Translate

Friday, April 8, 2016

ምን ዓይነት ድል? (ዶ/ር ታደሰ ብሩ የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር)

ምን ዓይነት ድል?
image
ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት “የተገኘው ሰ,ላምና እድገት የሚንድ የአመራር ዘዴ በአስቸኳይ ይታረም” በሚለው ጽሁፉ ውስጥ እንደዋዛ ጣል ያደረጋት በህወሓቶች የምትዘወተር “ኢሕአዴግ ከሞት አፋፍ ተነስቶ፣ አንሰራርቶ ለድል የመብቃት ባህል አለው” የምትል ዓረፍተ ነገር አለች። ይህ አባባል በተለያዩ አቀራረቦች በጣም ብዙ ጊዜ ሰምቸዋለሁ።  ላተኩር የምፈልገው “ለድል መብቃት” የምትለዋ ሀረግ ላይ ነው። ለእንዴት ዓይነት ድል?
በነገራችን ላይ የሜ/ጄ አበበ ጽሁፍ ህወሓት ላይ ጥንቃቄ የበዛበት ልስላሴ ቢያሳይም በአጠቃላይ ሲታይ በጣም ጥሩና የተኙትን አንቂ ደወል ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ይህንን ደወል የሚሰሙ ጆሮዎች ኢህአዴግ የሚባለው ስብስብ ውስጥ ያሉ ግን አይመስለኝም። ወደ ጉዳዬ ልመለስ።

ሜ/ጄ አበበ “ኢሕአዴግ ከሞት አፋፍ ተነስቶ፣ አንሰራርቶ ለድል የመብቃት ባህል አለው” ከማለቱ በፊት “ቁርጠኝነትና ጥበብ በተሞላበት መንገድ ከተሠራ አሁንም የማይቻል ነገር የለም” በማለት ቅድመ ሁኔታ የሚመስል ነገር በማስቀመጡ በዚህ ጉዳይ ላይ እኔ ከሰማኋቸው የህወሓት ሰዎች ሁሉ በላይ ትሁት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ሌሎች የህወሓት ሹሞችና ምንዝሮች ይህኑ ዓይነት ዓረፍተ ነገር የሚናገሩት መረን በለቀቀ ትዕቢትና ጉራ ነው። በምርጫ 97 ማግስት አንድ “እንዳስጠነቅቅህ ከበላይ ታዝዤ ነው” ያለኝ ሰላይ “ኢህአዴግ ይወድቃል ብለህ በህልምህ አታስብ፤ አፈር ልሶ ይነሳል” ብሎኝ ነበር። በሌላ ጊዜ ተማሪዬ የነበረ የህወሓት ሹም “ህወሓት ከሞት ተነስቶ ያሸንፋል” ሲል ተጎረነነብኝ። “ህወሓትን አንገቱን እንኳን ብትቀጠቅጠው አይሞትም” ያለኝ የህወሓት ሰውም አለ። ሁሉም ሙታ ስለምትነሳዋ የተረት ወፍ ፊኒክስ ማስታወስ ይቀናቸዋል። በአጠቃላይ የህወሓት ሰዎች ጉራ አናታቸው ላይ ወጥቷል፤ የመለስ ዜናዊ “የሲኒ ውስጥ ማዕበል” ምሳሌም የዚሁ ተቀጥላ ነው።
ለመሆኑ ህወሓቶችን እንዲህ ትዕቢተኛ ያደረጋቸው ምንድነው?
ለዚህ ሁሉ ጉራ የልብ ልብ የሰጧቸው ሶስት ዋና ዋና ክስተቶች ይመስሉኛል። 1ኛ) “ህንፍሽፍሽ” እያሉ በሚጠሩት ውስጠ ፓርቲ ፍትጊያ በግደይ ዘርዓጽንና አረጋዊ በርሄን መባረርና በስብሀት ነጋና መለስ ዜናዊ ገኖ መውጣት መጠናቀቁ ድል አድርገው ስለሚወስዱት፤ 2ኛ) ስልጣን ከያዙ በኋላ በ1994 በደረሰው መሰንጠቅ በመለስ ዜናዊ የሚመራው “ተንበርካኪው የቤተመንግሥት ቡድን” አሸንፎ እነ ስየን፣ ፃድቃንን፣ ገብሩን፣ አረጋሽን፣ ሰለሞንን .. ወዘተ አራግፎ መሄዱ ድል አድርገው ስለሚወስዱት (ሜ/ጄ አበበም በዚህ ወቅት ከተናጡት አንዱ ሆኖ እያለ መጎረን መቀጠሉ ራሱን የቻለ ምፀት ነው) እና 3ኛ) የምርጫ 97 ማዕበልን “ፀጥ አሰኘን” ብለው የሚያምኑ መሆኑ ነው።
ህወሓት፣ ክፋት እና ክፋት ሲጣሉ የበለጠ ክፉ የሆነው ወገን የሚያሸንፍበት አስገራሚ ድርጅት ነው። የበለጠ ክፉ የሆነው ወገን  ማሸነፍን ነው ድል እያሉ የሚመፃደቁብን። እነሱ “ድል” እያሉ የሚመፃደቁባቸው ክስተቶች በእርግጥ ድሎች ናቸው ወይስ ሽንፈቶች?
የናዚ  ፓርቲ መመረጥና የሂትለር ወደ ስልጣን መምጣት ለጀርመን ድል ነበር ወይስ ውድቀት? ለዚህ ጥያቄ ለጀርመን ድል ነበር የሚል የሚኖር አይመስለኝም። ሌላ ጥያቄ ልጠይቅ። የናዚ ፓርቲ መመረጥና የሂትለር ወደ ስልጣን መምጣት ለናዚ ፓርቲ ድል ነበር ወይስ ውድቀት? ይህ ጥያቄ እንደላይኛው ቀላል አይደለም። የናዚ ፓርቲ አባላት በወቅቱ ድል ነው ብለው ፈንጥዘዋል፤ ጨፍረዋል። ከሁለኛው ዓለም ጦርነት ማለቅ በኋላ ግን እንደዚያ አይሉም፤ ብዙዎች የሉም፤ ጠፍተዋል።  ያ ድል ያሉት ነገር መጥፊያቸው ሆኗል።
እንደ ናዚ ፓርቲ ሁሉ፣ ህወሓቶች ዛሬ “ድል” እያሉ የሚጠሯቸው ነገሮች እውነተኛ ድሎች ሳይሆኑ ሽንፈቶች መሆናቸው እና ዛሬ የሚያወድሷቸው “ድሎች” መጥፊያቸው እንደሚሆኑ ማየት ተስኗቸዋል።

No comments:

Post a Comment