ልክ ከምሽቱ አራት ሰዓት …!! የሰፈራችን ታዋቂ ሰካራም ጋሽ አዳሙ እየዘፈነ እየፎከረ እየተሳደበ እና እየተራገመ …. የምሽት ጭርታ የተጫጫናት ሰፈራችንን የዝምታ ድባብ ገፈፈው ….‹‹ እ ያ ን ዳ ን ድ ሽ ›› ሲል ገና
‹‹ጋሽ አዳሙ መጣ ..›› ተባብለን የቴሌቪዥን ድምፅ ለመቀነስ ተራወጥን
‹‹ኧረ ቀስ ቡናውን እንዳትደፉት›› እየተባልን ….በቃ ጋሽ አዳሙን ለመስማት መንደርተኛው በሙሉ ማታ ማታ በየቤቱ ሁኖ ጆሮውን ያቆማል …ጋሽ አዳሙም እንደሚሰማ ያውቀዋል መሰል ድምፅ እስከምንቀንስ ጠብቆ ….እያንዳንድሽ …..ብሎ ይቀጥላል …. አይዛነፍም ሰዓቱ ልክ አራት ሰዓት ላይ ነው ሰፈራችን የሚደርሰው !
‹‹ጋሽ አዳሙ መጣ ..›› ተባብለን የቴሌቪዥን ድምፅ ለመቀነስ ተራወጥን
‹‹ኧረ ቀስ ቡናውን እንዳትደፉት›› እየተባልን ….በቃ ጋሽ አዳሙን ለመስማት መንደርተኛው በሙሉ ማታ ማታ በየቤቱ ሁኖ ጆሮውን ያቆማል …ጋሽ አዳሙም እንደሚሰማ ያውቀዋል መሰል ድምፅ እስከምንቀንስ ጠብቆ ….እያንዳንድሽ …..ብሎ ይቀጥላል …. አይዛነፍም ሰዓቱ ልክ አራት ሰዓት ላይ ነው ሰፈራችን የሚደርሰው !
‹‹ እኔ የምለው …ይሄ ሰፈር በጊዜ መብራቱን አጠፋፍቶ ለሽሽ የሚለው ምን ነክቶት ነው ….ወይስ የሌላውም ሰፈር እንቅልፍ ወደዚህ ሰፈር ተግዟል ! …. እንቅልፍ ብቻ …. ደህና ህልም እንኳን አታልሙ እንቅልፍ ታባክናላችሁ …. ሃሃሃሃሃ ....የማላውቅ መሰለሽ እያንዳድሽ ጋሽ ተሸ ቤት ህልም ልታስፈች ስትመጭ ‹‹ ሱዳን ስሄድ አየሁ … ዱባይ ስሄድ አየሁ ›› አሁን እስቲ ማን ይሙት ሱዳንና ዱባይ እንኳን በህልም በዜና ስማቸው ሊነሳ ይገባ ነበር ….ህልማችን ከጊዜ ወደጊዜ ወርዷል …. የህልም ግሽበት ! አሁን በዚህ በሚመጣው ምርጫ ‹‹ህዝቡን ደህና ነገር እንዲያልም አደርጋለሁ ›› የሚል ፓርቲ ካለ እመርጣለሁ ሃሃሃሃሃሃ! …
....ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ …ከዶሮ የተሸለ ህልም የሚያልም አንድ እንኳን የሰፈሬ ሰው ልጣ ...ወይኔ አዳሙ !……….. ዶሮ ለሚመጣው ፋሲካ ስለሚሳልላት ቢላ እንኳ ተስቷት አታልም ሁሌ ጥሬ …አራጆቿም ቢሆኑ ጥሬ እየረጩ እስከፋሲካ ሲያከርሟት ፍቅር እየመሰላት ታስካካለች ….››
ቡፍ እያልን እንሳሳቃለን !
‹‹ እያንዳንድሽ ከዛሬ ጀምሮ … ይሄን መንገድ ‹አዳሙ ጎዳና› ብለሽ በስሜ ካልሰየምሽ እኔን አያርገኝ … መስከር ነው የማቆምልሽ … አዎ ስካሬን ድንገት ነው ቀጥ አድርጌ የማቆምልሽ …. የእያንዳንድሽን ሹክሹክታ ማን ጩኾ እንደሚናገርልሽ አያለሁ ! እንኳን በእኔ ስም በማንም ፊታውራሪ ስም መንገድ ስትሰይሚ ኑረሽ የለ …. ፊታውራሪ ማንትስ ምን ሰሩ ....ጥሊያንን አባረሩ …ከዛሰ … ህዝቡ ራሱ እየፈለሰ ጥሊያን መሄድ ጀመረ ! አሁን የሚያስፈልገን መጭውን የሚባርር ሳይሆን ሂያጁን የሚመልስ ነው …ይቅርታ መመለስ ስል ደግሞ ጠመንጃ እና ቆመጥ ይዛችሁ ድንበር ላይ እንዳትቆሙ ….ምን ልል መሰላችሁ … ምንስ ባልል ግድ አለኝ ! አዳሙ ዘ ብሔረ አዲስ አበባ ››
እንስቃለን በየቤታችን ……..
