Translate

Friday, June 10, 2016

በእነ አቶ በቀለ ገርባ ላይ የቀረበውን ክስ የፌዴራል ፍርድ ቤት እንዳያይ ተቃውሞ ቀረበ

የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ በቀለ ገርባ (22 ተከሳሾች) የክስ ሒደት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት ‹‹የማየት ሥልጣን የለውም›› ሲሉ የመጀመርያ የክስ መቃወሚያቸውን ክሱ ለተከፈተበት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቀረቡ፡፡

ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አቶ አመሐ መኰንንና አቶ አብዱልጀባር ሁሴን አማካይነት ያቀረቡት መቃወሚያ እንደሚያስረዳው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) መሠረት ለፌዴራል የተሰጠ ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት፡፡ ለክልሎች የተሰጠ ሥልጣንም በፌዴራል መከበር አለበት፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በክልሎች ባለመቋቋማቸው፣ የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራሉን የመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ኖራቸው እንዲዳኙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡ ወይም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78(2) 80(2) እና 80(4) መደንገጉንም ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፣ በቅጽ 12 የሰ/መ/ቁ 54577 እና በቅጽ 17 የሰ/መ/ቁ/ 105962 በሰጠው ትርጉም፣ በክልሎች የሚነሱ የፌዴራል ጉዳዮችን የዳኝነት ሥልጣን፣ የክልል ፍርድ ቤቶች የሚያጡት ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ውክልናቸው ሲነሳ ብቻ መሆኑን መግለጹንም አስረድተዋል፡፡ ውክልናቸው እንዳልተነሳም አክለዋል፡፡ በመሆኑም ደንበኞቻቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጄኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላና ጉርሜሳ አያኖን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾችም ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በአዋጁ ቁጥር 25/88፣ 138/2001፣ 321/96 እና 141/2000 መሠረት፣ የነሱን ጉዳይ የማየት ሥልጣን ያለው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሆኑ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሥረ ነገር ሥልጣን እንደሌለው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ የክልሉ ቋሚ ነዋሪዎች በመሆናቸው ክልሉ የተለየ ጥቅም ስለሚኖረው ክሳቸው በክልሉ ፍርድ ቤት መታየት እንደሚገባውና ይኼም ፌዴራሊዝምን በተግባር የሚተረጎምና የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተከሳሾቹ በራሳቸው ቋንቋ የመዳኘት ሕገ መንግሥታዊ መብትንም እንደሚያረጋገጥና የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 99 እና ተከታዬቹን በአግባቡ ለመተርጎም እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡
ሌላው ተከሳሾቹ በጠበቆቹ አማካይነት ያቀረቡት ተቃውሞ የቀረበባቸው ክስ ጭብጥ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፣ ተከሳሾቹ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የማስተር ፕላን እንዲሁም የኦሮሚያ ከተሞች የዕድገት ፕላን፣ የኦሮሚያን ሕዝብ ቋንቋና ባህል የሚያጠፋ፣ የኦሮሞ ሕዝብን ከመሬቱ የሚያፈናቅል መሆኑን በመግለጽ፣ በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች ሕዝቡን በመቀስቀስ ለአመጽ በመቀስቀስና በማስነሳት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን እንደሚገልጽ ተናግረዋል፡፡
ማስተር ፕላኑ እንዳይፀድቅ አቤቱታ ማቅረብ ወንጀል አለመሆኑን የገለጹት ተከሳሾቹ፣ እንደ መብት እንደሚቆጠር ወይም መብት እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ላይ መደንገጉን ጠቁመዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 43(2) ዜጎች እነሱን በሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ የመሳተፍና የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ጠቁመው፣ ተከሳሾቹ የኦፌኮ አመራርና የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አባላት እንደመሆናቸው ለሚታገሉለት ማኅበረሰብ ይበጃል ያሉትን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
የመንግሥትን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን የመቃወምና የመተቸት ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የዴሞክራሲ መብት እንጂ፣ በምንም መልኩ የሕግ ድንጋጌ የሚጥስና የወንጀል ተግባር ሊሆን እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ ተከሳሾቹ ፈጽመዋል የተባው ድርጊት የወንጀል ኃላፊነት የሚያስከትል፣ ሕገወጥነቱ በሕግ ያልተደነገገና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገለት መብት መሆኑን ጠቁመው፣ ሊያስከስሳቸው ስለማይገባ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብታቸው አመልክተዋል፡፡
ተላልፋችኋል የተባሉት የፀር ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 መግቢያ (Preamble) ከሚገልጸው አንፃር ክሱ ያልታየ መሆኑን፣ በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረው ረብሻና ቀውስ የመልካም አስተዳዳር ዕጦት መሆኑ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በአገሪቱ ሕግ አውጪ ተቋም ፊት ቀርበው የመሰከሩበትና የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የሌለበት መሆኑን የተናገሩት፣ የክልሉ መንግሥታትና አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ያረጋገጡበትና የመሰከሩበት ሁኔታ ስላለ ፍርድ ቤቱ የሕግ ግምት እንዲወስድና ክሱ አግባብነት የሌለው መሆኑን አውቆ ወይም መከሰስም ካለበት የፖለቲካ ድርጀቱ (ኦፌኮ) እንጂ አመራሮቹ አለመሆናቸው፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 40(1) ላይ መደንገጉን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ በነፃ እንዲያሰናብታቸው አመልክተዋል፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቆች ሰፋ ያለ የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የዓቃቤ ሕግን መልስ ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡

No comments:

Post a Comment