግንባር ቀደም ተጠቂ የሆኑትን ሰማዕት ወገኖቻችንን ነፍስ ጌታ በቀኙ ያስቀምጣት ዘንድ በጸሎት የታገዘ ምኞቴን ልገልጽ እወዳለሁ። በማስከተልም ድንገተኛና አስደንጋጩ ሃዘን ለጎዳው የቅርብ ቤተሰባቸውና በአጠቃላይም ለመላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ መጽናናትን አብዝቶ ይስጠን እላለሁ።
ውድ ወገኖቼ! ያለፉት ሳምንታት እንደ ሃገር፦ ለኢትዮጵያ እንደ ዜጋ፦ ለኢትዮጵያዊው ሁሉ አሳዛኛ፤ አስደንጋጭ፤ አሰቃቂ፤ አስቆጭ …. ነበሩ። ሃዘኑ የሚከብደው ደግሞ ለደረሰብን ጥቃት ምንም ምላሽ መስጠት የማንችል መሆናችንን ስናስብ ነው። በጀግንነት ያለፉት ሰማዕታት ያልሞቱት እኛ በቁም ያለነው ብቻ የሞትነው ሞት ይህ ነው። ጥቃት መመከት አለመቻላችን!። ለማንኛውም ሁላችንም በዚሁ ስሜት የከረምን በመሆኑ መጽናናትን ይስጠን ብዬ ልለፈው፡፡
የዛሬው ጽሁፌ የሚያጠነጥነው በነኝሁ በመከራ ሳምንታት ውስጥ በታዘብኳቸው ሁነቶች ዙሪያ ነው። በተለይም የህውሃት መንግስት ባለስልጣናትና የደጋፊዎቻቸውን ልማታዊ የሃዘንተኝነት አክራሞት ይመለከታል።
የባለስልጣናቱ ድንቁርና፦
ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ ወያኔ መራሹ መንግስት አንድ ወጥ አመራር የሚሰጥ መሪ በማጣቱ ድግሱ ሁሉ የጨበሬ ተስካር እየሆነ እያስተዋልን ነው።
ለዚህም ይመስላል እንደ መና ከሰማይ የወረደላቸውን “ፖለቲካዊ ትርፍ” የሚያስገኝ አጋጣሚ እንኳ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ሲሞክሩም አይታዩም። ሰውየው (መ.ዜ) “ልማታዊ” ና “ሽብርተኛ” በሚሉት ቃሎች ላይ ፖዝ አድርጓቸው ሄዶ፦ ፖለቲካውንም፤ ብሄራዊ ሃዘኑንም፤ ሃይማኖቱም፤ ማህበራዊ ቀውሱንም ….. በልማታዊና በሽብርተኛ መነጽር ከማየት፤ በልማታዊና በሽብርተኛ ሚዛን ከመስፈር፤ በልማታዊና በሽብርተኛ ቋንቋ ከመተርጎም በተለየ የሚያውቁት ነገር ያለ አይመስልም።
ቀደም ሲል (ሰውየው በነበረበት ወቅት) ያደርጉት እንደነበረው በብልጣ ብልጥ አካሄድ ያገኙትን ቀዳዳና አጋጣሚ ሁሉ የመንግስትን መልካም ገጽታ ለመገንባት ሊያውሉ ሲሞክሩ አይስተዋሉም።ጭራሹኑ አካሄዳቸው ሁሉ ፍርስራሹን ገጽታ የሚያጠፋ እየሆነ ነው።
በስልጣን እርከኑ በረከት ስምዖንን የተካው፤ በተግባር ግን ሽመልስ ከማልን ተክቶ የወያኔን ነውር እንዲተነፍስ የተፈረደበት የወቅቱ አፈቀላጤ ሬድዋን ሁሴን በሊቢያ ከተሰዉት ወገኖቻችን ጋር በተገናኘ የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ ለዚህ የእውር ድንብር አካሄዳቸው ማሳያ ናቸው።
