Translate

Monday, May 18, 2015

የመሪዎች እምባ

የመሪዎች እምባ

hailemariam d


ከስም ልጀምር፣ የዛሬ ወጣቶች በተለይ ዘፋኞች ስማቸው በመጠኑ ተቆርጦ ወይም አንሶ ሲጠሩ እየሰማን ነው፤ ቴዎድሮስ – ቴዲ ብዙ ባያስከፋም ተያይዘው የቀጠሉት ዘፋኞች ግን እስከ አባታቸው ስለሚያሳንሱት ኢትጵያዊ ስም መሆኑ ራሱ አጠራጣሪ የሆነብኝ ጊዜ አለ። እስቲ አሁን ጃህ ሉድ አጥሮ ነው ወይስ ተቆርጦ ቻቺ፣ ጃኪ፣ ጂጂ፣ አቢ፣ ኢሚ፣ ዮሲ፣ ጃኪ-ጎሲ፣ ሚሊ፣ ሚኪ፣ ዮኒ፣ … ልተዋቸው።

እንደውነቱ ከሆነ ይህ በፊትም እንዳለ የሚጠቁሙ ማስረጃዎች አሉ አጼ ቴዎድሮስ (መይሳው) መዩ ይባሉ ነበር። ገብርዬም ስማቸው አጥሮ ነው ገብርዬ የሆኑት፣ ኃይለሥላሴም ኃይሌ፣ መንግሥቱም መንጌ ተብለዋል። መለስን መሌ ሲባሉ ባልሰማም ሊባልላቸው ይችል ነበር። በረከት ቤኪ፣ ተፈራ ተፌ … መባላቸውን ግን ሰምቻለሁ። የኃይለማርያም ደሳለኝ ስም ረዥም ነው መቆረጥ ይገባዋል፤ ኃይሌ ሊባል ይቻል ነበር፤ ግን ኃይሌ ለሳቸው እንደ ረዥም ኮት አያምርባቸውም። ቢያምርስ ምን ኃይል አላቸውና ኃይሌ ይባሉ?
የለቅሶ ነገር ሲነሳ ደግሞ “ዋይ ዋይ ሲሉ” በማለት አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ያፈሰሰው እንባ የማንንም አንጀት የሚያላውስ ነበር። ነጋሶም የፍርድ መዛባትን፣ የሕዝብ ውርደትን፣ የህልውና መደፈርን አይተው ደጋግመው በአደባባይ አልቅሰዋል። የነጋሶም እንባ በቀልድ አልፈሰሰችም፤ ሆድ ማገላበጥዋ አልቀረም። ነጋሶ መሪ ነበሩ፤ ከኢትዮጵያ መሪዎች ያለቀሱ እሳቸው ብቻ አይደሉም አጼ ቴዎድሮስም አልቅሰዋል፤ ፈርተው ተሰድበው ተገምግመው አልነበረም ያለቀሱት፤ አንድ ሊያደርጓት የጣሩላት አገርን መጨረሻ ሳያዩ በነጭ ወታደሮች ተከበው የመጨረሻ ሰዓታቸው መቃረቡን ሲያውቁት፤ የዚች አገር ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን? ብለው ነበር ያለቀሱት። የዛሬ ውድቀታችን፣ የዛሬ ለቅሶአችን፣ የዛሬ ስደታችን፣ የዛሬ መታረዳችን ያን ጊዜ ታይቷቸው ነበር ያለቀሱት። ሰላሙን ሊያስከብሩለት፣ መብቱን ሊያስጠብቁለት፣ አንድ ሊያደርጉት የተነሱለትን ሕዝብ በትነውት መሞታቸው ነበር ያስለቀሳቸው።
ጃንሆይም አልቅሰዋል፤ ያስለቀሳችው ግን ሃምሳ ዓመት ከኖሩበት ቤተ መንግሥት በመውጣታቸው፣ ከተከበረው ዙፋናቸው በመውረዳቸው አልነበረም፤ እንደውም «… ለአገር በጎ አስባችሁ ከተነሳችሁ፣ የአገርን ጥቅም ከራስ ጥቅም ማስቀደም አይቻልም፤ እኛ እስካሁን አገራችንና ሕዝባችንን በምንችለው አገልግለናል፤ አሁን ተራው የኛ ነው ካላችሁ ኢትዮጵያን ጠብቁ …» በማለት ነበር ቤተ መንግሥቱን የለቀቁት፤ በኋላ ግን በእስር በቆዩበት ጊዚያት አገራቸው በምን አይነት ሰዎች እጅ እንደወደቀች ሲገነዘቡ ያ ሁሉ ከውጪ ጠላት ያደረጉት ትንቅንቅ፣ ለነጻነት ያደረጉት ተጋድሎ፣ ለሥልጣኔ ያደረጉት ጥረት፣ … እንዲህ ከንቱ ሲቀር አገሪቱ አስከፊ አደጋ ውስጥ እንደምትወድቅ ገብቷቸው ነበር ያለቀሱት። ለሕዝቡ ነበር ያነቡት።
