Translate

Thursday, July 17, 2014

ጠበቆቻቸው በሌሉበት በጋዜጠኞች እና ጦማሪዎች ላይ የሽብር ክስ ተመሰረተ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) ከቤታቸው እና ከያሉበት ቦታ ታፍነው ከተወሰዱ ሶስት ወራት ያስቆጠሩት ዘጠኝ ጋዜጠኞች እና ጦማሪዎች ላይ፤ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ወንጀል እንዲቀጡ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው የአቤቱታ ሰነድ አመልክቷል።ፖሊስ ዘጠኙን ይዞ የቀረበው ያለምንም ማስጠንቀቂያ እና ቀጠሮ በመሆኑ ቤተሰብም ሆነ፤ ጠበቆቻቸው በስፍራው አልተገኙም ነበር። ሆኖም አቃቤ ህጉ ፖሊስ ባቀረባቸው ዘጠኝ ወጣቶች ላይ የክስ መዝገብ አስከፍቶ የክስ ቻርጁን ሰጥቷቸዋል።
እንደ ክስ ቻርጁ ከሆነ አቃቤ ህግ ሽብርተኛ ያላቸው ጦማሪያን፣ ሶልያና ሽመልስ (በሌለችበት ነው የተከሰሰችው)፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አቤል ዋበላ፣  ዘለዓለም ክብረት፣  ሲሆኑ ከነሱ ጋር ጋዜጠኞቹን አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬና ተስፋለም ወልደየስ በተመሣሳይ ሁኔታ በአሸባሪነት እንዲቀጡለት መጠየቁን የኢ.ኤም.ኤፍ ዜና አቀባይ ገልጾልናል –  ዛሬ ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. (ጁላይ 17፣ 2014)፡፡
የአሸባሪነት ክስ የተመሰረተባቸው ጋዜጠኞች እና ጦማርያን።
የአሸባሪነት ክስ የተመሰረተባቸው የዞን9 – ዘጠኝ ጋዜጠኞች እና ጦማርያን።
የኢ.ኤም.ኤፍ ዜና አቀባይ እንደገለጸው ከሆነ ፖሊስ ልደታ በሚገኘው ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በድንገት ይዟቸው በመቅረቡ ምክንያት ጠበቆቻቸው በስፍራው አልነበሩም።፡ በመሆኑም “ጥፋተኛ ነኝ ወይም አይደለሁም” ለማለት ጠበቆቻቸው በተገኙበት መፈጸም ስላለበት፤ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ነገ ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ እንደገና እንዲቀርቡ ተብሏል።
የሆኖ ሆኖ አቃቤ ህጉ አቅርቦት የነበረው ወይም በክስ ዝርዝሩ ላይ “ወጣቶቹ ከአሸባሪዎቹ ግንቦት ሰባት እና ኦነግ ጋር በመመሳጠር መንግስት ለመጣል ሙከራ አድርገዋል” ብሏል። ከነሱም መካከል በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት ሶሊያና ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ ጦማርያኑን በማስተባበር እና የውጭ ጉዳይ ሃላፊ በመሆን ሰርታለች የሚል ክስ አቅርበውባታል።

ያው እንደተለመደው የክሱ ሃሳብ በአጭሩ፤ “በህግ የተቋቋመውን መንግስት በረብሻ እና በብጥብጥ ለማፍረስ ከአሸባሪዎች ጋር ተባብረዋል።” የሚል ነበር።
ዘጠኙ ጋዜጠኞችና ጦማርያን ክስ ሳይመሰረትባቸው፤ ላለፉት ሶስት ወራት በእስር መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
(በተደጋጋሚ በድረ ገጻችን ላይ የምናወጣቸው ዜናዎች፤ ምንጫቸው ሳይጠቀስ ወይም “ኢ.ኤም.ኤፍ” የሚለው ተሰርዞ  በሌሎች ድረ ገጾች ላይ እያየናቸው ነው። ምንጭ አለመጥቀስ ነውር ብቻ ሳይሆን፤ ጸያፍ ተግባር ነውና አንባቢዎች ጭምር ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ድረ ገጾችን  ምከሩልን።)

No comments:

Post a Comment