ገዳዮቹ(አይሲስ) ኢትዮጵያዊያንን መግደላቸውን እየተናገሩ የለቀቁት ቪዲዮ በመላው አለም ከተሰራጨ በኋላ “ሟቾች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን አላረጋገጥንም” ማለት ምን ማለት ነው? ይህን ከማለትስ ምን የፖለቲካ ጥቅም እናገኛለን ብለው ነው? የሚለው ጥያቄ የብዙ ወገኖች ጥያቄ ነው።
በኔ ጥርጣሬ ግን ሬድዋን ሁሴን “ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አላረጋገጥንም” ያለው የሟቾች ማንነት በርሃ ውጦት የሚቀር እንጂ በገሃድ የሚወጣ ስላልመሰላቸው “ኤርትራዊም ሊሆኑ ይችላሉ” በሚል እሳቤ ህዝብን ማምታታት ከተቻለ ዕድሉን ለመሞከር ያደረገው ይመስለኛል። ትልቁ ስህተቱ ግን ይህን ቃል ካፉ ሲያወጣ ሰብአዊነት የጎደለው መንግስት ቃል አቀባይ መሆኑን እያረጋገጠ መሆኑን አለማስተዋሉ ነው። እንደ መንግስት አፈ ቀላጤነቱ ማድረግ የነበረበት ከሁሉም በፊት ሟቾች ማንም ይሁኑ ማን…. የግፍ ግድያውን በጽኑ በማውገዝ የሟች ቤተሰቦችን ማጽናናት ነበር፡፡ እሱ የመረጠው ግን ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አላረጋገጥንም ካለ በኋላ፦
“እኛ ከጅምሩም ሽብርተኝነት እየተዋጋንና እየታገልን በመምጣታችን የአገሪቱን ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት በአስተማማኝ ማረጋገጥ ችለናል።”
በማለት በታረዱት ወገኖቻችን ደም ላይ የልማታዊውን መንግስት አረንጓዴ ባንዲራ ለማውለብለብ መሞከርን ነው። ታዲያ ይህ ከአንድ ፖለቲከኛ የሚጠበቅ ስልታዊ አካሄድ ነው ትላላችሁ?
“ድርጊቱ ለሌላው ወገን መማሪያ ይሆናል” ማለቱስ? እስይ! አጀት ቅቤ ..ማለት አይመስልም?
“የአይሲስ ተግባር ልማታችንን አያደናቅፍም!” የሚለው መፈክር ደግሞ ሌላው የዚህን መንግስት ተብዬ ቡድን መካሪ አልባነት የሚያሳይ ነው።
አንድ በህዝብ የተጠላ መንግስት የህዝብን ቀልብ ሊገዛና ስሙን ሊያድስ ከሚችልባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች አንዱ በሃገርና በህዝብ ልዋላዊነት ላይ ይህን መሰል ጥቃትና መከራ ሲደርስ፤ የህዝብን ፍላጎትና ስሜት ያማከለ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ሲችል ነው። ወያኔ ግን ይህን አላደረገም። ለምን? መልሱ በህዝብ ላይ ቂም የሚይዝ መንግስት ስለሆነ ነው!!!። ሬድዋን ሁሴንም ከወራት በፊት በአሜሪካ በደረሰበት ውርደት ቂሙን መወጣቱ ነበር !።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እነኚህ ሰዎች (የወያኔ ባለስልጣናት) የሚያደርጉት ሁሉ የጠፋባቸው መሆኑን የሚያሳይ ሰሞኑን ሌላም ክስተት ተስተውሏል።