አብዮታዊው መሪ መንግሥቱ ኃ/ማርያምም አስራ ሰባት ዓመታት ሳይተኙ፣ ሳይስቁ፣ አብዮታዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት፣ ዳር ድንበርዋን ለመጠበቅ፣ አገራቸው ተቆርሳ እንዳትወሰድ ከውስጥና ከውጪ ጠላት ለመከላከል ያደራጁት ያነቁት የሚተማመኑበት ጦር ፈርሶ እንደጎርፍ መንገዱን ሞልቱ ሲሄድ በአንቦ አቅጣጫ በሚገኝ አንድ ተራራ አናት ላይ ወጥተው ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለው ጦሩን ቁልቁል እያዩ ነበር ያለቀሱት፤ የሀገራቸው መጪ ዕድል አስከፊ ውድቀት እየታያቸው ነበር ያነቡት።
የሁሉም እንባ አላግባብ የፈሰሰ አልነበረም፤ ከመቆርቆር ከመቆጨት ምንም ማድረግ ካለመቻል የመነጨ ነበር። ይህ ደግሞ ምስክር የሚያስፈልገው፣ ማስረጃ የሚጎተትለት አይደለም፤ ጠቀመም ጎዳ የሁሉንም ታሪክ ሥራቸው በይፋ ያስረዳል። ለዚህ ጽሁፍ ያነሳሳኝ ኃይለማርያም ዓይን ስር ቁርዝዝ ብላ የወረደችው እንባ ናት። እንደውነቱ ጉንጫቸውን ሰንጥቃ ባትወርድም ያው እንባ ናትና እንደመሪ እንባ ልቆጥራት አስቤ ነበር፤ ግን እሷንስ ቢሆን ለምን አለቀሷት ብዬ ሳስብ የባሰ ንድድ አለኝ። እንደዚች አይነት የምታቅለሸልሽ አስቀያሚ እንባ ዕድሜዬን ሙሉ አይቼ አላውቅም። ለነገሩ እንኳን እንባቸው ሳቃቸውንም ያምራል ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም።
ዋናው ነገር ግን ይሄ አይደለም ለምን አለቀሱ ነው? ጥያቄው እንዴ! እንዴት አያለቅሱም በደቡብ አፍሪካ የተቃጠሉት ወገኖቻቸው አይደሉም እንዴ! ምን ማለትህ ነው። ባህር እየሰመጠ የሚሞተው ወጣት አያሳዝናቸውም እንዴ! ሰሞኑንስ እንደመስዋዕት በግ የታረዱት ወገኖቻቸው አይደሉም እንዴ! ሌላም ሌላም ልትሉ ትችሉ ይሆናል። የኃይለማርያም ለቅሶ ግን በዚህ አይደለም፤ ግምገማ በሚባል ፈሊጥ እየታዘዙ ከሚመሩባት ወንበር ተሽቀንጥረው እንደሚወረወሩ የሚያመላክት ዘለፋና ስድብ ስለደረሰባቸው ነው። ሌሎችን በዚችው ጥበብ እሳቸውም አባረው ያውቃሉ፤ ያቺ ቀን ለሳቸውም በጣም ቅርብ መሆንዋ ስለተሰማቸው ነበር ያነቡት (ማንባት እንኳን አትባልም)። ብዙዎች ለምን ደም አያለቅሱም ይበላቸው ከማለት ውጪ ከንፈር ይመጡላቸዋል ብዬ አላስብም፤ እራሳቸውም ቢሆኑ ጥርስ ከማፋጨትና ጸጉር ከመንጨት በቀር የሚሉት ይኖራል ተብሎ አይገመትም።
የእንባን ነገር ካነሳሁ አይቀር ጠ/ሚንስትሩን ምክር መክሬ ልሰናበት። ጠ/ሚንስትር ሆይ! ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በይቅርታም ሆነ ነገርን አለዝበው የመውረጃዎን ጊዜን አበላሽተዋል። ካሁን በኋላም ተሰድጄ እኖራለሁም ብለው አያስቡ። ያንንም አጥተዋል። የጠቅላይ ሚንስትርነቱንም ሥልጣን ይዘው መቀመጥ ካሁን በኋላ የህልም እንጀራ ነው። የሥራ ጊዜዎን ወይም መጠቀሚያነትዎን በአግባቡ ጨርሰዋል። ማድረግ የሚገባዎ ቢኖር ረዥም የማልቀሻ ጊዜ ስለሚጠብቅዎ እንባ ቁጠባ በማድረግ ዓይንዎትን መጠበቅ ብቻ ነው። ኖሮም አላማረበት «ከሞጨሞጨ ዓይን የጠፋ ይሻላል» ካሉም የራስዎ ጉዳይ ግምገማውን ያቅልልዎ።
ወለላዬ 

No comments:

Post a Comment