‹‹ እኔኮ የሚገርመኝ ስደተኛ በዛ …. አረብ አገር የሚሰደደው ውሮፓ አሜሪካ የሚጎርፈውን ማለቴ አይደለም …. እዚሁ ከክፍለ ሃገር ወደአዲስ አበባ የሚጎርፈውን ማለቴ ነው … የትም ክፍለ ሃገር ብትሄዱ ነዋሪው አዲስ አበባ መኖርን እንደተስፋ ምድር የሚያልምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል … ይገርማልኮ
‹‹እሸቱን ከጓሮ ወተቱን ከማጀት ›› የሚባልለት የገጠሩ ልማታዊ ገበሬ እንኳን ወተቱንም እሸቱንም ጣጥሎት የአዲስ አበባ ድራፍትና ቋን ጣ ፍርፍር በአይኑ ውል ይልበታል ….. እስቲ ተመልከቱና አዳሙ ዋሸ በሉኝ …የትም ብትሄዱ ነጋዴው ተወልዶ ያደገበትን ቃየ እየተዎ አዲስ አበባ መርካቶ ክተት የተጠራ ይመስል ይታጎራል …አዲስ አበባ ልትፈነዳ ደረሰች …. ኧረ ጎበዝ እርሻና ማረሻቸውን ተሸክመው ስላልመጡ እንጅ አዲሳባ እኮ በገጠሩ ሰው ተሞልታለች ….. ለምን መጡብን ብየ አይደለም … ከቃያቸው ምን ጉድ አባረራቸው ብየ ገርሞኝ እንጅ …አዲሳባ እንደሆነች የገጠሩን ሰው የምታውቀው በድራማ ነው ዘበኛ ሰራተኛ ሁሎ ሲላፋ … እስቲ ታዘቡኝ በድራማ ወላ በፊልም የገጠር ሰው ከዘበኝነትና ከቤት ሰራተኝነት ሌላ የረባ ቁም ነገር ሲሰራ ካያችሁ …ሰው ድራማ ለመሆን ቃየውን ትቶ ይፈልሳል ….
እንግዲህ የከተሞች እድገት ማለት ምንድን ነው … እኛ ከአገር የሚወጣውን እያየን ስደት ቅብርጥስ ስንል እዚሁ አፍንጫችን ስር መሬቱን እየሸጠ አዲስ አበባ ቀልጦ የሚቀረው የክፍለ ሃገር ሰው ውጦን ሊያርፍ ነው ….መብቱ ነው ይምጣ ! ግን ህዝቡ ለምን ቃየውን ጠላ …. ነጋዴው ለምን ወደአዲስ አበባ ብቻ መግባት ህልሙ ሆነ … አሁን ነው ነቃ ማለት …እንዴት ነው ክፍለ ሃገር ስርዓቱ …እንዴት ነው ክፍለ ሃገር አስተዳደሩ ….ሰው መቸስ ከመሬት ተነስቶ የትውልድ ቀየውን አይለቅ ….
ሰው መቸስ ውብ ሜዳውን ትቶ ደረቅ የመኪና መንገድ ላይ መኳተን ካለነገሩ አያምረው …ወይስ እነዛ ውብ የተፈጥሮ ተራሮችን በመስተዋት ክምር ተክቶ መኖር ብርቅ ሆነበት …. እድገቱ ያመጣው ፍልሰት ነው ሃሃሃሃ ታዲያ ይሄ እድገት አዲስ አበባን ወደየት ያፍልሳት ……እንዲህ ክፍለ ሃገሩ ሁሉ ነጋዴውን ገበሬውን እየሸኘ ቀፎው ቀረና ኢትዮጲያ ጥቅልል ብላ አዲስ አበባ ሁና አረፈች ! አይ ጣይቱ አይ ሚኒሊክ ምናይነት ነፍስን የሚስብ ማግኔት ብትቀብሩባት ነው አዲስ አበባችሁ እንዲህ አቅልጣ የምታስቀረው …….
ለማንኛውም አማረርንም አላማረርንም …. ታመስንም አልታመስንም እንኖራለን ! ለመሆኑ … ውድ ጎረቤቶቸ የምርጫ ካርድ አውጥታችኋል ? …. በጣም ጥሩ …አረጋሽ ጥሩ ሰርታለች ማለት ነው …. አሁን አረጋሽ የቀራት አንዱ ህንፃ ላይ ቆማ በስናይፐር አነጣጥራ በመተኮስ በየኪሳችን ካርድ ማስገባት ነው ሃሃሃሃሃሃ ››
አብረን እንስቃለን አረጋሽ የቀበሊያችን ምክትል ሊቀመንበር ናት ! አዳሙ በስካሩ ሁሉ የአረጋሽን ስም ካላነሳ አይገባም !
‹‹ ምርጫ ጥሩ ነው …. እውነቴን ነው ምርጫ ጥሩ ነው …..ጥሎብን እኛ ኢትዮጲያዊያን የተሰጠንን እንጅ የመረጥነውን ባናገኝም …ምርጫ ጥሩ ነው …. አሁን አምስተኛ ምርጫችን አይደል ?….አምስት ሲባዛ በአምስት ሃያ አምስት ….ሩብ ክፍለ ዘመን መረጥን ….ሃሃሃሃ ሩብ ክፍለዘመን ስንመርጥ ስንመርጥ ስንመርጥ ….ይሁን ! ህዝቡ ከዳር እስከዳር በነቂስ ወጥቶ የሚበሳጭበት ድራማ ምርጫ ይባላል ! ሃሃሃ
‹‹አይዞህ ወገኔ ውሃ እንደልብህ እናስገባልሃለን ምረጠን ብቻ ›› …..ይሉናል ……ሩብ ክፍለ ዘመን ቃል የገቡልን ውሃ ቢሳካላቸው እስካሁን አገራችን ላይ ውቂያኖስ ይፈጠር ነበር …ምን ውቂያኖስ ብቻ የባህር በር ይፈጠር ነበር ….ግን ይሄው ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ ቧንቧውን ስንከፍተው እሽሽሽሽሽሽ ብቻ ….ሬዲዮውን ስንከፍተው ግን ‹ ሰባ ስምንት በመቶ ነዋሪው ውሃ ተዳርሷል ተትረፍርፎታል ›› ይለናል …..ጎበዝ ውሃ በሬዲዮ እየተለቀቀ የሬዲዮው እሽሽታ በቧንቧ እየመጣልን ነው …መተካካት ….ሃሃሃሃ! ቢሆንም ተደምረን ተቀንሰን ተባዝተንና ተካፍለን ያው አገር ነን ከነችግራችን !! አገርነና በቃ …. ምን ነበር ያለው ደራሲው ስብሃት …..
‹‹ጥሩ ነው ወጣት መሆን ኑሮ ቢመርህ ጦማሪ ትሆናለህ …ሃሃሃሃሃ ›› ጥሩ ነው አገር መሆን እንበላ እኛም ……..
ጋሽ አዳሙ እያወራ በጨለማው ድምፁ እየቀነሰ ….እየቀነሰ ….. ወደቤቱ ይጓዛል ጥሩ ነው አገር መሆን እያለ …….ዜማ ባለው አነጋገር
‹‹ ጥሩ ነው አገር መሆን ……. ህጉ ባይጥምህም ህገ መንግስት ይኖርሃል …. አማራጭ ባይኖርህም ምርጫ ይኖርሃል …ፍትህ ባይኖርህም ፍርድ ቤት ይኖርሃል …ጥሩ ነው አገር መሆን ! መልስ ባይኖርህም ጥያቄ ይኖርሃል ….የእውነት መረጃ ባይኖርህም የቴሌቪዥን ጣቢያ ይኖርሃል …ትራንስፖርት በመከራ ብታገኝም መንገድ ይኖርሃል …መብራት ባይኖርህም ግድብ ይኖርሃል ….
ጥሩ ነው አገር መሆን …… ስራ ባይኖርህም ከዩኒቨርስቲ ትመረቃለህ ….ሰላማዊ ሰልፍ ባይፈቀድልህም ሰልፍ በታኝ ወታደር ይኖርሃል … ሽብር ባይኖርህም በሽብር ከሳሽ ይኖርሃል …ጥሩ ነው አገር መሆን ! ውሃ ባይኖርህም የውሃ መስመሮች ይኖሩሃል ኔትዎርክ ባይኖርህም አትራፊ የቴሌፎን ኮርፖሬሽን ይኖርሃል ……ነፃ ፕሬስ ባይኖርህም ነፃነትህ መትረፍረፉን የሚያትቱ ጋዜጠኖች ይኖሩሃል …. .
ጥሩ ነው አገር መሆን …….መኖሪያ ቤት ባይኖርህም የደከረተ አሰልች ኑሮ ይኖርሃል... ዘፈን ባይኖርህም ዘፋኝ ይኖርሃል ….. ከራስህ ጋር ብትጣላም በመሃበር ትደራጃለህ …ኑሮ ቢመርህ ምንም አታመጣም …. ቢበዛ ከአገር መውጣት ነው …ጥርግ በል !! …ነፃነት ባይኖርም በነፃ የሚባዛ ህዝብ ሞልቷል አንተ ሄድክ አልሄድክ ….እና ጥሩ ነው አገር መሆን …..ካላመንክ አረጋሽን ጠይቃት ………ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ…
የጋሽ አዳሙ ድምፅ ይጠፋል …እኛም እተሳሳቅን ወደቴሌቪዥናችን እንመለሳለን ….. የተራዘመ ዜና ይጠብቅናል
‹‹ አገርን በማፈራረስና ህገ መንግስቱን በጉልበት ለመናድ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ………..›› ሌላ ቀጠሮ ስለተሰጣቸው እስረኞች ………..
No comments:
Post a Comment