አድምጣችሁት ከሆነ? የጠ/ሚሩ የደህንነት አማካሪና ከህውሃት ቱባ ባለስልጣናት መካከል አንዱ የሆነው ጸጋዬ በርሄ ከመራው በትግራይ ከተካሄደው ሚስጥራዊ ስብሰባ ሾልኮ ቢቢኤን ለተሰኘው የዜና አውታር የደረሰው የድምጽ ዘገባ በጋዜጠኛ ሳዲቅ አቅራቢነት ለህዝብ ጆሮ በቅቷል።
በዚህ ስብስባ ላይ ከተደመጡት አስተያየቶች በጣም ያስገረመኝ ቱባው ባለስልጣን ጸጋዬ በርሄ ሰማያዊ ፓርቲና ግንቦት ሰባትን ከአይሲስ ጋር ለማገናኘት የሞከረበት ተራ ንግግር ነው።
ጸጋዬ በርሄ ለተሰብሳቢው ሊያስጨብጥ የፈለገው ሃሳብ ሰሞኑን በሊቢያ በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ግድያ የሰማያዊ ፓርቲና የግንቦት ሰባት እጅ አለበት የሚለውን ቀሽም ተረት ነው። እናም ሁለቱ ድርጅቶች(ሰማያዊና ግንቦት) በሃገር ውስጥ መፈጸም ያቃታቸውን የሽብር ተግባር በውጭ ከሚገኙ አሸባሪዎች ጋር ተላልከው አስፈጸሙ።ኢትዮጵያዊያኑን አስገደሉ ነው የሚለው ጸጋዬ በርሄ። ። ከ6ኛው ደቂቃ ጀምሮ ያድምጡት
ከዚህ ሌላ ታዲያ ምን የድንቁርና መገለጫ ይኖራል ወገን? ሰማያዊን ከግንቦት7 አገናኝቶ፤ ሁለቱን ደግሞ ከአይሲስ ጋር ተላልከው ኢትዮጵያዊያንን አስገደሉ ማለት ምን ይባላል? ውንጀላ? የምርጫ ቅስቀሳ? በአስማት እንኳ ሊሆን የማይችል ነገርን ማን ይቀበለኛል ብሎ ነው የተናገረው?። በርግጥም እነዚህ ሰዎች መካሪ አጥተዋል… ወንበሩም ሺህ መሪውም ሺህ ሆኗል! ስርዓተ አልበኝነት ይሏል ይህ ነው።
በሌላ በኩል የጸጋዬ ንግግር የሚያሳያን፡፟ እነኚህ ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ህዝብ መስማት እንጂ ማሰብ እንደማይችል አድርገው እየቆጠሩት መሆኑን ነው ።
በስብሰባው ላይ የተሳተፈው እኮ በአንድ ወቅት ሟቹ ጠ/ሚ “ከወርቅ ህዝብ በመፈጠሬ እኮራለሁ” ያሉት የትግራይ ህዝብ ነው። ታዲያ ንቀቱ ከየት መጣ ? ለነገሩ “የማይመስል ነገር … አትንገር እንዲሉ” በዛው ስብሰባ ላይ “ብሄራዊ ሃዘኑን ለፖለቲካ መጠቀሚያ አታድርጉ” የሚል አስደንጋጭ ተቃውሞ እንደገጠማቸውም ከሳዲቅ ዘገባ አድምጠናል።የማይጠበቅ አልነበረም። እንዴት ያለ ድንቁርና ነው ወገኖች?
