Translate

Thursday, January 29, 2015

ምርጫ ቦርድ፣ ቦርዱን ያከብራሉ ያላቸውን በእነ ትግዕስቱ አወሉ ለሚመራው አንድነት እና በእነ አቶ አበባው መሀሪ ለሚመራው መኢአድ ዕውቅና ሰጠ፡፡

ጥር ፳፩(ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እና የቦርዱ ጸሀፊና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ በጋራ ዛሬ ጥር 21 ከቀኑ 10፡00 ሰኣት በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በሰጡት መግለጫ በእነአቶ በላይ ፍቃዱ የሚመራው አንድነት፤ የፓርቲውን ደንብና የምርጫ አዋጁን የጣሱ ተግባራትን እንደሚያከናውን፣ ፓርቲው ያካሄደውን ጉባዔ ለሰባት ወራት ሳያሳውቀው መቆየቱን፣ የቀድሞ ፕሬዚደንት ከሃላፊነታቸው የተነሱት ሕጉን ጠብቆ አለመሆኑን፣ ፓርቲው ለሁለት ሲከፈል ቦርዱ ልዩነታቸውን በጋራ ለጠቅላላ ጉባዔ አቅርበው እንዲያስወስኑ ቢጠይቅም ፈቃደኛ ሆነው አለመገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በአንጻሩ የአንድነት ፓርቲን ሕግና ደንብ አክብረው ተንቀሳቅሰዋል፣ ጠቅላላ ጉባዔ አካሄደዋል  ላላቸው ለአቶ ትግእስቱ አወል ቡድን ዕውቅና እንዲሰጥ ቦርዱ በዛሬው እለት ባካሄደው ስብሰባ በሙሉ ድምጽ ወስኖል ብለዋል፡፡ ቦርዱ በመግለጫው፣ የፓርቲውን ህልውና ለማስቀጠልና ወደ ምርጫ የሚገባ ፓርቲ ስለሚያስፈልግ ፣ የእነ አቶ በላይ በፈቃዱ ቡድን በርካታ የህግ ጥሰቶችን የፈጸመና እየፈጸመ የሚገኝ በመሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ የእነ አቶ ትእግስቱ አወሉ ቡድን ህግን በማክበር ለመንቀሳቀስ ጥረት እያደረገ ያለ በመሆኑ፣ ይህንን ፓርቲ ለመምራት ቦርዱ እውቅና ሰጥቷል ብሎአል። እነ አቶ ትእግስቱ አወሉ አንድነትን በመምራት ወደ ምርጫው እንዲገቡ ፈቃድ መስጠቱን ቦርዱ አስታውቋል መኢአድንም በተመለከተ በአቶ ማሙሸት የሚመራውን ቡድን  በ2003 ዓ.ም ከፓርቲው አባልነት የተሰረዙ፣የ አባልነት መዋጮ ያልከፈሉ መሆናቸውን፣ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያካሂዱም የቦርዱ ተወካይ ያልተገኘ ነበር በሚል ለቀድሞ ፕሬዚደንት ለአቶ አበባው መሐሪ ዕውቅና ይገባቸዋል ሲል ወስኖአል፡፡ መኢአድን በተመለከተ ደግሞ የእነ አቶ ማሙሸት አማረ ቡድን የምርጫ ህጉን የጣሱ በመሆኑ እውቅና አይገባቸውም በማለት አቶ አበባው መሃሪ የመኢአድ መሪ ሆነው በምርጫው እንዲሳተፉ ወስኗል።

የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኛው አቶ መለስካቸው አምሃ ” የእነ አቶ ትእግስቱ አወሉ ቡድን በአብዛኛው አባላት ለመመረጣቸው ማስረጃ አላችሁን? መራጮችስ የአንድነት አባላት መሆናቸው በምን ይታወቃል?” በሚል ላቀረበው ጥያቄ፣ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ፕ/ር መርጋ በቃና ” ሁለቱን ቡድኖች ግድፈቶች እንዳሉባቸውና የማመዛዘን ስራ መሰራቱን እንዲሁም ለቦርዱ ታዛዥ ለሆነው አካል መወሰኑን ተናግረዋል ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ የቀረበላቸው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃለፊ አቶ አስራት አብርሃ፣ ድርጅቱን ለማፍረስ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሰጠቱን ገልጸው፣ ስራ አስፈጻሚውና ምክር ቤቱ  ተሰብስቦ ውሳኔ እንደሚአሳልፍ አክለዋል ቀደም ሲል ቦርዱ ሁለቱ ፓርቲዎች ችግሮቻቸውን በጋራ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂደው እንዲፈቱ መመሪያ የሰጠ ሲሆን ይህ ባለመፈጸሙ አሁንም በድጋሚ በጋራ ስብሰባውን እንዲያካሂዱ የሁለት ሳምንት ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በጋራ ስብሰባው ባልተካሄደበት ሁኔታ ለአንድ ወገን ዕውቅና መስጠቱ ውሳኔው ፖለቲካዊ እንደሚያደርገው ጉዳን የተከታተሉ ወገኖች እየገለጹ ነው፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ከመግለጫው በሁዋላ አንድ ጥያቄ ብቻ ተቀብለው ሌላ አልቀበልም በማለት ተቻኩለው አዳራሹን ለቀው ወጥተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ መግለጫ በሚሰጥበት ወቅት የመደናገጥና ያለመረጋጋት ስሜት ፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር፡፡ አንድነት ፓርቲ የተሰጣቸው የእነ ትግስቱ ቡድን፣ እንዲሁም መኢአድ የተሰጣቸው የእነ አበባው መሃሪ ቡድን በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ፓርቲዎች ወክሎ ጽ/ቤት ከሚገኘው የፓርቲ አመራር ጋር አለመግባባት በመፍጠራቸው በውጭ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment