Translate

Tuesday, October 28, 2014

የማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ግንባታ: እውነቱና አሉቧልታው!

ማኅበረ ቅዱሳንን የሚወቅሱ ወገኖች ማኅበረ ቅዱሳንን ከሚወቅሱበት ነጥብ አንዱ ማኅበሩ ያሰራው ባለ ሰባት ፎቅ ሕንጻ ነው:: ለመሆኑ ይሄ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ሕንጻ እንዴትና ለምን ተሰራ የሚለውን ጉዳይ ማየቱ ጠቃሚ ስለሆነ ባጭሩ እንመልከት::
mahbere kidusan building
ማኅበሩ ዋናው ማዕከል በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ አባላቱን ለማስተባበርና የሚሰሩ ስራዎችን ለማቀናጀት አዲስ አበባ ላይ ቢሮ ተከራየ:: የአዲስ አበባ ማዕከልም እንዲሁ:: ከዚህም ባሻገር ሥራቸውን ባግባቡ ያከናውኑ ዘንድ የማኅበሩ የልማት ተቋማትም የራሳቸውን ቢሮ መከራየት ነበረባቸው:: ለነዚህ ቢሮዎች ኪራይ በየወሩ የሚከፈለው ገንዘብ ግን እጅግ ብዙ ሆነ::
በዚህ ወቅት ነበር ” ለኪራይ ይሄን ያህል ወጭ ከምናወጣ ለምን የራሳችንን ጽ/ቤት አንሰራም የሚል ሀሳብ የተነሳው:: ይህ ምክረ ሀሳብ ለሚመለከታቸው አመራሮች ቀርቦ ስለታመነበት የጽሕፈት ቤት ግንባታው ሥራ ተጀመረ::