ሟቹ ጠ/ሚር በአንድ ወቅት የህውሃት አባል የጥንካሬ መለኪያው “ታማኝነት” እንጂ “ብቃት” አለመሆኑን ግልጽ አድርጎ መናገሩን ብዙዎች የምናስታውስ ይመስለኛል። በእርግጥ ጠ/ሚሩ በወቅቱ “እኔ ከሞትኩ ….አይብቀል፡” እንዳለቺው እንስሳ ራሱን ዘላለማዊ አድርጎ በማሰቡ፤ እሱ የሚወጥነውን ሴራ የለጥያቄና ያለማወላወል የሚተገብር ታማኝ ደንቆሮ መሰብሰብ ለስራው ቅልጥፍና እንደሚያመቸው አስቦ ያደረገው መሆኑ ለማንም አይጠፋውም። ይሁንና ማንም ዘላለማዊ የለምና የሴራው ኪሮሽ ሲሰበር ደንቆሮው ሜዳ ፈሶ ቀረ። ድንቁርናም ነገሰ! እንሆ ሁሉም ነገር እየተበለሻሸ ሄደ…
በዚሁ በወያኔ ባለስልጣናት ድንቁርና ዙሪያ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንወያይ እንዲህ ስትል አንድ ድንገተኛ ጥያቄ አቀረበችልኝ፤
የ11ኛ ክፍሉን ጄነራል ሳሞራ የኑስንና በሶስት መንግስታት ውስጥ አልፈው በሺ የሚቆጠር ዜጋ ያነጹትን የፕ/ር መስፍን ወልደ ማሪያምን ስብዕናና እንደ ዜጋ ለሃገራቸው ያደረጉትን አስተዋጾ እንዴት ታነጻጽሪዋለሽ? የሚል ነበር ጥያቄዋ፡
ለደቂቃዎች ያህል ምንም ትንፍሽ ማለት አልቻልኩም! ፊቴን ከስክሼ ዝም ብዬ አየኋት!
ወዳጄም መልሳ “ይገባኛል ጥያቄዬ ከበደሽ አይደል?” አለችኝ
እኔም እንደምንም ሃሳቤን ሰብስቤ፡ አይ ጥያቄሽ ከብዶኝ ሳይሆን ቀፎኝ ነው አልኳት።
ወዳጄ ቀጠለችም፡ “በርግጥም የሚቀፍ ጥያቄ ነው፡፡ ሁለቱ ሰዎች በምስራቅ አፍሪካ ከመወለዳቸው በስተቀር (ሳሞራ ኤርትራዊ መሆኑን ለማመላከት ነው) ምንም የሚነጻጸር ነገር የላቸውም። የግድ ይነጻጸሩ ከተባለም ልዩነታቸው በሞተና በህይወት ባለ ሰው መካከል የሚኖር ልዩነት ነው የሚሆነው፡፡ ነጥቤም ይኸው ነው! ዛሬ በብሄራዊ ሙዚየም ኃውልት የቆመለት ደግሞ ይኸው የሞተ ሰው ነው።” አለችና በቁጭት አስደመመችኝ፡፡
የባለስልጣናቱን ድንቁርና ብቻ ሳይሆን ዕውቀት በኮሰሰበት ድንቁርና በነገሰበት ዘመን ላይ እንደምንገኝ ከአይምሮዬ ሊጠፋ በማይችል ዘግናኝ ንፅፅር(ፕ/ር መስፍንና ሳሞራ ይዘገንናል)አሳየቺኝ።
የደንቆሮዎች ዘመን ላይ ለመገኘታችን ከዚህ በላይ ምን ማሳያ ይገኛል? መልሱን ….
የልማታዊ ሃዘንተኞች አክራሞት
ባለፉት ሳምንታት ሁለት አይነት ኢትዮጵያዊ ሃዘንተኞችን አስተውለናል።ልማታዊ ሃዘንተኞችና ነጻነት ናፋቂ ሃዘንተኞች።
ነጻነት ናፋቂው ወገን (ራሴን ጨምሮ) ባለፉት ሳምንታት በየመን ፤በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን እልቂት ያስተናገደው ቃላቶች ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ በተደበላለቀ ስሜት ነበር። ቁጣውም ፤ቁጭቱም ፤ ምሬቱም ፤ ሃዘኑም መሪር ነበርና በየሃገሩ ያሉ የደቡብ አፍሪካ ኤንባሲዎችን አጨናንቋል። በሻማ ማብራት ሥነ-ስርአት ላይም በእንባ ተራጭቷል።ለጊዜው ግን ትኩረቴ አግራሞት በፈጠረብኝ በልማታዊ ሃዘንተኞች ላይ ነውና ወደዛው ላምራ)
በየሃገሩ በሚገኙ የወያኔ አምባሳደሮች መመሪያ ሰጭነት የተንቀሳቀሱት(አምስት/ለአንድ) ልማታዊ ሃዘንተኞች ደግሞ ከሃዘኑ ይልቅ ቅድሚያ የሰጡት በሃዘኑ ሳቢያ የልማታዊው መንግስት መልካም ገጽታ እንዳይበላሽ ጥንቃቄ ማድረግን ነበር።
