አገቱኒ የምትለውን የግዕዝ ቃል በመጀመሪያ በመዝሙረ ዳዊት ላይ ነው ያየሁዋት ፣ መዝሙር (3)፣ እንዲህ ነበር ሰንጠር ብላ የገባችው ።
ትርጉሙም ….
እግዚያብሔር አንቅቶኛልና እና ነቃሁ
ከአእላፍ ሕዝብ ከከበቡኝም አልፈራም ።
ከአእላፍ ሕዝብ ከከበቡኝም አልፈራም ።
ስለዚህ ( አገቱኒ =ከከበቡኝም ) ማለት ይሆናል ። መያዝም አቻ ቃል ነው ።
ከዚያ ወዲያ ታዋቂው ቦጠሊቀኛ ፣ መምህር ፣ ተመራማሪ ፣ እኔ ደሞ ነብሴ እስኪጠፋ የምወዳቸው ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ለ መጽሃፋቸው አርዕስት አድርገውት ። አዎ አገቱኒ እና መታገት መንፈሳቸውን አንድ ያደረጉልኝ መሳይ መኮንንና ፋሲል የኔ-ዓለም ናቸው ። በመታገት !መስይና ፋሲል ግን ዛሬ መታገታቸውን አብስረዋል ።
መሳይና ፋሲልን ያገታቸው ግን አንዳርጋቸውን የመን ላይ አፍኖ የወሰደው ስርዓት ፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ቃሊቲ አፍኖ የገደለው ስርዓት ፣ እስክንድርን ፣ ተመስገንን ፣ አንዷለምን ፣ ር’ዮትን ፣ በቀለን ፣ ኦልባናን ፣ ናትናዔልን ፣ የሽዋስን እና ሌሎችንም በውሸት አዋጅ እና ክስ ያሰረው ስርዓት አይደለም ፣ ወይም ደሞ አምነውት የተጠጉት ፣ በብዙ ሀሜት እና ጥርጣሬ ስር ያለው የዔርትራ መንግስትም አይደለም ፣ ወይም ደሞ የሚኖሩባት አማሪካ እና አምስተርዳም መንግስታቶች በአሸባሪ ክስ ከሰዋቸው ፣ የመንቀሳቀስ መብታቸውን ነፍገው ይዘዋቸውም አይደልም ። ይልቁንስ መሳይንና ፋሲልን ያገተው ስለ ኢትዮጵያ የሚያስበው ህሊናቸው ፣ ጠንካራ ፍቅራቸው ፣ እምነታቸው ነው ። በፊትም ይሁን በጉዋሮ በር የሞት ቀጠና እየተባለ የሚጠራውን የኤርትራ አየር ሰንጥቀው እንዲገቡ ያደረጋቸው ለሀገራቸው ያላቸው እምነት ፣ በይበልጥም ለጋዜጠኝነት ( ለሙያው )ያላቸው ክብርም ነው ። እርግጥ ነው ጋዜጠኝነት አድርባይነት ፣ ጸጉርን ከምክሞ ፣ ባዝሊን ለድፎ ፣ በከረባት እና በኮት ተቆልፎ ፣ ጀምር ! ሲባል ውሸት ማውራት በሚጀምር ህሊና ቢስ ጋዜጠኞች ፣ ሆድ አምላኩ ፣ ምቾት ልኩ በበዙበት ፣ እንዲህ ባለ ሁናቴ ለፍቅር እና ለእውነት መገዛት ፣ ለማኝነት እና በማንነት መታገት መታደል ነው ።
ዘርኝነት በተንሰራፋበት ፣ እውነት እንደ ውሃ በተደፋበት ፣ ገዳይ በሚደነፋበት ፣ ተበዳይ አንገቱን በደፋበት ስርዓት ውስጥ ተለማማጭ ስብእና ፣ ተገዢ ልቦና የለኝም ብለው ህውሃትን ሌት ተቀን እየተታገሉት ፣ እየተቃወሙት ፣ እየተፋጩት ያሉ ጥቂቶች አይደሉም ። ያም ሆኑ መስዋትነት ልክ አለውና ፣ የመሳይና የሲሳይ መስዋትነት ፣ ከጥቂቶቹ ከባድ እና ፈታኝ ድፍረቶች እና ቆራጥነቶች ውስጥ አንዱ ነው ። ስለዚህም እነሱን ያገታቸው ፍቅር እኔንም በነካ እጁ ይዳብሰኝ ዘንድ ምኞቴ ነው ። በርቱ ! ከ ጨለማው ልንወጣ ነው ፣ የብርሃኑ ጫፍ ከ ዋሻው ጫፍ ላይ ይታየኛል ። ልናሸንፍ ነው ምክንያቱም ልቤ አልፈራም ፣ አልሸሽም ይለኛል ።
አምላኬ ያቺን ቀን ፣ ያቺን ቀን አምጣት ። ጠላቴን ” ያዝልቅልሽ እስከሚያልቅልሽ !” ብያታለሁና ። ያቺ ቀን ። ትታየኛለች ። እንደ ሰመመን ሳይሆን ፍንትው ብላ !
No comments:
Post a Comment