ከአንድነት ሃይሌ
በየመን የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መታገትን በመስማቴ አዘንኩ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በዝምታ እየተቀበላቸው የሚገኙትን በደሎችም መለስ አድርጌ ባጭሩ እንድቃኝ አስገደደኝ።
ያሳዝናል! በአመት ከ70 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ህፃናት በማደጎነት ሲሸጡ እያየን፣ እየሰማን፤ ከ45 ሺህ በላይ ሴቶቻችን ለሳውዲ አረቢያ በቤት ሰራተኝነት ሲቸረቸሩና፤ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ዜጎቻችን በተመሳሳይ መልኩ ለሌሎች አረብ ሃገራት በሃራጭ ሲሸጡ እያየን፣ እየሰማን፤ ሴቶቻችን በየ አረብ ሃገሩ ለመስማት እጅግ በሚያዳግት ሁኔታ አሰቃቂ በደሎች ባደባባይ ሲፈፀምባቸው እያየን፣ እየሰማን፤ አያሌ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍና ለማሻሻል ወደተለያዩ ሃገራት ተሰደው ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ እያየን፣ እየሰማን፤ ከዚህም በላይ ደግሞ ይህ ሁሉ በደል በዜጎች ላይ ሲፈፀም ቢያንስ ተቃውሞውን ሊያሰማ ፈፅሞ ፍላጎት የሌለው፤ ይባስ ብሎ በደሉን በተቃወሙ ዜጎች ላይ ከበዳዮቹ ሃገራት ጋር በማበር ንፁሃን ዜጎችን የሚደበድብ፣ የሚያስር ጭካኝ ስርዓት በጫንቃችን ተሸክመን፤ አንጀታችን እያረረ፣ ልባችን በሃዘን እየተጎዳ፣ ሞራላችን በውድቀት እየተሰበረ፣ አንገታችንን ደፍተን በዝምታ እየኖርን እንገኛለን።
ሁላችንም እንደምናቀው የኬኒያ፣ የሱዳን፣ የጅቡቲና፣ ሌሎች የጎረቤት ሃገራት በወያኔ በደል ምክንያት ሳይወዱ ተገደው ህይወታቸውን ለማዳን ከሃገራቸው በተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ላይ በተደጋጋሚ አፈና እየፈፀሙ ይገኛሉ። በቅርቡ በኬኒያ መንግስት ታፍኖ ለወያኔ ከተሰጠ በኋላ ህይወቱ እስክታልፍ ድረስ ለአመታት በወያኔ እስር ቤት በተሰቃየው በወንድማችን ወጣት ተስፋሁን ጨመዳ ላይ የተፈፀመውን አሳዛኝ በደልና በኦብነግ አመራር አባላት ላይ የተደረገው አፈና፤ በደቡብ ሱዳን በአቶ ኦኬሎ አኩአይና ሌሎች የጋምቤላ ንቅናቄ አባላት ላይ በተመሳሳይ መልኩ የተደረገው አፈና ያለምንም ተጨባጭ እርምጃ በዝምታ ታልፈዋል። ዛሬ ደግሞ የየመን መንግስት በአሳዛኝ ሁኔታ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ማገቱ በመገናኛ ብዙሃን ተነግሯል።
በዜጎቻችን ላይ እየደረሱ ለሚገኙት አሰቃቂ በደሎች በዋነኝነት ተጠያቂው የወያኔ መንግስት ቢሆንም፤ በስደት የሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ ከወያኔ መንግስት ጋር በመተባበር በተደጋጋሚ አፈና እየፈፀሙና አጋልጠው እየሰጡ የሚገኙ የጎረቤት ሃገራት ወደፊት በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም። ነገር ግን ወገኖቼ ይህ አፈና እስከመቼ ይቀጥላል!? ዜጎች ጭቆናን በመቃወማቸው ብቻ በስደት ከሚደርስባቸው ስቃይ በላይ ለምን በየ ጎረቤት ሃገሩ ይታፈናሉ!? እኛ ኢትዮጵያውያን እስከመቼ እየተናቅን እንኖራለን!? ጎበዝ ዝምታውና መነጣጠሉ ይብቃ! የሚደርስብንን አፈና ለማስቆምና ራሳችንን ለመከላከል ሁላችንም በአንድነት ጫና መፍጠርና ማስገደድ ግድ ስለሚለን፤ በምንችለው ሁሉ መረባረብና መተባበር ይኖርብናል እላለሁ።
አፈናው ይብቃ!
No comments:
Post a Comment