በመሆኑም ለዚህ ሁሉ እልቂት አብይ ምክንያት ሆኖ ወገኖቻችንን ለስደት ጎርፍ የዳረገው “ዘረኛው” መንግስት እንዳይነካ “ከፖለቲካ የጸዳ የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓት” አዘጋጅተዋል፡፡ “መንግስት” የያዘው የልማት አቅጣጫ ስደቱን ይገድበዋል ሲሉም በሻም ጭላንጭል የታጀበ የሚያቅለሸልሽና ደም ደም የሚል ዲስኩር አስደምጠውናል።(ከፖለቲካ ነጻ የሆነ የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርአት የሚል ማስታወቂያ በፌስ ቡክ ላይ ተለጥፎ አይቻለሁ።)
ለዚህ መገለጫ የሚሆነው፡ በሬድዮ ጣቢያዋ የመንግስትን መልካም ገጽታ ለመገንባት በምታቀርበው የዳንቴ ተረቶቿ የምትታወቀው ሚሚ ስብሃቱ እግር ጥሏት ይሁን ዶላር ጠርቷት የተገኝችበት በዋሽንግቶን ዲሲ የወያኔ ኤንባሲ የተከናወነው ልማታዊ የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓት ነው።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ድምጻዊያን በእንጉርጉሮ ጸሃፍት በብእራቸው የኔቢጤውም በጩኸትና በለቅሶ የሃዘን ስሜቱን ሲገልጽ ሰንብቷል። እንጉርጉሮውም፤ ግጥሙም ለቅሶና ጩኸቱም ብቻ ሁሉም ሁሉም፤ ለሰማዕታቱ ብቻ ሳይሆን በጣር ላይ ለምትገኝ ሃገራችንም ጭምር ነበር። የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሃዘን ድርብ ነው።
የልማታዊ ሃዘንተኞች አክራሞት ግን ለየት ያለ ነበር፡፡ የሞቱትን ነፍስ በቀኝህ አውልልን ፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ስጥልን! ከሚል ማሳረጊያ ጸሎት ይልቅ “በሽብርተኞች ልማታችን አይቆምም! አንደናገጥም!” የሚል መዝሙር ነበር ለሟች ቤተሰቦች ማጽናኛነት የተዘመረው።
አሁን ይሄ ምን ማለት ነው? የሟች ቤተሰቦችን ፊት ለፊት አስቀምጦ “በሽብርተኞች ልማታችን አይቆምም! አንደናገጥም!” ብሎ መዘመር እውን የሟቾች የነእያሱ፤ የነባልቻ፤ የነፍቃዱ፤ የነጀማል ….. እናቶች በጸሃዩ መንግስታችን የልማት እንቅስቃሴ እንባችን ይታበሳል! ብለው እንዲጽናኑ ተስቦ ነው?
ሃዘንተኛ በመዝሙር ይጽናናል እንዴ? ሃብት ሲበዛ ባህልና ወግ ይረሳል እንዴ?
በእርግጥ በትጥቅ ትግል ወቅት ጓዶች ሲወድቁ የቀሪውን ጓድ ሞራል ለማነጽ “ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም” በሚል ይዘመር እንደነበር እንሰማለን… ታዲያ በግፍ የተገደሉት ወገኖች የማን ታጋዮች ናቸው ለማለት ይሆን ወላጆቻቸውን አስቀምጦ “በሽብርተኞች ልማታችን አይቆምም! ብሎ መዘመር ያስፈልገው? ግራ ቢገባኝ ጊዜ ወስጄ ልማቱ ከሟቾችም ሆነ ከሟቾቹ ወላጆች መከራ ጋር ሊገናኝ የሚችልበትን ቀጭን መስመር ለማግኘት ብዙ አሰብኩ…ምንም ምንም ላገኝ አልቻልኩም። እናም….አሁንም ድረስ ግራ እያጋባኝ ያለ ነገር ነው።“በሽብርተኞች ልማታችን አይቆምም!”
