የምርጫው ማግስት መቼ ነው ? ( ሄኖክ የሺጥላ )
ታሪክ በሕይወት ዑደትና ሂደት ፣ ድርጊት ና በጊዜ ቀመር ተለክቶ ፣ ነገ ፣ ትናንት ፣ አምና ፣ ካቻምና ፣ የዛሬ ወር ፣ የዛሬ ዓመት ይባላል ። ይህም ታሪክ ድርጊቱ የሆነበትን ወቅት ከመለካት አልፎ ፣ የዘመኑን እድገት ፣ ፍልስፍና ፣ የህዝቦች ስነ ልቦናና ፣ አኗኗር አስረጅ አማዳዊ እና እምርታዊ ፣ ስለ ያኔው በመንገር ዛሬን ምን እንደሚመስል እና መምሰል እናዳለበት መሪ መንገድ ይሆናል ።
ለምሳሌ የአድዋ ድል ታሪክነቱ ትልቅነትን የተላበሰው ፣ ድሉ ቀን ስለነበረው ነው ። ድሉ ስል እና ብልህ አርበኞች ስለነበሩት ነው ። ድሉን የሚመሰክሩ ቋሚ ምስክራን ስለነበሩን ነው ። ድሉ የህዝብ ስለነበረ ነው ። ድሉ በነጻነት እና በባርነት መሃከል ስለተደረገው ትግል ጀግንነት ምስክር ስለነበረ ነው ። የአደዋ ድል ቀን አለው ። የድሉ ማግስትም ይታወቃል ።
የአድዋ ድል መጽሐፍ ተጽፎለታል ፣ የውጭ ሀገር ጸሐፊያን ( እነ አሉላ ፓንክረስት ስለ እኔ አሉላ ገጥመዋል ፣ እነ ጆሴፍ ሬሞንድ ስለ እቴጌ ጣይቱ ጽፈዋል ) የሀገራችን ገጣምያን እና ጸሐፊያን ( እነ ጳውሎስ ኞኞ የማይነጥፍ ብእራቸው ቃላቱን እስኪያጥጥ ተርከውለታል ፣ እነ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ተቀኝተውለታል ፣ ብላቴናው ቴዎድሮስ ካሳሁን የጥበብ ጥንፋሱን እፍ ብሎለታል ፣ እነ ገብረክርስቶስ ደስታ ፣ እነ ፣ እነ ከበደ ሚካዔል ፣ እነ መንግሱ ለማ ፣ ራሳቸው አለቃ ለማ ፣ እነ ሐዲስ አለማየሁ ፣ እና ሌሎቹም ስለ አድዋ ድል መስክረዋል ፣ አመስግነዋል ፣ ዘምረዋል ) ። ለምን አድዋ ድል ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ድሉ ቀን ስላለው ፣ ድሉ ማግስት ስላለው ፣ ድሉ ከድልነት ባሻገር ለታሪክ በረከት ስለነበረ ፣ ድሉ ድል ስለነበረ ።