ይህም ኮሚቴ በሥሩ ሶስት ንኡሳን ኮሚቴዎች ነበሩት:: የመጀመርያው የምሕንድስና ክፍል ሲሆን በውስጡ በርካታ ኢንጂነሮችንና አርክቴክቶችን ያካተተ ነበር:: ሁለተኛው ንኡስ ኮሚቴ ደግሞ የገቢ አሰባሳቢ( fundraising)ኮሚቴ ሲሆን ሶስተኛው ኮሚቴ ሂሳብ ክፍል ነበር:: ማኅበሩ በውስጡ ያሉትን ኢንጆነሮች አርክቴክቶች የሂሳብ ባለሙያዎችና ሌሎች አስፈላጊ ሙያተኞችን ከአባላቱ በመመልመልና በነዚህ ዘርፎች ውስጥ በማደራጀት ሥራው ተጀመረ:: ከዚህ ውጭ ደግሞ የሕንጻ ሥራውን እንዲያማክሩ ታላላቅ ያገር ሽማግሌዎችና ባለሙያዎችን ያካተተ አማካሪ ዘርፍ ነበረው::
በርካታ ጉዳዮችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት : ማኅበሩ ተከራይቶት የነበረውን ቤት ለመግዛት ኮሜው ወሰነ:: ይሄ ቤት ንብረትነቱ የንቡረ ዕድ ድሜጥሮስ ነው:: እሳቸው ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት የሕንጻው ህጋዊ ባለቤቶች ህጋዊ ወራሾቻቸው የንቡረ ዕድ ዲሜጥሮስ ልጆች ስለነበሩ የግዥ ድርድሩ የተካሄደው ከህጋዊ ወራሽ ልጆቻቸው ጋር ነበር:: የቦታውን መሸጥ የሰሙ የሌሎች እምነት ተከታዮች ማኅበሩ ካቀረበው ዋጋ እጅግ የሚበልጥ ዋጋ በማቅረባቸው ስጋት ተፈጥሮ ነበር:: ነገር የንቡረ ዕድ ድሜጥሮስ ልጆች ” ለሌላ ሃይማኖት መስኪድነት ብንሸጠው ያባታችን አጽም ይወቅሰናል ስለዚህ በዋጋ ብንዳም የምንሸጠው ለማኅበሩ ነው” ብለው በመወሰናቸውና ቤተሰቦቻቸውም በመስማማታቸው ቦታውን በአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር ተገዛ::
ከብዙ ድካምና ሙያዊ ውይይት በኋላ የማህበሩ የምሕንድስና ክፍል በአባላቱ የተሰሩ የተለያዩ አማራጭ ዲዛየኖችን አቀረበ:: ልዩ ልዩ ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የዲዛየን መረጣው ተጠናቀቀ:: የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴውም የማኅበሩን አባላት በማወያየት እያንዳንዱ የማኅበሩ አባል የወር ደሞዙን በዓመት ለዚህ ሕንጻ ግንባታ እንዲያዋጣ የውዴታ ግዴታ ቃል ገባ:: ይሄ የደሞዝ ልገሳ እያንዳንዱ አባል ለቤተ ክርስትያን ገቢ ከሚያደርገው አስራት እና በኩራት ክፍያ ውጭ ነው:: የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴውም በርካታ የገቢ ማስገኛዎችን ማለትም እንደ እግር ጉዞ : የመጻሕፍት ሽያጭ ወዘተ የመሰሉ ዘዴዎችን በመጠቀም ለሕንጻው ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ስብሰባ ተጀመረ:: በየዩንቨርስቲው ትምህርት ላይ ያሉ የማኅበሩ አባላትም የቁርስና የምሳ ዳቦአቸውን ካፋቸው በመነጠል ተሸጦ ለህንጻው ግንባታ ይውል ዘንድ ይለግሱ ነበር::
በዚህ ሁኔታ ማሰርያ ገንዘብ እየተሰበሰበ እነሆ ሕንጻው በብዙ ዘርፉ ተጠናቆአል ::ይሄ ሕንጻ የተሰራው ሙሉ በሙሉ የማኅበሩ አባላት መሀንዲሶችና አርክቴክቶች ሲሆን ወጭውም የተሸፈነው በማኅበሩ አባላት እና ደጋፊዎች ነው:: ማኅበሩ ይሄን ሕንጻ ለማሰራት የቤተ ክርስትያንን አስራት አልወሰደም::ከቤተ ክህነትም የተበጀተለት የገንዘብ ድጎማ የለም::
ማኅበሩ ዋናው አላማው ቤተ ክርስትያንን በ እውቀት በጉልበትና በገንዘብ ለመርዳት በመሆኑ ; ማኅበሩ የኔ የሚለው ሀብት የለውም:; የማኅበሩ ሀብት በሙሉ የቤተ ክርስትያንን ሀብት ነው::
ሕንጻውም ሲገዛ በባለቤትነት የተመዘገበው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን እንጂ በማኅበሩ አመራር ግለሰቦች ወይም ወይም በሌላ ድርጅት ስም አይደለም:: ይህንንም የሚመለከተው ጽፈት ቤት ሄዶ ማረጋገጥ ይቻላል:: እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ ካንዳንድ ሙሰኞች የሚሰማው ድምጽ ግን ይገርማል::
በእግዚአብሔር ፈቃድ አባላቶቹን በማስተባበር የጽፈት ቤት ሕንጻውን ማሰራቱ ወንጀል ነውን? የማኅበሩ አባላትስ ዶክተር ይሁኑ ፕሮፌሰር ማኅበራቸው ሕንጻ ውስጥ መገናኘታቸው : ስለ ቤተ ክርስትያን ጉዳይ መወያየታቸው ወንጀል ነውን?
ማኅበሩ ህንጻውን ብቻ ሳይሆን ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ አባላቱንም ገንብቷል:: ዲያቆን አባይነህ ካሴ ባንድ ጽሁፉ እንደገለጸው ማኅበረ ቅዱሳን ሲገነባ የኖረው አስተሳሰብን ጭምር ነው:: ሰዎች ለምን ሕንጻውን እንደሚገርማቸው ይደንቀኛል:: ምናለ ትውልዱ ውስጥ የገነባውን ኦርቶዶክሳዊ እና ሃይማኖታዊ ህንጻ ቢመለከቱ!
አዎ እኛም ማኅበረ ቅዱሳን ነን:: ማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚደረግ ትንኮሳ ሁሉ ቤተ ክርስትያን ላይ የሚደረግ የጥፋት አዋጅ ነው:: የሃሰት ክስ ይቁም::እግዚአብሔር ያያል:: በስጋም ያስቀጣል:: በሃይማኖትም ሃጥያት ነው::
” እውነት አርነት ታወጣሃለች”
EMF

No comments:

Post a Comment