ሌላው ልማታዊ ሃዘንተኛ የትናቱ ብሄራዊ ወታደር ዛሬ ደግሞ ለአገር ሻጮች በባንዳነት አድሮ ሚሊየነር ለመሆን የበቃው ሰራዊት ፍቅሬ “ከስደት ይልቅ አሹቅ በልቶ በሃገር መኖር ይሻላል” ሲል መመጻደቁንም ሰምተናል።
ልማታዊ ሃዘንተኛ ሰራዊት ፍቅሬ “ማጣት” ና “ድህነት”ን ከምንም በላይ ያውቃቸዋል። የዛሬን አያድርገውና በማስታውቂያ ሚ/ር በር ላይ ቆሞ ማስታወቂያ ሊያስነግሩ የሚመጡ ሰዎችን ላንብብላችሁ እያለ 2 ና 3 ብር ይጠይቅ በነበረበት ወቅት “ድህነት” ታላቅ ወንድሙ “ማጣትም” ጓደኛው ነበር። ዛሬ ያ ሁሉ አለፈና ይህን ለማለት በቃ።
በሰው ቁስል እንጨት ሰደደ!፤ በወገኖቻችን ደም ተመጻደቀ!። ለመሆኑ ሟቾቹ ሁሉ አሹቅ ንቀው የተሰደዱ መሆናቸውን በምን አወቀ? የኢኮኖሚ ስደተኞች መሆናቸውን አድምቃችሁ አሳዩ የምትል ለልማታዊ ሃዘንተኞች የተሰጠች ቀጭን መመሪያ ትሆን? ለነገሩ እንደ ሰራዊት ያለ 8+ምላስ አይነቱ ለአገዛዙ አድሮ ሚሊየነር ሲሆን ባለዲግሪው እየተሰደደ በየበርሃው ማለቁ በራሱ ሌላው የደንቆሮዎች ዘመን ላይ መገኘታችንን የሚያሳይ ነው።
ይልቅዬ፦ በአቶ መለስ ሞት ማግስት የውዳሴ እንጉርጉሮ ገጥሞ ልማታዊ አርቲስቶች መደዳ ያየነው ጌትነት እንየው “ማርም ሲበዛ ይመራል!” በሚል ስሜት ይመስላል ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ባሉበት ያቀረበው ግጥም ልብ የሚነካ፤ የህዝብን ስሜት ያንጸባረቀንና ሃዘንተኞችንም ያጽናና ነበር። “እንቢኝ ለነጻነቴ!” ብሎ የበላይ ዘለቀን ገድል የተወነ አርቲስት ፤ በዛው አምደበቱ “መወድሰ መለስ ዜናዊ” ሲያንጎራጉርበት መስማታችን ቢያስደነግጠንም፤ ዛሬ ደግሞ ከተኛበት ነቅቶ፤ የፈሰሰው የህዝብ ልጆች ደም አንገፍግፎት ያከበረውን ህዝብ አክብሮ ብሶቱን በመግለጹ ደስ ብሎናል።
በሙያችሁ ለወገኖቻችሁ ያዜማችሁ ፤ የጻፋችሁና በተለያየ መንገድ ብሶቱን የገለጻችሁለት ሁሉ ክብር ለናንተ ይሁን!
የኢትዮጵያ ትንሣዔ ቅርብ ነው!!!።ያኔ ሆዳሞች የበሉትን ብቻ ሳይሆን የጠቡትንም ይተፋሉ። አዎ ያኔ! ግፈኞችም በሰፈሩበት ቁና ይሰፈራሉ። አትጠራጠሩ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
አዜብ ጌታቸው
azebgeta@gmail.com
azebgeta@gmail.com
No comments:
Post a Comment